የየመን አማጺያን በርካታ የሳኡዲ ወታደሮች መማረካቸውን ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሁቲ አማጺያን በየመንና በሳኡዲ ድንበር መካከል በሚገኝ ቦታ በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ቁጥር ያላቸው የሳኡዲ አረቢያ ወታደሮች መማረካቸውን አስታወቁ።
የሁቲ አማጺያን ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ናጅራን ተብላ በምትታወቀው የሳኡዲ አነስተኛ መንደር ውስጥ የሦስት ብርጌድ ወታደሮች እጃቸውን ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ እንደሚሉት በሺዎች የሚቆጠሩ የሳኡዲ ወታደሮች የተያዙ ሲሆን በርካቶች ደግሞ ተደግለዋል። የሳኡዲ ባለስልጣናት ስለሁኔታው እስካሁን ምንም ያሉት ነገር የለም።
''ይህ ክስተት ግጭቱ ከተጀመረ አንስቶ እጅግ ከፍተኛ የሚባል ነው'' ብለዋል ቃል አቀባዩ።
የሳኡዲ ሠራዊት ላይ በሰው ህይወትም ሆነ በጦር መሳሪያ ከፍተኛ የሚባል ውድምት መድረሱን ቃል አቀባዩ ኮሎኔል ያሂያ ሳሬአ አክለዋል። ሁሉም የተያዙት ወታደሮችም ዛሬ በሁቲ አማጺያን በሚመራው የአል ማሲራህ ቴሌቪዥን እንደሚቀርቡ ታውቋል።
በኢራን የሚደገፉት የየመን ሁቲ አማፂያን ከሁለት ሳምንት በፊት በሳዑዲ ሁለት የነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማት ላይ ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነቱን እንወስዳለን ማለታቸው ይታወሳል።
ነገር ግን አሜሪካም ሆነች ሳዑዲ አረቢያ ለጥቃቱ ተጠያቂ ያደረጉት ኢራንን ነው።
በኢራን መንግሥት ድጋፍ የሚደረግላቸው የሁቲ አማጽያን የየመንን መንግሥትና የሳዑዲ መራሹን ኃይል ሲፋለሙ ቆይተዋል።
የየመኑ ፕሬዝደንት አብደራቡህ ማንሱር ከመዲናዋ ሰነዓ በሁቲ አማጽያን ተባረው ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ ሃገሪቱ ላለፉት 4 ዓመታት በጦርነት ስትታመስ ቆይታለች።
ሳዑዲ ከመዲናቸው የተባረሩትን ፕሬዝደንት በመደገፍ በሁቲ አማጽያን ላይ በየቀኑ ማለት በሚቻል መልኩ የአየር ጥቃቶችን ትፈጽማለች። የሁቲ አማጽያን በበኩላቸው ሚሳኤሎችን ወደ ሳዑዲ ያስወነጭፋሉ።
የእርስ በርስ ግጭቱ ከ24 ሚሊዮን በላይ ከሚሆነው የየመን ሕዝብ 80 በመቶው ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። ከእነዚህ መካከል 10 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በቀጥተኛ የምግብና ውሃ እርዳታ ነው ህይወታቸውን እየመሩ የሚገኙት።
እ.አ.አ. ከ2016 ጀምሮ በግጭቱ ከ70 ሺ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ይገምታል።












