ሙጋቤ በተወለዱበት ከተማ እንዲቀበሩ መንግሥት ወሰነ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የዚምባብዌ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ የቀብር ስፍራ ካጨቃጨቀ በኋላ የመጨረሻ ውሳኔ አግኝቶ በትውልድ ከተማቸው እንዲቀበሩ ተወስኗል።
በ95 ዓመታቸው የሞቱት ሙጋቤ ከፍተኛ የአህጉሪቱ ሹማምንት በተገኙበት በሀገሪቱ መናገሻ ከተማ ሀራሬ ሽኝት የተደረገላቸው በቅርብ ነበር።
ቤተሰቦቻቸው በትውልድ ስፍራቸው ዝቪምባ አፅማቸው ይረፍ ብለው ቢጠይቁም የዚምባብዌ መንግሥት ግን አሻፈረኝ በማለት በሀራሬ የጀግኖች መካነ መቃብር ቀብራቸው እንደሚፈፀም ተናግሮ ነበር።
በዚህም የተነሳ ቤተሰቦቻቸው ተቃውሞዋቸውን ደጋግመው አሰምተዋል።
የዚምባብዌ መንግሥት ቀብራቸውን ይፈፀምበታል ባለው ስፍራ ለስማቸው መጠሪያ ሐውልት አቆማለሁ፣ በትውልድም ሲታወሱም ይኖራሉ በማለቱ አስከሬናቸው በቤታቸው ተቀምጦ ቆይቶ ነበር።
በመጨረሻም ሐሙስ ዕለት መንግሥት የቤተሰቡን የማያቋርጥ አቤቱታ ሰምቶ ፈቃዳቸው ይፈፀም ዘንድ ውሳኔ አሳልፏል።
መንግሥት በመጨረሻ የሀሳብ ለውጥ ለምን እንዳደረገ የታወቀ ነገር የለም።
የሀገሪቱ ኮሙኑኬሽን ሚኒስትር መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ውሳኔው የተላለፈው "በክብር ያለፉ ጀግኖቻችን ቤተሰቦችን ፍላጎትና ምኞት ከማክበር" መሆኑን ጠቅሷል።
ሙጋቤ ሕይወታቸው ያለፈው የካንሰር ህክምና እየተከታተሉበት በነበረው ሲንጋፖር ነበር።
ዜና እረፍታቸው ከተሰማ በኋላ ቤተሰቦቻቸው ቀብራቸው ስለሚፈፀምበት ስፍራ መንግሥት እንዳላማከራቸው ተናግረው ነበር።
ቤተሰቡ ባወጣው መግለጫም ላይ የመንግሥት እቅድ ተችተው " ከሙጋቤ ፍላጎት ውጪ" በጀግኖች መካነ መቃብር መቀበር የለባቸውም ሲሉ እርምጃውን ኮንነዋል።
ቤተሰቡ እንዳለው ለባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ የተናገሩት የመጨረሻ ቃል ስርዓተ ቀብሩ እስኪፈፀም ድረስ ከአጠገባቸው እንዳትርቅ ነበር።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2017 ላይ የዚምባብዌ መከላከያ ኃይል፤ ሮበርት ሙጋቤ ለሦስት አሥርት ዓመታት ይዘውት ከነበረው መንበረ ሥልጣን ማስነሳቱ ይታወሳል።
በ1980 በዚምባብዌ የተካሄደውን የመጀመሪያ ምርጫ አሸንፈው ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው የነበሩት ሙጋቤ፤ 1987 ላይ ፕሬዘዳንት ሆነዋል።













