ዕፅ በማዘዋወር የተጠረጠረው ኬንያዊ ቱጃር ቤት በፖሊስ እየተበረበረ ነው

የኬንያ ፖሊስ ዕፅ በማዘዋወር ወንጀል ጠርጥረነዋል ያሉትን አሊ ፑንጃኒ በመርመር ላይ ናቸው፤ ሞምባሳ የሚገኘው መኖሪያ ቤቱንም ትላንት ሲያስሱ ውለዋል።

ሚስቱ ነኝ የምትል አንድ የኔፓል ዜግነት ያላት ሴት እና ሌሎች ሁለት ወንዶች ከአሰሳው ጋር በተያያዘ ሶስት ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ግለሰቦቹ የተያዙት ኒያሊ በተሰኘችው የሞምባሳ መንደር ውስጥ በሚገኘው የፑንጃኒ መኖሪያ ቤት ውስጥ መሆኑ ታውቋል።

አሊ ፑንጃኒ፣ ሁለቱ ኬንያውያን ወንድማማቾች ባክታሽ እና ኢብራሂም አካሽ፣ እንዲሁም ቪጄ ጎስዋሚ የተባለ ግለሰብ ከዕፅ ዝውውር ጋር በተያያዘ በአሜሪካ መንግሥት ይፈለጋሉ።

ፑንጃኒ፤ እሳከሁን በዕፅ ዝውውር ስለመጠርጠሩ ምንም የሰጠው አስተያየት የለም።

ወንድማማቾቹ ባለፈው ዓመት ዕፅ ታዘዋውራላችሁ፤ 100 ኪሎ ግራም ሄሮይን የተባለ ዕፅ ወደ አሜሪካ ለማስገባትም አቅዳችኋል ተብሎ የቀረበባቸውን ክስ ማመናቸው አይዘነጋም።

የወንድማማቾቹ ክስ እስከ ዕድሜ ልክ ሊያስቀጣ ይችላል ቢባልም የተባባሪዎቻቸውን ስም በማጋለጥ ቅጣታቸውን ለማስቀለል አስበዋል የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ነው።

የአሊ ፑንጃኒ የግል ጠበቃ ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ ደንበኛው የሕክምና እርዳታ ለማገኝት ወደ ሕንድ እንዳቀኑ አስታውቀዋል።

የአሊ ፑንጃኒ ቤተሰቦች ቱጃሩ የሆስፒታል አልጋ ላይ ተኝቶ ሕክምና ሲከታተል የሚያሳይ ፎቶ ለቀዋል።

የጉምቱው ቱጃር ክስ ኒው ዮርክ ውስጥ በሚገኝ ፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል።