በምዕራብ ሀረርጌ ዞን በተሰነዘረ ጥቃት ሰባት ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሀረርጌ ዞን በተሰነዘረ ጥቃት የሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለፀ። ጥቃቱ የተሰነዘረው ኦሮሚያ ክልልን ከአፋር በምታዋስነው ጉምቢ ቦርደዴ ወረዳ ጉምቢ ቀበሌ ነው።

የሁለቱ ክልል አጎራባች ማህበረሰቦች ለረዥም ጊዜ አብረው የኖሩ ቢሆንም ዛሬ ነሐሴ 2 ቀን 2011 ዓ.ም ባልታወቀ ምክንያት ከአፋር ክልል አጎራባች ቀበሌ በኩል ጥቃት መሰንዘሩን የምዕራብ ሃረርጌ ዞን ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ሚሊዮን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

''ባልታወቀ ምክንያት የተወሰኑ ግለሰቦች መሳሪያ ይዘው ወደ ኦሮሚያ ክልል ጉምቢ ቀበሌ ገብተው ከጠዋቱ 12 ጀምሮ ጥቃት አድርሰዋል'' ብለዋል።

በጥቃቱ የጉምቢ ቀበሌ ኗሪ የሆኑ 7 ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ ጉዳት የደረሰባቸው 3 ደግሞ በአዳማ ከተማ ህክምና እየተከታተሉ እንደሆነም ሃላፊው አክለዋል።

ሌላኛው ያነጋገርናቸው የምዕራብ ሃረርጌ ዞን የፀጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ከድር መሃመድ ጥቃቱ የተፈፀመው በአፋር ልዩ ሃይል ነው ቢሉም አቶ ፍቃዱ ግን እስካሁን ባለው መረጃ ጥቃቱን የፈፀሙት ከፊል አርሶ አደሮች እንደሆኑ ይገልፃሉ።

''ጥቃቱን የፈጸሙት አካላት ወደፊት በፖሊስና በሚመለከታቸው አካላት ተጣርቶ የሚቀርብ መሆኑ እንዳለ ሆኖ አሁን ከአካባቢው ነዋሪዎች መረዳት እንደቻልነው ግን ጥቃት አድራሾቹ የሚታወቁና በአጎራባች ቀበሌ የሚኖሩ የአፋር ክልል ነዋሪ ከፊል አርሶ አደሮች ናቸው። ከጀርባ ሌላ ሃይል ይኑር አይኑር የሚለው ግን ገና ወደፊት ተጣርቶ ለህዝቡ ግልጽ የሚሆን ነገር ነው'' በማለት አክለዋል።

ጉዳዩን አስመልክተን ያነጋገርናቸው የአፋር ክልል ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አህመድ መሀመድም በአፋር በኩል አንድ ሰው መቁሰሉንና እስካሁን ጥቃቱን ማን እንደፈፀመ የሚታወቅ ነገር አለመኖሩንም ይናገራሉ።

''አሁን ቦታው ላይ የመከላከያ ሰራዊትና ፌደራል ፖሊስ አስገብተን የማረጋጋትና የማጣራት ስራ እየተሰራ ነው። በህዝቡ ላይ ጉዳት ያደረሱ አካላትም ተለይተው ለህግ እንዲቀርቡ ተስማምተናል።''

ከጥቃቱ ጋር ተያያዘ እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋለ እንደሌለም አቶ አህመድ አረጋግጠዋል።