የኦሃዮው ታጣቂ እህቱንና ስምንት ሰዎችን ገደለ

የፎቶው ባለመብት, CBS NEWS
በሰላሳ ሰከንዶች ውስጥ በተፈጸመው ጥቃት ታጣቂው እህቱን ጨምሮ ቢያንስ ስምንት ሰዎችን መግደሉን ፖሊስ ገለጸ።
በአሜሪካዋ የኦሃዮ ግዛት የውስጥ የተፈጸመው የዚህ ጥቃት ፈጻሚ ኮነር ቤትስ የተባለ የ24 ዓመት ወጣት ሲሆን፤ በቅርብ የነበሩ ፖሊሶች የተኩስ ድምጽ ከሰሙ በኋላ ግለሰቡ በርካታ ሰው ተሰብስቦበት ወደነበረ መጠጥ ቤት እንዳይሄድ አድርገዋል።
የዳይተን ፖሊስ ኃላፊ እንደተናገሩት ጥቃት ፈጻሚው ወደ መጠጥ ቤቱ መግባት ቢችል ኖሮ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት "ዘግናኝ"ይሆን እንደነበር ተናግረዋል።
ጠመንጃ አንጋቹ ግለሰብ ለጥቃቱ ምክንያቱ ምን እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
በ24 ሰዓታት ውስጥ በተፈጸመው በዚህ ሁለተኛ ጥቃት ቢያንስ 27 ሰዎች የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ጥቃት አድራሹ የመጀመሪያውን ጥቃት ከፈጸመ በኋላ በርካታ ሰዎች ወደተሰበሰቡበት ቦታ እየሮጠ በመሄድ ላይ እያለ ነው በፖሊስ ጥይት የተመታው።
ግለሰቡ ሰውነትን ከጥይት የሚከላከል ልብስ ያጠለቀ ሲሆን ተጨማሪ ጥይቶችንም ይዞ ነበር። አጥቂው ኔድ ፒፐርስ ወደተባለው የምሽት ክበብ የመግባት ዕድልን ቢያገኝ ኖሮ ከያዘው የጦር መሳሪያ አንጻር ከባድ ጉዳትን ሊያደርስ ይችል እንደነበር ፖሊስ ገልጿል።
ጥቃት ፈጻሚው የጦር መሳሪያውን በኢንተርኔት አማካይነት ከቴክሳስ ግዛት የገዛ ሲሆን፤ በግለ ታሩኩ ላይ ምንም አጠራጣሪ ነገር ስላልነበረ በሕጋዊ መንገድ የጦር መሳሪያ እንዳይገዛ ለመከልከል የሚያስችል ምክንያት እንዳለነበረ ፖሊስ አመልክቷል።
ጥቃቱ ፈጻሚው ታናሽ እህቱ የሆነችውን የ22 ዓመቷ ሜጋን ቤትስንም ገድሏል። ፖሊስ እንዳለውም እህትየው ከመጀመሪያዎቹ ሟቾች መካከል ናት።
ጥቃቱ ከዘር ጥላቻ ጋር የተያያዘ ይሁን አይሁን የታወቀ ነገር እንደሌለና ለምን ድርጊቱን እንደፈጸመ ለመገመት ጊዜው እንዳልሆነ ፖሊስ ገልጾል።
የመገናኛ ብዙሃን የጥቃት ፈጻሚውን ስም ይፋ ካደረጉ በኋላ ፖሊስ በሰጠው መረጃ ታጣቂው ኮነር ቤትስ የተባለ ኦሃዮ ግዛት ውስጥ ቤልብሩክ ነዋሪ የሆነ የ24 ዓመት ወጣት ነው።












