የሥራ ቃለመጠይቅ ማድረግ ያስፈራዎታል? መፍትሄዎቹን እነሆ

ቃለመጠይቅ ላይ ፈገግ ያለች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቃለመጠይቅ አሁንም ሠራተኞችን ለመመልመል ወሳኝ ዘዴ ነው

ዓመታትን ተምረው ሲመረቁ፣ በሰለጠኑበት ሙያ ሥራ ማግኘት ፈታኝ ሲሆን፣ በዛ ላይ ደግሞ አሠሪዎች ምን እንደሚፈልጉ ሳያውቁ ሲቀር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆናል። ሠራተኞችን የመቅጠሪያ ዘዴ በየጊዜው የሚለዋወጥ ቢሆንም አካላዊ ቃለ-መጠይቅ ግን እስካሁን ያልተቀየረ የምልመላ ወሳኝ አካል ነው።

"ቃለ-መጠይቅ እስካሁን ለማንኛውም የሥራ ምልመላ በጣም አስፈላጊው ሠራተኞችን የመለያ መንገድ ነው" የምትለው ጄን ቲፕን በሎይድ ባንኪንግ ግሩፕ የሰው ኃይል ባለሙያ ናት።

ከሰው ፊት ሃሳብን መግለፅና ጥያቄዎችን መመለስ መቻል የሰዎችን ሥራ የማግኘት እድል ይወስናል ትላለች።

በቃለመጠይቅ ጊዜ የሚረዱ ጥቂት ነጥቦች እነሆ፡

1.ስለመሥሪያ ቤቱ ጥናት ያድርጉ

አንድ ወጣት ላፕቶፑን ተጠቅሞ ነጥቦችን ሲወስድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቃለመጠይቁ ምን ዓይነት ሊመስል እንደሚችል ጥናት ያድርጉ

በመጨረሻ የሚፈልጉትን ስራ አግኝተው ለቃለመጠይቅ ከደረሱ ከቃለመጠይቁ በፊት ስለ ድርጅቱ በቂ ጥናት ማድረግዎን እንዳይዘነጉ።

ጥናትዎ ድርጅቱ ምን አይነት ሥራ ላይ ነው የተሰማራው? አመታዊ ገቢው ምን ያህል ነው? አለቃው ማን ነው? የሚሉትን ጥያቄዎችና የድርጅቱን ቀንደኛ ተፎካካሪዎች ለማወቅ ይሞክሩ።

ስለድርጅቱ ለማጥናት ሲፈልጉም ከድረ-ገፅ መጀመር ስራን ያቀላል።

ድርጅቱ ላይ ካደረጉት ጥናት ባለፈ ቃለ መጠይቅ የሚያደርግልዎትን ኃላፊ ለማወቅ ይሞክሩ።

ቃለመጠይቁም ካለቀ በኋላ የሚጠይቁት ጥያቄ ማዘጋጀት ስለድርጅቱ ያለዎትን እውቀትና ፍላጎት ስለሚያሳይ የተመራጭነት እድልዎትን ያሰፋል።

2.ሊጠየቁ የሚችሏቸውን ጥያቄዎች ይለማመዱ

አንዲት ሴት ጓደኞችዋን እንደ ስራ ቀጣሪዎች ደርድራ ስትለማመድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጓደኞችዎን ደርድረው ቃለመጠይቅ ማድረግ ይለማመዱ

ቃለመጠይቅ ከመግባትዎ በፊት ሊጠየቁ ይችላሉ ብለው የሚያስቧቸውን ጥያቄዎች መርጠው በመመለስ ይለማመዱ።

ጥያቄዎቹ ከከበድዎት የተለያዩ ጥያቄዎችን እንዴት ባለ መልኩ መመለስ እንዳለብን የሚያስረዱ ድረ-ገፆችን መመልከት ይችላሉ።

መልስዎትን ሲያዘጋጁ ብዙ ጊዜ ካሳለፏቸው የሥራ ልምዶች ምሳሌዎችን እየወሰዱ ቢሆን ይመረጣል። ምሳሌዎትንም መቼ፣ የትና እንዴት እንዳደረጉት በመግለፅ ጥልቀት ይስጡት።

የሚሰጧቸው መልሶች ከባለፈው የሥራ ልምድዎ ተነስተው በአዲሱ የሥራ ዘርፍ ላይ የሚፈጥሩትን መልካም እሴት ቢያስረዱ መልካም ነው።

3.ቀልብን የሚገዛ አለባበስ ይልበሱ

ሱፍ የለበሰ ወጣት ወንድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ራስዎን ከተጠራጠሩ በደንብ በመልበስ የራስ መተማመንዎን ይጨምሩ

የመጀመሪያ እይታ አሁንም ወሳኝ ነው።

አንዳንድ ቀጣሪዎች ውሳኔያቸውን የሚያደርጉት በ30 ሰከንድ ውስጥ ነው። አንዴ የአሰሪዎን ቀልብ ካልገዙ አስገራሚ መልሶችን ቢመልሱም ስራውን የማግኘት እድሎ ይጠባል።

ድርጅቱ የአለባበስ ምርጫ ባይኖረውም በቃለመጠይቅዎ ጊዜ ግን በጅንስ እንዲመጡ አይጠብቁም። ሥራ ቀጣሪዎች ሠራተኞች ለቃለመጠይቅ ሲመጡ ለሥራው የሚመጥነውን "ፕሮፌሽናል" ልብስ እንዲለብሱ ይጠበቃሉ። ለወንዶች ሱፍ በከረባት የተመረጠ እንደሆነ የቀጣሪዎች ሃሳብ ነው።

ቀለል ያለ ቃለመጠይቅ ከሆነ ደግሞ ንፁህና የተተኮሰ ልብስ ቢለብሱ መልካም ይሆናል።

4.አጨባበጥዎን ያስተካክሉ

ቀጣሪና ተቀጣሪ ሰላም ሲባባሉ የሚያሳይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከቃለመጠይቅዎ በፊት የሚያደርጉት አጨባበጥ ሚና አለው

ብዙ ጊዜ ችላ የምንለው ነገር ቢሆንም ሥራ ቀጣሪዎ በእጅ አጨባበጥዎ ሊገምትዎት ይችላል።

ትክክለኛ ጠንከር ያለ ሰላምታ ደፋር፣ የሥራ ሰውና ስለራስዎ ያለዎትን በጎ ግንዛቤ ይናገራል። ነገር ግን ከመጠን ያለፈ ጠንካራ ሰላምታ የሚሰጡ ከሆነ የበላይነት ባህሪ እንዳለዎት ሊናገር ይችላል። በሌላ መልኩ እጅዎ ላላ ያለ ከሆነ የማፈርና የመፍራት ባህሪ እንዳለዎት ያሳብቃል።

ይሄንንም ለማሻሻል ጓደኞችዎን ሰላም በማለት ተለማምደው እጆትን ማላላት ወይም ማጥበቅ እንዳለብዎት ይለዩ።

የቃለመጠይቁ ቀን ሰላምታ ሲሰጡ ዓይን ለዓይን መተያየትን አይዘንጉ። ከሰላምታ በፊትም የእጆትን ላብ መጥረጊያ መሃረብ መያዝ እንዳይረሱ ማንም ሰው በላብ የተጠመቀ መዳፍ መጨበጥ አይፈልግም።

5.ፈገግታ

በፈገግታ የታጀበ ወጣት ወንድ በቃለመጠይቅ ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እዚህ በመገኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ!

ተጨንቀውና በሃሳብ ተውጠው ባሉበት ጊዜ ሌላው ቀርቶ ስሞትንም ሊረሱት ይችላሉ።

ፈገግታ በቀላሉ ሰላምታ ማስተላለፍ ሲችል "እዚ ስለተገኘው ደስ ብሎኛል፤ ደስተኛ ሰው ነኝ" ይላል። ስለዚህ በሩን ከፍተው ከገቡበት ቅፅበት ጀምሮ ፊቶን ፈገግታ ባይለየው እድሎትን ያሰፋሎታል።

አካላዊ አቀማመጥን በተመለከተ ደግሞ ቀጥ ብሎ መቀመጥ ከፈገግታ ጋር ተጨምሮ መልካም አካላዊ ገፅታ ይሰጥዎታል።

6.ጭንቀት እድልዎን እንዲያሳጣዎ አይፍቀዱለት

ሰዎች ለቃለመጠይቅ ተደርድረው ተቀምጠዋል፤ አንዲት ሴት በቅርበት ካሜራውን ትመለከታለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከቃለመጠይቅ በፊት ራሶትን ያረጋጉ፤ ትንፋሽ መውሰድ አንዱ መንገድ ነው

አድሬናሊን በጣም አስገራሚ ነገሮችን እንድናካሂድ ወይም ደግሞ በጣም የወረደ ስራ እንድንሰራ ሊያደርገን ይችላል።

ቃለመጠይቁን ስንደርስ ያጠናናቸውና ለመመለስ የተዘጋጀናቸው መልሶች በሙሉ በነው ሊጠፉ ይችላሉ። ከዚህም አልፈው በአካላዊ ገፅታችን እጃችን ሲንቀጠቀጥ፣ ሲያልበን ወይም ስንደናበር ለሰዎች ሊታይ ይችላል።

እርስዎ እንደዚህ ያለ ጭንቀት የሚያስቸግርዎት ከሆነ ከቃለመጠይቁ በፊት ራስዎን ለማረጋጋት የሚረዱ እንደ ትንፋሽ መውሰድ የመሳሰሉ ልምዶችን ሊያዳብሩ ይችላሉ።

መልካሙ ነገር አድሬናሊን የተለየና በጣም አሪፍ ቃለመጠይቅ እንድናደርግ ሊረዳን ስለሚችል ነው።

7.እርስዎን ምን ልዩ እንደሚያደርጎት ይናገሩ

ወጣት ሴት ቃለመጠይቅ ሲደረግላት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በቃለመጠይቅ ላይ እርስዎን ልዩ የሚያደርጎትን ነገሮች ይግለፁ

የኮንስትራክሽን ድርጅት ባለቤት የሆኑት ዴርሞት ሮኒ "ፊት ለፊት የሚደረግ ቃለመጠይቅ ሰዎች ስለራሳቸው ልዩ ተሰጥኦ፣ ፍላጎትና ባህሪ እንዲናገሩ እድል ይሰጣቸዋል" ይላሉ። በቃለመጠየቁ ጊዜ ራስዎን በጥልቀት ማስተዋወቅ መቻል አለብዎት።

ከዚህም በተጨማሪ ምን ያህል ሥራውን ለማግኘት ጉጉት እንዳለዎት፣ ድርጅቱን ምን ያህል እንደሚወዱትና መሥራት እንደሚፈልጉ መግለፅ መልካም ነው።

8.ተስፋ አይቁረጡ

አንዲት ሴት ቃለመጠይቅ ስትደረግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የሚችሉትን ጥረት ማድረግ ይቀጥሉ!

ቃለመጠይቁ በጠበቁት መንገድ እየተሳካልዎት ባይሆንም እርስዎ ግን እንደማያገኙት ወስነው ከመሞከር መሸሽ የለብዎትም። ቃለመጠይቅ አድራጊዎቹም እንዳልወደድዎት ሊሰማዎት ይችላል፤ ነገር ግን ውሳኔያቸውን ሳይሰሙ አይወስኑ።

የሥራ ቀጣሪው የሚፈልገው የእርስዎን ቀጣይ መልስ ሊሆን ስለሚችል ለሁሉም ጥያቄዎች የሚችሉትንና አሪፍ የሚሉትን ይመልሱ።