የላሙ ፕሮጀክት ቦርድ አባላት በኢትዮጵያ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው

የፎቶው ባለመብት, Embassy of Ethiopia in Kenya
የላሙ ኮሪዶር ልማት ፕሮጀክት የቦርድ አባላት በኢትዮጵያ ጉብኝት ሊያደርጉ መሆኑን በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምሳሲ አስታወቀ።
በፕሮጀክቱ ዳይሬክተር ጄኔራል ሲልቪስተር ካሱኩ የሚመራው ይህ የልዑክ ቡድን፤ ከሚያዚያ 26 እስከ ግንቦት 2 ቀን 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ በሚያደርገው ቆይታ ከተለያዩ የመንግሥት አካላት ጋር ውይይት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህ ጉብኝት ላይ 30 የሚሆኑ አባላት የላሙ ኮርደር ልማት የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ ከኢትዮጵያ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር የሚወያይ ሲሆን በተጨማሪ በኬንያ በኩል የደረሰበትን ደረጃ ማብራሪያ እንደሚያቀርብ ኤምባሲው አስታውቋል።
ከኬንያ የውጭ ጉዳይ የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ የላሙ ጉዳዮች ባለስልጣን እና የሌሎች ተቋሞች ኃላፊዎችን ያከተተው ይህ ቡድን፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እንደሚጎበኝ ተጠቅሷል።
ላሙ ወደብ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ትራንስፖርት ኮሪዶር (ላፕሴት) በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ እና ብዙ ተስፋ የተጣለበት የመሠረተ ልማት ግንባታ ሲሆን፤ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳንን የሚያገናኝ ፕሮጀክት ነው።
በፕሮጀክቱ የወደብ እና አየር ማረፊያ ልማት፣ ሦስቱን ሃገራት የሚያገናኙ የባቡር መስመር እና መንገድ ግንባታ፣ እንዲሁም ነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ዝርጋታ ተካተውበታል።
በኬንያ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም እና የላሙ ፕሮጀክት ዳይሬክተር ጄኔራል በቅርብ በሚመረቀው የላሙ ወደብ የመርከቦች ማቆያ ዙሪያ ተወያይተዋል።
የላሙ ወደብ ልማት የአካባቢው አገሮች ኢኮኖሚ ለማስተሳሰር አስፈላጊ በመሆኑ ኢትዮጵያ ለስኬታማነቱ እንደምትሰራ አምባሳደሩ ገልፀውላቸዋል።
ዳይሬክትር ጄኔራሉ በላሙ ሦስት የመርከቦች ማቆያ ሥራ እየተፋጠነ መሆኑን ገልፀው ይህም የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ብለዋል።












