ዶ/ር አብዲሳ ዘርአይ፡ "ከውጪ የገቡ ሚዲያዎች 'ማገገምያ' መግባት ያለባቸው ይመስለኛል"

የፕሬስ ነጻነት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በተደጋጋሚ እየተገለፀ እንዳለው በአዲሱ ጠ/ሚ እና በለውጥ ሃይል መምጣት የፖለቲካ ምህዳሩን መስፋት ተከትሎ ሚዲያውም ከፈት ብሏል።

አሸባሪ የተባሉና በውጭ የነበሩ ሚዲያዎች መግባታቸው፣ በመንግስት ተዘግተው የነበሩ ድረ ገፆች ዳግም መከፈታቸው፣ በውጪ ሃገር ስርዓቱን ሲታገሉ የነበሩ ጋዜጠኞች ወደ ሃገር መግባት፣ አገር ውስጥ እስር ላይ የነበሩ ጋዜጠኞች መለቀቅ ፣ የህትመት ውጤቶችና መገናኛ ብዙሃን በመበርከታቸው የተለያዩ ሃሳቦች እየተንፀባረቁ መሆኑ ትልቅ አዎንታዊ እርምጃ ነው።

ይህ የሚዲያ ክፍት መሆንና ነፃነት ለማህበረሰቡ ምን አመጣ? ማህበረሰቡን ወደ ውይይትና መግበባት አምጥቷል ወይ? የሚለው ግን አሁንም ጥያቄ ነው።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት የቀድሞ ዲን የነበሩትና በአሁኑ ወቅት በአሜሪካው ኒው ሜክሲኮ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩት ዶ/ር አብዲሳ ዘርአይን ከለውጡ በኋላ የሚዲያውን እንቅስቃሴ በማስመልከት አነጋግረናቸዋል።

ሚዲያው ከፈት ከማለቱ ምን ተገኘ?

ዶ/ር አብዲሳ ዘርአይ፡ ሚዲያው መከፈቱ ወሳኝ አዎንታዊ እርምጃ ነው። ነፃነቱም በጣም አስፈላጊ ነው ። ነገር ግን ጥያቄ የሚሆኑ ነገሮችም አሉ። ከውጭ የገቡት ሚዲያዎችን ስንመለከት በጫና ከሃገር የወጡ፤ ሙያው የሚመራቸው ሳይሆን ሥርዓቱን ሲታገሉ የነበሩ ነፃ አውጪዎች ናቸው። ስለዚህ አገር ቤት ቢገቡም ከነፃ አውጪነታቸው በሙያ ወደሚመራ ሚዲያ የሚያደርጉት ሽግግር ቀላል አይሆንም።

አሁንም የቀደመ የነፃ አውጪነት መንፈስ የለቀቃቸውም አይመስልም። ጋዜጠኞቹ ራሳቸው ናቸው ፤ አሠራራቸውም ያው እንደቀደመው ነው። ስለዚህ ቢሯቸውን ቀይረው አዲስ አበባ ስለከተሙ ብቻ ሙያውን ተከትለው ይሠራሉ ማለት ይከብዳል።

በትጥቅ ትግል ኢህአዴግን ሲታገሉ የነበሩ ወደ አገረ ቤት ሲገቡ ትጥቅ ፈትተውና ተሃድሶ ወስደው ነው ወደ ማኅበረሰቡ የተቀላቀሉት። በተመሳሳይ የነፃነት ትግል ላይ የነበሩ ሚዲያዎችም ማገገሚያ መግባት ያለባቸው ይመስለኛል። መስመራቸውን አስተካክለው፣ ቅኝታቸውን ቀይረው ነው የአገር ውስጥ ሚዲያውን መቀላቀል ያለባቸው።

መንግሥት መሣሪያ በመሆን ይተቹ የነበሩት የዝብ መገናኛ ብዙንስ?

ዶ/ር አብዲሳ ዘርአይ፡ የመንግስት ፕሮፖጋንዳ መሳሪያ በመሆን ይተቹ የነበሩት የመንግስት ሚዲያዎችም ልጓሙ ተነሳላቸው ቢባልም እያንዳንዳቸው የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ ይዘው ወደ ወገናቸውና ወደ ጎጣቸው ነው የሄዱት። በተለይም የክልል ቴሌቭዥኞች በፕሮከፖጋንዳ የተጠመዱ ፤ የሚያናግሯችው ምሁራንም ከአንድ ውሃ የተቀዱ ነው የሚመስሉት።

ዘገባቸው የማህበረሰቦች መስተጋብር ላይ ነውጥ እያነገሰ እንጂ ለአገርና ለማህበረሰብ ጥቅም እየሰራ ነው ብሎ መናገር አይቻልም። እነዚህ ሚዲያዎች ምናልባትም ከነበሩበት ሁሉ የባሰ አደገኛ መስመር ላይ ነው ያሉት። ሚዲያዎቹ በዚሁ ቀጥለው ምርጫ የሚኖር ከሆነ ነገሮች ይበልጥ ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ።

መንግሥት ሚዲያውን ከፈት ሲያደርግ አብሮ የመረጃ ሮችንም ከፍቷል ብለው ያስባሉ?

ዶ/ር አብዲሳ ዘርአይ፡ መረጃ የማግኘት ችግር የባሰበት ነው የሚመስለኝ። በፊት በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት መረጃ ማግኘት ይቻል ነበር። የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ፈርሶ ነገሮች በጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ ሴክሬታሪ ስር ከተጠቃለለ በኋላ ግን አዲሱ ቢሮ በአግባቡ መረጃ ለጋዜጠኞች እንዲደርስ እያደረገ አይመስልም። የሚፃፉ ነገሮች ትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረቱ አለመሆን የሚያሳየውም ይህንኑ ነው። አብዛኛው በስማ በለው እየፃፈ ያለ ነው የሚመስለኝ። ለውጥ ላይ ስላለን ነው ሊባል ይችላል። ነገር ግን ብዙዎች እንደሚሉት እውነት ለውጥ ላይ ነን ወይ? ለውጥም ሽግግርም ላይ ነን ብዬ አላስብም እኔ። ይልቁንም አገሪቷ ባልሰራው አሮጌውና ባልተወለደው አዲሱ ስርዓት መካከል ውዥንብር ውስጥ ነው ያለችው። ሚዲያውም የዚህ ፖለቲካ ነፀብራቅ ነው። በእርግጥ ፖለቲካው ነውጥ ውስጥ እያለ ሚዲያውን ስርዓት አስይዛለሁ ማለትም ከባድ ነው።

የሚዲያ መብዛት ጥሩ ቢሆንም የአገሪቱ የሚዲያ ኢኮኖሚ ቁጥሩን ሊሸከም የሚችል ነው ?

ዶ/ር አብዲሳ ዘርአይ፡ የሚዲያ ኢኮኖሚው ይህን ሁሉ ይዞ መቀጠል የሚችል አይደለም። ከዚህ በፊትም ስንጮኸበት የነበረ ጉዳይ ነው። ሚዲያ ዝምብሎ የሚያብብ ነገር አይደለም። ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል፤ ለመንቀሳቀስ ገቢ ማግኘት አለባቸው። በበዙ ቁጥር ኢኮኖሚው ከሚሸከመው በላይ ስለሚሆኑ ገበያ ውስጥ ለመቆየት ሲታገሉ በተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች እጃቸው የመጠምዘዝ እድሉ ከፍተኛ ይሆናል ፣ የራሳቸው የሆነ አድማጭ ተመልካች ለመፍጠርና ለመያዝ እውነተኛ ጋዜጠኝነት ሳይሆን ነገር ወደ ማራገብ ፣ አንድ የፖለቲካ አቋም ላይ ቸክሎ የመሄድ ነገር ይመጣል።

ይህ ነገር የብሄራዊ ጥቅምን ሁሉ አደጋ ላይ ሊጥል የሚችልበት እድልም ሰፊ ነው።

የማህበረሰቡ የአብሮነት ጉዞ ላይም አደጋ ያመጣል ፤ ሽግግሩንም የማደናቀፍ እድል አለው። አሁንም እያየን ያለነው በዚህ አቅጣጫ የተቃኙ ነገሮች ይመስላሉ።

ነፃነቱ ቁጥጥርም ስርዓትም የሌለው ከመሆኑ የተነሳ እንዲያውም ወደ ሚዲያ ስርዓት አልበኝነት እየሄደ ነው። ነፃነቱም መስመር ሊበጅለት ይገባል። የአገሪቱ ፖለቲካ በብሄር ላይ የተመሰረተና ብዙ አይነት ውስብስብ ችግር ያለበት ከመሆኑ አንፃር ሚዲያው በሚዛናዊነትና በጥንቃቄ ካልሰራ አብሮነትን የማፍረስ የብሄር ግጭትንም የመቀስቀስ እድሉ ሰፊ ነው።

በክልል ቲቪ እና ሬዲዮዎች የሚተላለፉ ነገሮች ሲታዩ በአንድ አገር ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ማእቀፍ ውስጥ ሳይሆን የተለያየ አገር ላይ እንዳሉ ወይም እንደ ራስ ገዝ አስተዳደር እያሰበ ዘገባውን ከክልሉና ከብሄሩ አንፃር የሚሰራ ነው የሚመስለው።

ፖለቲከኞችም የኔ ነው በሚሉትና እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ይዘግባል ለሚሉት ሚዲያ ብቻ ነው ሃሳባቸውን እየገለፁ ያሉት።

የሚዲያ ነፃነቱን ተከትሎ እየመጣ ያለ አደጋም አለ?

ዶ/ር አብዲሳ ዘርአይ፡ ሚዲያው መከፈቱ መልካም ሆኖ ሳለ ነፃነቱ ስርዓት የተበጀለት አለመሆኑ አደጋ አለው። በተለይም አጠቃላይ የፖለቲካ ስርዓቱ የሽግግር ውዥንብር ውስጥ ባለበት በዚህ ጊዜ ሚዲያው በዚሁ ከቀጠለ አገሪቱን ከባድ ነገር ውስጥ ሊከታት ይችላል።

ኢህአዴግ ስልጣን በያዘ ማግስት ሚዲያው እንዳሁኑ ክፍት ተደርጎ ነበር። ሚዲያውን መክፈትና ሰዎች በነፃነት ሃሳባቸውን እንዲገልፁ ማድረግ ከቀድሞ ስርዓት የተሻልኩ ነኝ ያለበት ነበር። ነገር ግን ሚዲያው ሃላፊነት የጎደለው ስለነበር ፣ ስርዓቱ ችግሮችን ለመታገስ ባለመፈለጉ ነፃነቱ አልቀጠለም። አዲስ ስርዓት ሲመጣ ሁሌም ሚዲያን ክፍት ማድረግ የተለመደ ነው።

ነፃነት ከሃላፊነት ጋር የሚመጣ ነገር ካልሆነ በጣም አደገኛ ነው። ነፃነት ከሃላፊነት ውጭ ትርጉም የለውም የሚወስደው ወደ ስርዓት አርበኝነት ነው።

በውጭም በአገር ውስጥ ያሉ ፖከቲከኛው፣ አክቲቪስትና ጋዜጠኛው ሁሉ ግባ ተብሎ ሜዳው እንዴት ነው መስመርና ስርዓት መያዝ ያለበት የሚለው ነገር ላይ የተሰራ ነገር የለም። ስለዚህም በዚህ አንገብጋቢ ሰዓት ሁሉም እንደመሰለው በግራም በቀኝም እየሄደ በዚህ አንድ ዓመት የሚዲያ ነፃነቱ ጠብ ያደረገው ነገር የለም።

ሚዲያው ቁጥጥር ያስፈልገዋል። ነገር ግን መንግሥት ሳይሆን ሚዲያው ራሱን እንዲቆጣር ነው የሚመከረው።አሁን ሚዲያው ራሱን መቆጣጠር የሚችል ይመስልዎታል?

ዶ/ር አብዲሳ ዘርአይ፡ የፖለቲካ ለውጥ ሲመጣ የሚዲያ ነፃነትም ይመጣል። ዋናው ነገር ነፃነቱን ይዞ ለመቀጠል በጣም ሃላፊነት የተሞላበት ጋዜጠኝነትን መገንባት እንደሚያስፈልግ መገንዘብ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ነፃነቱ የአጭር ጊዜ ነው የሚሆነው። ነፃነቱን ሃላፊነት በጎደለው መንገድ ተጠቀማችሁ ብሎ ጫን የሚል ሃይል እንደሚመጣ ማሰብ አስፈላጊ ነው። ሃላፊነትና ተጠያቂነትን ይዞ ነው ሚዲያው ነፃነቱን ማጣጣም ያለበት።

የተቋቋመው ሚዲያ ካውንስልስ ሚዲያው ራሱን እነዲቆጣጠር ሃላፊነቱ መወጣት ይችላል ብለው ያምናሉ?

ዶ/ር አብዲሳ ዘርአይ፡ በሚዲያ ካውንስሉ ምስረታ ላይ ብዙ ሚና ስለነበረኝ ከሚዲያ ባለቤቶቹንና ከሌሎቹም ጋር አብሬ ሰርቻለሁ። አንዳቸው ሌላውን ያለመቀበል ነገር ያላቸው ናቸው። ሚዲያ ካውንስሉ ስርዓት ይዞ በአሁኑ ወቅት ወደ ስራ እንዳይገባ ያደረገው አንዱ የሚዲያ ተቋማትና አመራሮች አንዳቸው ሌላውን ያለመቀበልና ያለመተማመንም ችግር ስላለ ነው። ቀደም ሲል ካውንስሉን መስመር ለማስያዝ ተብሎ በዩኔስኮ ተመድቦ የነበረ በጀት በማን የባንክ ሂሳብ ይግባ በሚለው መስማማት ባለመቻላቸው ለሌላ የአፍሪካ አገር ሄዷል። ከዚህ በመነሳት ስለ ሚዲያ ካውንስሉ ውጤታማነት በሙሉ ልብ የምናገረው ነገር የለም። ነገር ግን ለሚዲያውም ጤንነት የተገኘውንም ነፃነት ዘላቂ ለማድረግ ሚዲያው በሚዲያ ካውንሰሉ አማካኝነት ራሱን እንዲቆጣጠር ነው የምፈልገው።