በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር በተፈጠረ ግጭት ሰዎች ሞቱ

የኢትዮጵያ ካርታ

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ደዌ ሃረዋ ወረዳ በታጠቁ ሃይሎችና የአከባቢው ነዋሪ መካካል ግጭት ተቀስቅሶ የሰው ህይወት መጥፋቱ ተገለፀ።

የወረዳው ነዋሪ የሆኑት አቶ ሞሃመድ ሰይድ ለቢቢሲ እንደገለጹት የጸጥታ ሃይል ነን ብለው የሚንቀሳቀሱና የመለያ ልብስ የሌላቸው የታጠቁ ሰዎች በአካባቢው ሰፍረው ነበር።

"አለባበሳቸው ልክ እንደማንኛውም ሰው ነበር። የመለያ ልብስ ስላልነበራቸው የጸጥታ ሃይል አይመስሉም ። የያዙት ባንዲራም መሃሉ ላይ ኮከብ የሌለው ነው። በዚሁ ሁኔታ ለአንድ ሳምንት ከቆዩ በኋላ የመከላከያ የደንብ ልብስ የሚመስል ነገር እዛው በአካባቢ አሰፍተው ለበሱ።" ይላሉ።

በኋላም በአካባቢው መሳሪያ አንግበው በመንቀሳቀስ ነዋሪዎችን ትጥቅ ማስፈታት ሲጀምሩ ከተደራጁ የአካባቢው ወጣቶች ጋር ተኩስ ልውውጥ መደረጉን የሚናገሩት አቶ ሞሃመድ " የተኩስ ልውውጡ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል።''ይላሉ።

የዞኑ የጸጥታ መምሪያ ሃላፊ የሆኑት አቶ አብዱ ሞሃመድ ግን በአካባቢው የሰፈሩትና ትጥቅ ይዘው የሚንቀሳቀሱት በክልሉ የተሰማሩ ጸጥታ አስከባሪዎች መሆናቸውን ያረጋግጣሉ።

ግጭቱ መፈጠሩንም በማረጋገጥ ነገሮችን ለማረጋጋትም መከላከያ ቦታው ላይ መግባቱን ይናገራሉ ።

ገና ተጨማሪ ማጣራቶችን እያደረጉ ቢሆንም የአምስት ሰዎች ህይወት መጥፋቱም ገልፀዋል ሃላፊው።

አቶ ሞሃመድም በግጭቱ ታጣቂዎችና የበአካባቢው ወጣቶች ስለመገደላቸው ይናገራሉ።

"ከትናንት ማታ 12 ሰአት ጀምሮ የአካባቢው ሽማግሌዎችና የመከላከያ ሰራዊት በመሃል ገብተው ተኩስ አቁም ተደርጓል። እስካሁን ባለኝ መረጃ 10 ታጣቂዎች ሲገደሉ ሁለት ወጣቶች ህይወታቸው አልፏል።''