የሰው ፊት ማስታወስ የማትችለው ሴት

በአንድ ወቅት የከተማ አውቶብስ ውስጥ የማላውቃት ሴት እጇን አውለብልባ ሰላም አለችኝ። የማላውቃት ሴት እንዴት እነደዚህ ሰላም ልትለኝ ቻለች ብዬ አስቤ ነበር በወቅቱ ትላለች ቡ ጄምስ።

የኋላ ኋላ ግን ያቺ አውቶብስ ውስጥ ሰላም ያለቻት ሴት እናቷ ነበረች።

እሷ እንደምትለው የሰዎችን የፊት ገጽታ ማስታወስ እንዳትችል የሚያደርጋት የጤና እክል አለባት። የቤተሰቦቿን፣ የጓደኞቿን፣ ይባስ ብሎ የእራሷንም መልክ ማስታወስ አትችልም። ሁሌም ቢሆን በመስታው አጠገብ ሆና ስትመለከት የምታየው ፊት ለእሷ አዲስ ነው።

በዚህ የጤና እክል ምክንያት ከሌላ ዓለም የመጣችና ከሰዎች የተለየች እንደሆነች ታስብ እንደነበረ ቡ ትናገራለች።

'' ማንም ሰው ሊያስበው ከሚችለው በላይ አስጨናቂና የስሜት መዋዠቅ የሚያስከትል ህመም ነው። በተቻለኝ መጠን ትክረት ላለመስጠት እሞክራለሁ፤ ግን ቀላል አይደለም።''

''ቀኑን ሙሉ ከባድ ጊዜ ነው የማሳልፈው። በመንገድ ላይ የምመለከታቸው ሰዎች ሁሉ የሚያውቁኝ ይሆን፤ ሰላም ማለት ይኖርብኝ ይሆን እያልኩ እጨነቃለሁ። '' ብሏል።

ምንም እንኳን ይህ የጤና እክል 'ፕሮሶፓግኖዚያ' የሚል ሳይንሳዊ ስያሜ ቢኖረውም እሷ ግን አብዛኛውን የእድሜዋን ክፍል እራሷን በመውቀስና የመርሳት ችግር እንዳለባት በማሰብ አሳልፋለች።

"ብዙ ሰዎች ከእኔ ግዴለሽነትና ስንፍና የተነሳ መልካቸውን እንደምረሳ ያስባሉ። እኔም ቢሆን የራሴ ጥፋት እንደሆነ ነበር የማስበው።'' ትላለች።

በእድሜዋ አርባዎቹ ውስጥ ከገባች በኋላ ነበር ቡ ስለ በሽታው የተዘጋጀ ጥንቅር በቴሌቪዥን የተመለከተችው።

'' ልክ ዜናውን ስመለከት የተረዳሁት ነገር የሰዎችን መልክ የምረሳው ከእኔ ግዴለሽነት በመነጨ ሳይሆን አእምሮዬ ይህንን የማድረግ አቅም እንደሌለው ነው።''

ስል ልጅነቷ ስታስታውስ በጣም አስጋሪ እንደነበረ ትገልጻለች። ፊታቸውን የማታስታውሳቸው ህጻናት ጋር አንድ ክፍል ውስጥ መማርና ጓደኝነት መመስረት ምን ያክል ከባድ ሊሆን እንደሚችል ማንም ሊረዳው እንደማይችል ታስባለች። አስተማሪዎቿንም ቢሆን አታውቃቸውም ነበር።

በአሁኑ ሰአት የ51 ዓመት ዕድሜ ላይ ሲሆን የምትገኘው ድንገት ካገኘቻቸው ሰዎች ጋር ውይይት ማካሄድ ይከብዳታል። ምክንያቱም ያንን ግለሰብ ትወቀው አትወቀው እርግጠኛ አይደለችም።

'' በአንድ ወቅት ከእናቴ ጋር ሆነን የድሮ ፍቶዎች ስንመለከት እናቴ በተደጋጋሚ በምስሉ ላይ ስላለች ሴት ታወራልኝ ነበር። ግራ ስለገባኝ ይህች ሴት ማን ነች? ብዬ ጠየቅኳት። አንቺ እኮ ነሽ ስትለኝ በጣም ደነገጥኩኝ።''

ቡ እንደምትለው የሰዎችን አፍንጫ፣ አይን፣ ጆሮ የመሳሰሉ ክፍሎችን ልታስተውል ትችላለች፤ ነገር ግን ሁሉንም አንድ ላይ አድርጋ እንደ አንድ ፊት መመልከት አትችልም።

ምንም እንኳን ይህ የጤና እክል ብዙ ውስንነቶች ቢፈጥሩባትም የራሷ የሆኑ መንገዶችን እንፈጠረች ትናገራለች። ሰዎች ደጋግመው የሚለብሱት የልብስ አይነት፣ ድምጻቸውን፣ ጌጣ ጌጦች፣ የጸጉር አይነትና የሰውነት ቅርጽ የመሳሰሉ ነገሮችን ለማስታወስ እንደምትሞክር ትናገራለች።

የዚህ በሽታ ሌላኛው ተጠቂ የሆነው ሪቻርድ ዋር ደግሞ ማስታወስ የማይለው እምብዛም የማይግባባቸውን ሰዎች ፊት እንደሆነ ይናገራል።

ከዚህ ባለፈ ግን ልክ እንደ ቡ የቤተሰቦቹንና የጓደኞቹን መልክ መለየት እንደማይቸገርና አዲስ ሰዎችን ሲተዋወቅ ጉዳዩን ቶሎ እንደሚያስረዳቸው ይናገራል።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት 'ፕሮሶፓግኖዚያ' የተባለው የሰዎችን የፊት ገጽታ ማስታወስ ያለመቻል ችግር በዋነኛነት በሁለት ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል።

የመጀመሪያው በአደጋ አልያም በተለያዩ ምክንያቶች ጭንቅላታችን ሲጎዳ የሚፈጠረው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በተፈጥሮ ስንወለድ ጀምሮ አንዳንድ የአእምሯችን ክፍሎች በአግባቡ መልእክት መለዋወጥ ሳይችሉ ሲቀሩ የሚከሰት ነው።