ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ናይሮቢ፡ የሟቾች ቁጥር 21 ደርሷል
በናይሮቢው ዱሲት2ናይሮቢ ሆቴል በደረሰው የሽብር ጥቃት የሟቾች ቁጥር 21 መድረሱን መንግሥት ይፋ አድርጓል።
በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው 28 ሰዎች ደግሞ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት በሆስፒታል ይገኛሉ። የኬንያ ቀይ መስቀል ማኅበር እስካሁን ድረስ 19 ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም ብሏል።
የኬንያ ፖሊስ አሸባሪዎቹን ገድሎ ህንጻውን ለመቆጣጠር የ19 ሰዓታት ኦፕሬሽን ማካሄድን ነበረበት። ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፤ ''አሸባሪዎቹ በሙሉ ተገድለዋል፤ ኦፕሬሽኑም ተጠናቋል'' ሲሉ አሳውቀል።
አል ሸባብ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ ማለቱ ይታወሳል።
ሮይተርስ እንደዘገበው፤ አል ሸባብ "ይህን ጥቃት የሰነዘርኩት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ አድርገው በመቁጠራቸው ምላሽ እንዲሆን ነው" ብሏል።
እየሩሳሌም ለእስልምና፣ ለክርስትና እና ለአይሁድ እምነት ቅድስት ስፍራ ተደርጋ ትወሰዳለች። እስራኤል አጠቃላይ የእየሩሳሌም ክፍልን መዲናዋ አድርጋ ትቆጥራለች። ፍልስጤሞች በበኩላቸው ምስራቃዊ እየሩሳሌም ወደፊት እውቅና ለምታገኘው ፍልስጤም መዲና ናት ይላሉ።
ኬንያ እአአ 2011 ላይ አል ሸባብን ለመውጋት እና ለሶማሊያ መንግሥት ድጋፍ ለመስጠት ጦሯን ወደ ሶማሊያ ካዘመተች በኋላ በአል ሸባብ ጥርስ ውስጥ ገብታ ቆይታለች።
ኤኤፍፒ እንደዘገበው፤ ትናንት ከሽብር ጥቃቱ ጋር ግንኙነት ሳይኖራቸው አይቀሩም የተባሉ ሁለት ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል አንዷ ከአሸባሪዎቹ የአንደኛው ሚስት እንደሆነች ሌላኛው ተጠርጣሪ ደግሞ ለጥቃቱ በገንዘብ ድጋፍ ሳያደርግ አይቀርም ሲሉ የኬንያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በሽብር ጥቃቱ የተገደሉት እነማን ናቸው?
የአሜሪካ ዜጋ የሆነው ጄሰን ስፒንድለር ከሟቾቹ መካከል አንዱ ነው። የጄሰን ወንድም የሆነው ጆናተን በትዊተር ገጹ ላይ እንዳስታወቀው ወንድሙ በኒው ዮርክ እአአ 2001 ተፈጽሞ ከነበረውን 9/11 የሽብር ጥቃት በህይወት ተርፎ ነበር።
የእንግሊዝ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቢሮ ከሟቾቹ መካከል ሉክ ፖተር የተሰኘ የእንግሊዝ ዜጋ እንደሚገኝበት አስታወቋል። በተጨማሪም አንድ እንግሊዛዊ በጥቃቱ ጉዳት አጋጥሞታል።
ኬንያዊው እግር ኳስ ተጫዋች ከሟቾቹ መካከል አንዱ ነው። ኮብራ በመባል የሚታወቀው ተጫዋች ለኳስ ባለው ፍቅር በብዙዎች ዘንድ ይታወቃል።
የልብ ወዳጆች የሆኑት ኬንያውያኑ አብደላ ዳሂር እና ፋይሰል አህመድ ከሟቾቹ መካከል ይገኙበታል።
አብደላ እና ፋይሰል በሆቴሉ ምሳ እየተመገቡ ሳለ ነበረ የሽብር ጥቃቱ የተፈጸመው። ሁለቱ ጓደኛሞች "ሁሌም የማይነጣጠሉ" ተብለው በሚያውቋቸው ሰዎች አንደበት ይገለጻሉ።