የጀማል ኻሾግጂ ግድያ፡ የካናዳ የደህንነት መስሪያ ቤት የግድያውን የድምፅ ቅጂ ሰምቶታል

የካናዳ የደህንነት መስሪያ ቤት የሳዑዲ አረቢያውን ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ግድያን የተመለከተ የድምፅ ቅጂ መስማቱን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በሳዑዲ አረቢያ ቆንስላ የተገኘውን የጋዜጠኛውን ግድያ የተመለከተውን የድምፅ ቅጂ መስማታቸውን ይፋ ያደረጉ የመጀመሪያ ምዕራባዊ መሪ ናቸው ተብሏል።

የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጠይብ ኤርዶዋን ባለፈው ቅዳሜ በሰጡት መግለጫ የድምፅ ቅጂውን ለእንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ሳዑዲ አረቢያ መስጠታቸውን ገልፀው ነበር።

ፕሬዚዳንቱ ለአንደኛው የዓለም ጦርነት 100ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ወደ ፈረንሳይ ከመብረራቸው አስቀድሞ "የሰጠናቸው የድምፅ ቅጂውን ነው " ብለዋል።

በፈረንሳይ በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ትሩዶ የአገሪቱ የደህንነት መስሪያ ቤት የጋዜጠኛውን ግድያ ለመመርመር ከቱርክ ጋር በቅርበት እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

"ከሳምንታት በፊት ኤርዶጋን ጋር በስልክ ተነጋግረን ነበር፤ አሁንም ተወያይተናል፤ በእውነቱ ቱርክ የጋዜጠኛውን ግድያ ጉዳይ ለማጣራት ያላትን ቁርጠኝነት አደንቃለሁ" ብለዋል።

የድምፅ ቅጂውን እርሳቸው ባያዳምጡትም የካናዳ የደህንነት መስሪያ ቤትና የስለላ ድርጅት ወደ ቱርክ ተጉዘው ግድያውን በተመለከተ የወጣውን የድምፅ ቅጂ እንደሰሙ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ከዚያም ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ ለሌሎች የአገሪቱ ባለስልጣናት ገለፃ እንዳደረጉ ጨምረው አስረድተዋል።

ማስረጃው ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሊያሻክረው ይችላል ስለመባሉም ዝርዝር መልስ ከመስጠት ቢቆጠቡም ከሳዑዲ አረቢያ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ዙሪያ ውይይት እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የፈረንሳዩ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጀን ይቬስ ሊ ድሪያን የደረሳቸውን የድምፅ ቅጂ በማስመልከት " የቱርክ መሪ የፖለቲካ ጨዋታ" ማለታቸውን ተከትሎ ቱርክ ተቆጥታለች።

"እውነታው አልወጣም፤ ሀቁን እንፈልጋለን፤ ከዚያም አስፈላጊውን እርምጃ እንወስዳለን" ብለዋል ሚንስትሩ ለአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ምላሽ።

ይህን ተከትሎ "የቱርኩ ፕሬዚደንት 'ዋሽተዋል ማለት ነው?" ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄም መንግሥት እየተጫወተ ያለው ፖለቲካዊ ጨዋታ እንደሆነ ለማስረዳት ዙሪያ ጥምጥም ሄደዋል።

የቱርኩ ፕሬዚዳንት የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ በበኩላቸው "ተቀባይነት የሌለው" ሲሉ የሚንስትሩን ንግግር አጣጥለው የፈረንሳይ የደህንነት መስሪያ ቤት ተወካይ የድምፅ ቅጂውን እንዲሰሙ መደረጉን ገልፀዋል።

ኃላፊው "በፈረንሳይ መንግሥት የሚገኙ የተለያዩ መስሪያ ቤቶች የተግባቦት ችግር ካለባቸው ይህ የቱርክ ጉዳይ አይደለም" ሲሉ የአፀፋ መልስ ሰጥተዋል።

አሜሪካ የድምፅ ቅጂው ይድረሳት አይድረሳት ያለችው ነገር የለም ።