ከደሴ ወደ አሰብ የትራንስፖርት አገልግሎት ሊጀመር ነው

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የሁለቱ አገራት ህዝቦች በተለያየ መልኩ የንግድና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ከአዲግራት ወደ ዛላምበሳ አስመራ የአውቶብስ ጉዞ መጀመሩም አንዱ ማሳያ ነው፡፡

ከሰሞኑም ከመስከረም 14፣ 2011 ዓ.ም አንስቶ ከደሴ ከተማ ወደ አሰብ የትራንስፖርት ስምሪት መጀመሩን የሚገልፁ ማስታዋወቂያዎች በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች እየተዘዋወረ ይገኛል፡፡

እውን ጉዞው ተጀምሯል?

አቶ ተፈሪ ኃይሌ በደሴ ከተማ ጥምረት በተሰኘ የአገር አቋራጭ አውቶብሶች ባለንብረት ማህበር ሊቀመንበርና ባለ ሃብት ናቸው፡፡

"ጉዞው አልተጀመረም እያስተዋወቅን ነው፤ ታሪፍና አንዳንድ ሂደቶች ይቀራሉ" ብለዋል፡፡

ስምሪቱ ከደሴ ከተማ አይጀምር እንጂ ከሎጊያ አሰብ ትራንስፖርት መጀመሩንና በቀን እስከ 10 አውቶብሶች ሰዎችን ጭነው ወደ አሰብ እንደሚሄዱ መታዘባቸውን ነግረውናል፡፡

ስምሪቱን የማውጣት ድርሻው የፌደራል መንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን በመሆኑ ለመስሪያ ቤቱ ደብዳቤ ማስገባታቸውን የገለጹልን ሊቀመንበሩ በመጭው ቅዳሜ አሊያም እሁድ ስራ ለመጀመር ተስፋን ሰንቀዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክተን የጠየቅናቸው የደቡብ ወሎ ዞን መንገድ ትራንስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምሴ ተፈራ በበኩላቸው"የሁለቱ አገራት የትራንስፖርት ስምሪት አፈጻጸም መመሪያ በፌደራል ደረጃ ወጥቶ ለኛ የደረሰን ነገር የለም፤ የመንገዱ ታሪፍ ወጥቶ በዚህ መልኩ ስምሪት ስሩ የሚል በሌለበትና በእኛና በፌደራል መካከል የመንገዱ አፈጻጸም ምን ይሁን የሚለው ጉዳይ የጋራ ባለመደረጉ፤ መንገዱ ተፈቅዷል የሚለው ነገር በእኛ በኩል አናውቀውም" ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ምን አልባት በህገ ወጥ መንገድ የሚገቡና የሚወጡ ተሸከርካሪዎች ሊኖሩ ይችሉ ይሆናል ብለዋል፡፡

ወደፊት ወደ አሰብ የሚደረገውን የትራንስፖርት ስምሪት ለማዘጋጀት በዞን ደረጃ ምን እየተሰራ እንደሆነ የጠየቅናቸው ኃላፊው፤ የሰላም ስምምነቱ የቅርብ ጊዜ ክንውን በመሆኑ ዘግይተናል ብለው ባያስቡም፤ ተጠቃሚዎች ካሉ ለሚመለከተው የፌደራል መንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን ጥያቄውን ለማቅረብ ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸውልናል፡፡