በአዲስ አበባ ለሚደረገው ሥነ-ሥርዓት ፖሊስ መዘጋጀቱን አስታወቀ

ፖሊስ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የተከሰተውን ውጥረት ማርገቡንና ነገ በሚካሄደው ሥነ-ሥርዓት ላይም ምንም አይነት የፀጥታ ችግር እንዳይከሰት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።
ኮሚሽነር ጀነራል ዘይኑ ጀማል እንዳሉት በተለያዩ ቦታዎች ላይ አጋጥመው የነበሩ ፍጥጫዎችንና ውጥረቶችን ፖሊስ አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ማርገቡንና ጉዳት እንዳይደርስ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በቡራዩ በኩል ወደ ከተማዋ ለመግባት ጥረት እያደረጉ የነበሩ በርካታ ወጣቶች ወደ ከተማዋ ዘልቀው እንዳይገቡ በፖሊስ በመታገዳቸው ከፍተኛ ውጥረት ተከስቶ ነበር።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ዘይኑ ጀማል ለቢቢሲ እንደተናገሩት ወጣቶቹ ወደ ከተማው እንዳይገቡ እንዳልተከለከሉ ነግር ግን በተጠቀሰው አካባቢ በወጣቶች መካከል ፍጥጫ በመፈጠሩ ፖሊስ በመሃል ገብቶ ለማረጋጋት ጥረት ሲያደርግ እንደነበር ገልፀዋል።
ጨምረውም በፍጥጫው ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ሳይገቡ የቆዩ ሰዎች እንዲገቡ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር ፖሊስ አስፈላጊው ነገር ማድረጉን ተናግረዋል።
ውጥረቱ በቀዳሚነት ተከስቶበት በነበረው ዊንጌት አካባቢ የሚገኙ ሱቆችና ሌሎች ንግድ ቤቶች አሁንም ዝግ ሲሆኑ፤ በዊንጌት፣ በጳውሎስና በመድሃኒዓለም አካባቢዎች ጥቂት የሕዝብ ትራንስፖርት መኪኖች ብቻ ናቸው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት።
ነገ ቅዳሜ የኦነግ አመራር አባላትን ለመቀበል በሚደረገው ሥነ-ሥርዓት ወቅትም ችግርና ግጭት ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት በበርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዘንድ የተፈጠረ ሲሆን ኦፌኮና ሰማያዊ ፓርቲ በጋራ ባወጡት መግለጫ ችግሩ ከቁጥጥር እንዳይወጣ መንግሥት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ዘይኑ ጀማል ግን ፖሊስ ሥነ-ሥርዓቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል። "ችግር ለመፍጠር የሚሞክር ካለ ለመቆጠጠር የሚስችል ተገቢ ዕቅድ አውጥተን ተዘጋጅተናል" ብለዋል።
የፊታችን ቅዳሜ ወደ ሃገር ቤት የሚመለሱትን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮችን ለመቀበል በደጋፊዎቻቸው ከሚደረገው ዝግጅት ጋር በተያያዘ በአንዳንድ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ያጋጠመውን ውጥረትና ግጭት ተከትሎ ስጋት ተከስቷል።
የቢቢሲ ዘጋቢ ውጥረትና ግጭት አጋጥሞባቸው ወደነበሩ አካባቢዎች ተዟዙሮ ተመልክቷል።
ዛሬ ጠዋት ላይ የመረጋጋት ምልክት ሲያሳዩ የነበሩ አካባቢዎች ዛሬ ከሰዓት ላይ እንደገና የግጭት ስጋት እንደሰፈነባቸው ዘጋቢያችን መታዘብ ችሏል። በዚህም ዛሬ ከሰዓት በፒያሳ፣ አዲሱ ገብያ እና ቡራዩ ውጥረት ሰፍኗል።
በአካባቢውም የሚታዩ በርካታ ሰዎች ትራንስፖርት በማጣታቸው ምክንያት በእግራቸው ሲጓዙ ዘጋቢያችን ተመልክቷል።

ጳውሎስ አካባቢ ባሉ አንዳንድ ሕንፃዎች ላይ የኦነግ ሰንደቅ አላማ ተሰቅሎ የሚታይ ሲሆን፤ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ የያዙ በርካታ ወጣቶችን ዘጋቢያችን በተዘዋወረባቸው ቦታዎች ተመልክቷል።
ይህ ቢሆንም ጠዋት ላይ በየትኛውም ቦታ ፍጥጫና ግጭት ሳያጋጥም ቆይቶ እኩለ ቀን ላይ ውጥረቱ በተለያዩ ቦታዎች ላይ አገርሽቷል።
ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው ከቡራዩ የመጡ ግለሰብ በነበረው ግጭትና ውጥረት ሳቢያ ወደመኖሪያቸው የሚወስድ ትራንስፖርት አጥተው መቅረታቸውንና ዛሬም ሊያገኙ እንደማይችሉ ስጋት እንደገባቸው ተናግረዋል።

ዘጋቢያችን በተዘዋወረባቸው አካባቢዎች በሙሉ በርካታ የፖሊስ አባላት ተሰማርተው ተመልክቷል።
ዕሮብ ዕለት ተከስቶ በነበረው ግጭት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉንና ሌሎች ላይ ደግሞ አካላዊ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ ማስታወቁ ይታወሳል።












