የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጉዳት ለማድረስ የሚሞክሩትን እንደማይታገሱ አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Screenshot
ዛሬ ረፋድ ላይ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኙት ሽሮሜዳ፣ አዲሱ ገበያ፣ ሾላ እና እንቁላል ፋብሪካ አካባቢዎች በወጣቶች መካከል መጠነኛ ግጭት እንደረበረ እማኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።
በግጭቱም የቤት እና መኪና መስኮቶች ተሰባብረዋል፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ለተወሰኑ ሰዓታት ተቋርጧል። የፌዴራል ፖሊስ አባላት ግጭቱን ለማስቆም በስፍራው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር እና ይህ ዘገባ በታተመበት ሰዓት ነገሮች እየተረጋጉ እንደሆነ እማኞች ጨምረው ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ግንኙነት ቢሮ ም/ሃላፊ ወ/ሮ ሃይማኖት ዘለቀ በበኩላቸው ለአዲስ ቴሌቭዥን እንደገለፁት ግጭቱን ወደ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ለማሸጋገር ሙከራ መደረጉን ጠቅሰው ተገቢ ያልሆኑ ነገሮች ካሉ መስተካከል ያለባቸው በኃይል እና በፀብ አጫሪነት ሳይሆን በከተማ አስተዳደሩ አማካይነት በህግ አግባብ እንደሆነ ሲናገሩ ተሰምተዋል።
የኦነግ የሥራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት እና ከፍተኛ አመራሮችን ለመቀበል የተቋቋመው ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ኢብሳ ነገዎ ለቢቢሲ እንደተናገሩት እየታየ ያለው «ጠብ አጫሪነት» ሊቆም እንደሚገባ መክረው የቄሮ ወጣቶች በሚታወቁበት ሰላማዊ ትግል እንጂ በንብረት ማውደም እና ጠበኝነት ውስጥ እንዳይሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
«ይሄንን አቀባበል ለማደፍረስ ለሚፈልጉ ኃይሎች መጠቀሚያ ከመሆን ታቀቡ» ሲሉም አሳስበዋል።
በቅዳሜው አቀባበል ከ2ሚሊየን በላይ ሰዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት አስተባበሪው አቀባበሉን ሰላማዊ ለማድረግ ከአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ጋር በቅርበት እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሁኔታዎች እንዲረጋጉ በማሰብ ድርጅታቸው ከግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን መግለጫ እና የሰላም ጥሪ እንዳስተላለፉም አብራርተዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል ዘይኑ ጀማልም ለሀገር ውስጥ የዜና ተቋማት በሰጡት መግለጫ «ማንም ሰው፣ ጉልበተኛ ነኝ ብሎ በህዝብ ላይ፣ በህዝብ እና ሀገር ተቋማት ላይ ጉዳት ሲያደርስ ቁጭ ብለን የምናይበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም» ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
አክለውም የአዲስ አበባ ወጣቶች ማንንም የመከልከል ሃላፊነት እንዳልተሰጣቸው፣ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ጎዳናዎች ወጥተው ከኦሮሚያ ወጣቶች ጋር መጋጨታቸውን ማቆም እንዳለባቸው ተናግረዋል ።
«የአሮሚያ ወጣቶችም በሰላማዊ ሁኔታ ባንዲራቸውን መስቀል ይችላሉ» ያሉት ኮሚሽነር ጄኔራሉ ጎዳናዎች እና የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ግን የህዝቡ የጋራ ንብረት ስለሆኑ የራስን አርማ ቀለም ለመቀባት መሞከር ተገቢ እንዳልሆነ አሳስበዋል።












