ሙገሳ እና ወቀሳ የተፈራረቀባቸው ሳን ሱ ኪ

ዛይድ ቤን ራድ አልሁሴን በበርማ ፖለቲካ ውስጥ ኃያል የሆኑትን ሳን ሱ ኪ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በሀገራቸው ውስጥ በሚኖሩ የሮይንጃ ሙስሊሞች ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት በሚከናወንበት ወቅት ያሳዩትን አቋም «በእጅጉ የሚያስቆጭ» ብለውታል።

«(ሳን ሱኪ)አንዳች ነገር ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ነበሩ» ይላሉ የ75 አመቷን ሳን ሱ ኪን ጥፋት የሚዘረዝሩት አል ሁሴን ምንም ማድረግ ባይቻላቸው እንኳ የጦር ሰራዊቱን አድራጎት በማውገዝ «ከሃላፊነታቸው መልቀቅ ይገባቸው ነበር» ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበርማ ጦር ሰራዊት የተደራጀ ርምጃ በሺዎች የሚቆጠሩ የሮይንጃ ሙስሊም ማህበረሰብ አባላት እንደተገደሉ፤ ከ70ሺ በላይ ደግሞ እንደተፈናቀሉ ከሰሞኑ አስታውቋል።

የሮይንጃ ታጣቂ ቡድኖች ፖሊስ ጣቢያዎችን በመሰሉ መንግስታዊ ተቋማት ላይ ጥቃት ፈፅመው እንደነበረም ተወስቷል።

ሳን ሱ ኪ ከዓመታት በፊት በሰብዓዊ እና ፖለቲካዊ መብት ተሟጋችነታቸው ሰበብ በተደጋጋሚ ለእስር እና እንግልት ተዳርገዋል። በገደል መልክ ሲነሳ ለነበረው አድራጎታቸውም በ1991 እኤአ የኖቤል ሰላም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የቡዲስት ዕምነት አማኞች በሚበዙባት በርማ በሮይንጃ ሙስሊሞች ላይ ጥቃት በሚፈፀምበት ወቅት ግን በለመዱት ሁኔታ ድርጊቱን ከመቃወም ይልቅ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸው ቁጣና ተቃውሞ መዞባቸዋል።

የተሰጣቸውን የኖቤል ሽልማት እንዲነጠቁ የሚጠይቁ ወገኖችም ተበራክተዋል። የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ ግን ሽልማቱን መንጠቅ እንደማይችል አስታውቋል።

ሳን ሱ ኪ በበርማ ህዝብ ዘንድ ተደማጭነት ያላቸው ስለመሆኑ ቢታመንም ወሳኝ የሀገሪቱ መንግስት ስልጣን ግን አሁንም በጦር ሰራዊቱ እጅ ውስጥ መሆኑን የሚያነሱ ወገኖች እሳቸው ሁኔታዎችን ለመለወጥ ያላቸውን ሀቅም ይጠራጠሩታል።