የኡጋንዳ ወታደሮች ጋዜጠኛ በመደብደባቸው ሰራዊቱ ይቅርታ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ባልተለመደ መልኩ ሰራዊቱ ይቅርታ የጠየቀው በእስር ለሚገኘው እውቁ ዘፋኝና ተቃዋሚ ቦቢ ዋይን የተደረገውን የድጋፍ ሰልፍ በመዘገብ ላይ የነበር አንድ ጋዜጠኛ በወታደሮች ሲደበደብ የሚያሳይ ቪዲዮ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ መውጣቱን ተከትሎ ነው።
ሁኔታውን አስመልክቶ ሰራዊቱ ያወጣው የፅሁፍ መግለጫ የወታደሮቹ ተግባር የሙያ ስነምግባርን የጣሰ እንደሆነና ወታደሮቹም እንደሚታሰሩ ይገልፃል።
ባለፈው ሳምንት ተቃዋሚ የፓርላማ አባል የሆነው ቦቢ ዋይንና ሌሎች አራት የፓርላማ አባላት መታሰርን ተከትሎ በኡጋንዳ ውጥረት ነግሷል።
በሙዚቃው እውቅናን ያተረፈው ቦቢ ዋይን እንደ አውሮፓውያኑ ባለፈው ዓመት በግል የፓርላማ አባል ሆኖ ተመረጠ።
ምናልባትም በአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውንና የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ዩዎሪ ሙሴቬኒን በመቃወም የተደረገን የወጣቶች ንቅናቄ የመራ ሰው እንደሆነ የቢቢሲዋ ዘጋቢ ካትሪን ባያሩሃንጋ ትናገራለች።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት የዛሬዋ ኡጋንዳ በርካታ ዜጎች እንደ አውሮፓውያኑ በ1986 ሙሴቬኒ ስልጣን ሲይዙ አልተወለዱም። ይህ ሙሴቬኒ ስልጣን ላይ ረዥም ጊዜ ከቆዩ የአፍሪካ መሪዎች አንዱ መሆናቸውን ያሳያል።
ቀደም ሲል መቀመጫውን ኒውዮርክ ያደረገው ሂውማን ራይትስ ዋች የኡጋንዳ ፖሊስና ወታደር መገናኛ ብዙሃንን ማጥቃት እንዲያቆም እንዲሁም የሰላማዊ ሰልፈኞችን መብት እንዲያከብር ማሳሰቢያ አውጥቶ ነበር።












