አፍሪካዊው ወጣት ለወባ በሽታ መፍትሄ ይዞ መጥቷል

"ይህ ፕሮጀክት የተጀመረው እንደ ቀልድ ነበር። ጓደኛሞች በጋራ ሰብሰብ ብለን የሆነ የሚያስደስት ነገር መስራት ፈለግን።" ይላል የ26 ዓመቱ ብሪየን ጊታ።
''ከአመት በኋላ ጓደኞቼን 'መልካም ጊዜ እያሳለፍን ነው። እየተዝናናን ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለንም የሰዎችን ህይወት መቀየር እንችላለን' አልኳቸው''። ይላል።
ብሪየን የወባ በሽታ መመርመሪያ መሳሪያ ግኝቱን አስመልክቶ ከሮያል አካዳሚ ኦፍ ኢንጅነሪንግ አፍሪካ ሽልማት ከመቀበሉ ሳምንታት በፊት ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርጎ ነበር።
ከአራት ዓመት በፊት ብሬን ከማከሬሬ ዩንቨርስቲ ጓደኞቹ ጋር በመሆን የደም ናሙና መውሰድ ሳያስፈልግ በፍጥነት የወባ በሽታን የሚመረምረውን ''ማቲባቡ'' ሲሉ የሰየሙትን በአነስተኛ ዋጋ እና መልሶ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችለውን የፈጠራ ውጤት እንካችሁ አሉ።
ምንም እንኳ ይህ ግኝት በሙከራ ደረጃ ላይ ያለ ቢሆንም ዳኞች ግን የወባ በሽታ መመርመሪያ መሳሪያውን ገዳዩን በሽታ በመዋጋት ሂደት ውስጥ በቀላሉ ታሪክ ቀያሪ ብለውታል።
ማግኔቶች እና ማቲስኮፕ
ማቲባቡ ማለት በስዋሂሊ ቋንቋ ''ህክምና'' ማለት ሲሆን፤ ማግኔት እና ማቲስኮፕ የተሰኘ ተንቀሳቃሽ መሳሪያን ይጠቀማል።
መሳሪያው ቀይ የብርሃን ሞገድ የተጠቃሚው እጣት ላይ የሚያበራ ሲሆን የወባ ጥገኛ የሆነ ሄሞዞን ክርስቲያልስ የተሰኘ ንጥረ ነገርን ይለያል።
ፈጣሪዎቹ ማቲባቡ የደም ናሙና መውሰድን የማይጠይቅ በመሆኑ የምርመራ ጊዜን ከማሳጠሩም በተጨማሪ ህጻናት የሚፈሩትን መርፌ መወጋት ስለሚያስቀር ሁኔታውን ወደላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ያመናሉ።

በዩጋንዳ ባለፈው ዓመት በበሽታው የሞቱትን 5100 ሰዎች ጨምሮ 9.5 ሚሊዮን ሰዎች በወባ በሽታ ተጠቅተዋል። ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ ህጻናት ናቸው።
"ልጄ በድንገት ማንቀጥቀጥ ጀመረው፤ ምግብም መብላት አቆመ። ደህና ይጫወት ነበር። ትምህርት ቤትም ይሄድ ነበር። ወዲያው ግን ታመመ።" ትላለች አቻን ናይቲ በሰሜን ዩጋንዳ በሚገኘው ኪጉሙ ሆስፒታል ውስጥ የስድስት ዓመት ልጇ ከተኛበት አልጋ ጎን ተቀምጣ።
"የምንኖረው ከክሊኒኩ በጣም ሩቅ በሆነች ትንሽዬ የእርሻ ቦታ ላይ ነው። ሌሎች ሶስት ትንንሽ ልጆቼን መንከባከብ አለብኝ። ገንዘብም የለኝም። እዚህ ለመምጣት ሶስት ቀን ፈጅቶብኛል። በመዘግየቴ ልጄ ተጎድቶ እንዳይሆን ሰል እፀልያለሁ።" ትላለች።

ብሪየን መጀመሪያ ይሄን የፈጠራ ሀሳብ ያመጣው በወባ እና ታይፎይድ በሽታ በተመሳሳይ ጊዜ በታመመበት ወቅት ነበር።
በሆስፒታል አልጋ ላይ ሳለም፤ መርፌ የማይፈልግ ፈጣን እና ህመም የለሽ ተንቀሳቃሽ የመመርመሪያ መሳሪያን አሰበ።
በምህንድስና፣ በኮምፒውተር ሳይንስ እና ተላላፊ በሽታዎች ክህሎት ካላቸው ምሩቆች ጋር ተጣመረ።
ማይከሮስኮፕ የወባ በሽታን ለመመርመር 30 ደቂቃ ወይም ከዚያ በላይ ይፈልጋል። በተቃራኒ የመጨረሻው የማቲባቡ ስሪት ግን ሁለት ደቂቃዎች ብቻ በቂ ናቸው።
ራፒድ ዳይግኖስቲክ ቴስትስ የተሰኘው ሌላው እና በአሁኑ ወቅት ተቀባይነት ያለው የናሙና መውሰጃ ዘዴ እስከ 15 ደቂቃ የሚወስድ ሲሆን የደም ናሙና ያስፈልገዋል። ነገር ግን የጥገኛ ትሎችን ብዛት ማሳየት ስለማይችል ከልክ ሊያሳልፍው ይችላል።
ማቲባቡ ምንም የደም ናሙና ስለማይፈልግ የተለየ ባለሙያ አያስፈልገውም ። በመሆኑም የማህበረሰብ አባላቱ በራሳቸው ሊያከናውኑት ይችላሉ።
የሀብት ምንጭ እጥረት
በተጨማሪም ማቲባቡ ከስማርት ስልክ ጋር የተገናኘ ነው። ይህም ማለት መረጃ ለመሰብሰብ እና የጤና ቡድኖች የወባ ወረርሽኝ በሚኖርበት ጊዜ ጥቆማ ለመስጠት ያስችላል።
"በርካታ ሰዎች የሚኖሩት በገጠር አካባቢዎች ሲሆን መንገዶችም አስቸጋሪ ናቸው። በመሆኑም ወደጤና አገልግሎቶች ለመድረስ ይቸገራሉ።" ይላሉ የኪትጉም ሆስፒታል ዳይሬክተር ዶ/ር ጎፍሬይ አኬና።
"ይህንን ችግር ለመፍታት ጥረት ለማድረግም በአካባቢው ሰዎችን የሚያክሙ የጤና ቡድኖችን አሰማርተናል። ነገር ግን መረጃ ስለሌለን እየተንቀሳቀሱ ያሉት በጭፍን ነው።"

እንደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከሆነ፤ በመላው ዩጋንዳ በየዓመቱ ወደ ተባባሰ በሽታ የሚሸጋገሩ 1.5 ሚሊዮን ከባድ የወባ በሽታ ጉዳቶች ይከሰታሉ። ይህም ማለት በሽታው የተደረሰበት ዘግይቶ ነው ማለት ነው። የወባ በሽታ በ24 ሰዓት ውስጥ ህክምና ከተደረገ በጣም በፍጥነት እና በተሰካ ሁኔታ ሊታከም ይችላል።
ለአገልግሎት ዝግጁ የሆነው እና በፍጥነት ለሚፈልጉት የሚደርሰው ማቲባቡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት እና የተረጋገጠ ህክምናን ለማግኘት ያግዛል።
ታሪክ ቀያሪ ግኝት?
ነገር ግን ሁሉም ነገር ግልጽ ነው ማለት አይደለም። የአሁኑ ማቲባቡ መሳሪያ መፈለግ የሚችለው 80 በመቶው ያህሉን የወባ በሽታ ጉዳቶችን ነው፡፡ ይህም ብራየንም እንደሚያውቀው በአለም አቀፍ ተቀባይነት ካለው የ99 በመቶው አሰራር በእጅጉ የራቀ ነው።
"የእኛ መሳሪያ ከበፊቶቹ ስሪቶች ጋር ሲነጻጸር የገዘፈ ነው። ከግለሰብ ኮምፒዩተር ጋር የተገናኘ ነው። እናም ብርሃኑ የደም ናሙናው ላይ ስለሚያንጸባርቅ ጣትህን ወደ ውስጥ መክተት አትችልም። ነገር ግን አሁን የእኛ ትኩረት በ300 ህሙማን ላይ የምናደርገው ቀጣይ የቤተሙከራ ምርመራዎች እና መሳሪያውን ፍጹም ማድረግ ላይ ነው። ዲዛይኑን በኋላ እናሻሽለዋለን።" ሲል ብሪየን ይናገራል። ለዶክተሮቹ ገለጻ ከሚያደርግባቸው በርካታ ክሊኒኮች አንዱ በሆነው እና ከካምፓላ ወጣ ብሎ በሚገኘው ክሊኒክ ውጪ ላይ ትንሽ ሻንጣ የምታክለውን መሳሪያውን ይዞ እንደቆመ።
ተግዳሮቶቹ እንዳሉ ሆነው ብራየን አሁንም ማቲባቡ እንደሚሰራ እርግጠኛ ነው። ለወደፊቱ መሳሪያው የደም ማነስን ለመሳሰሉ ሌሎች በሽታዎች መመርመሪያ እንደሚሆን ተስፋ በማድረግ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ገበያውን ለመያዝ 600 መቶ ሺህ ዶላር እየፈለገ ነው።
የወባ በሽታ በየዓመቱ ግማሽ ሚሊዮን ያህል ሰዎችን እንደሚገድልና ከእነዚህም የሚበዙት ከሰሃራ በታች የሚገኙ ትናንሽ ልጆች መሆናቸው ሲታሰብ አደጋው ከብራየን የስራ ህይወት እና መልካም ስምም በላይ ነው።
ይህ የቢቢሲ ተከታታይ ክፍል የተዘጋጀው ከቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ነው።












