የዙማ የሙስና ክስ፡ በደቡብ አፍሪካ የሙስና መረብ የሚያጋልጥ ምርመራ ተጀመረ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚደንትን የሙስና ቅሌት የሚያጋልጥ ምርመራ ተጀመረ።
ምርመራው 'ስቴት ካፕቸር' የተሰኘውንና በጉብታ ቤተሰብ ህንዳውያን ቱጃሮችና ከፍተኛ የአገሪቱ ሚንስትሮች በአገሪቱ የፖለቲካ ውሳኔ ላይ ያሳደሩትን ጫና ይመለከታል።
ይሄው ጉቦ የመቀበል ክሱ የጀመረው በየካቲት ወር ዙማ ከስልጣን እንዲወርዱ ከመደረጋቸው አስቀድሞ ቢሆንም ፕሬዚዳንቱም ሆኑ የጉብታ ቤተሰቦች አይኔን ግንባር ያድርገው ሲሉ ቆይተዋል።
የምርመራው ስራ መጀመሩን ተከትሎ የፍትህ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ሬይ ዞንዶ ደቡብ አፍሪካውያን የሚያውቁትን ሁሉ ማስረጃ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል።
"ሁላችንም አገራችንን የምንወድ ደቡብ አፍሪካውያን ሁሉ፤ ይህን ችግር ለመፍታት ኮሚሽኑን በትጋት ማገዝ አለብን" በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል።
'ስቴት ካፕቸር' ምንድን ነው
'ስቴት ካፕቸር' ማለት የሙስና መረብ ሲሆን ቱጃሮች በመንግሥት አስተዳደር ስር የሚገኙ ትላልቅ ኩባንያዎች ኮንትራት ለማሸነፍ ሲሉ ለባለስልጣናት የሚሰጡት ጉቦ ነው።
ባለፈው ታህሳስ ወር በዚሁ የሙስና መረብ የተጠመዱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት የሙስና ቅሌት ማስረጃ ተገኝቶባቸው ነበር።
ማስረጃው በአገሪቱ የሚገኙ የጉብታ ቤተሰብ አባላት ዙማ የሚንስትር ሹመት ሲያካሄዱ ተፅዕኖ ማሳደሩን ተመልክቷል።
አንደኛው ክስ ምክትል የገንዘብ ሚንስትር 1.2 ሚሊየን ብር ከጉብታ ቤተሰብ አባላት በአንዱ ተሰጥቷቸው እንደነበር የሚያሳይ ነው
የጉብታ ቤተሰቦች በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ ምንም ማለት እንደማይችሉና በሚዲያ እየጠፋ ያለ ስማቸውን ለማደስ በሂደት ላይ እንደሆኑ ባለፈው ዓመት አስታውቀዋል።












