የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ በረራ እንደሚጀምር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ከኤርትራ ልዑካን ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ ነው።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ ዝግጅት የሚደረገው አንድ ላይ አስመራና አዲስአበባ ላይ በመሆኑ፤ ለሁለቱም ሀገራት አርቲስቶችም ዝግጅቱን ለማድመቅ ተዘጋጁ ብለዋል።
"ምፅዋ ላይ መዝናናት የናፈቃችሁ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራራ በረራ ስለሚጀምር ተዘጋጁ" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስለኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች እየተናገሩ በነበረበት ወቅትም በ'ሶሰት ማእዘን' ፊልም ላይ በደራሲነት መሳተፋቸውን ገልፀዋል።
ለሌላኛው የፊልሙ ፀሐፊ ቴዎድሮስ ተሾመም ይህን በምስጢር እንዲይዘው ነግረውት የነበረ ቢሆንም ዛሬ ራሳቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ማድረጋቸውን ጨምረው ተናግረዋል።
በእራት ግብዣው ላይ ድምፃዊ መሀሙድ አህመድ ሰላም የተሰኘውን ዜማውን በማቀንቀን የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ልዑካንን እጅ ለእጅ አያይዟል።








