ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ ከዓለም ጥቂት አጫሾች ያሉባት አገር ናት
ትምባሆ ማጤስ በማቆም ፈረንሳዊያንን የሚያህል አልተገኘም። በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ አንድ ሚሊዮን ዜጎች የትምባሆን ነገር በቃን ብለዋል። ይህም ከ2016 እስከ 2017 ብቻ የሆነ ነው።
በርካታ አገራት የትምባሆ ስርጭትን ለመግታት ፖሊሲያቸውን ከልሰዋል። ያም ሆኖ በዓለም ላይ የአጫሾች ቁጥር ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይታይም።
ዛሬ የዓለም ትምባሆ ያለማጤስ ቀን ከመሆኑ ጋር አስታከን የአጫሽ አገራትን ዝርዝር አቅርበናል።
1. ኪሪባቲ
ኪሪባቲ የምትባል የማዕከላዊ ፓሲፊክ ደሴት በአጫሾች ቁጥር በዓለም ቀዳሚዋ ናት። ከሕዝቧ ሁለት ሦስተኛ ወንዶች ትምባሆ የሚያጤስ ነው። ከሴቶች ደግሞ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ደግሞ አጫሾች ናቸው።
በዚህች አገር 103,000 ሕዝብ ይኖራል። በትምባሆ ላይ የተጣለው ግብር አነስተኛ ሲሆን ሕዝቡ በቀላሉ በየትም ቦታ ትምባሆን ማግኘት ይችላል።
2. ሞንቴኔግሮ
ምሥራቅ አውሮፓዊቷ አገር ሞንቴኔግሮ ከአውሮፓ በአጫሽ ቁጥር የሚያህላት የለም። 46 በመቶ ሕዝቧ ሱሰኛ ሆኗል።
የባልካኗ ሞንቴኔግሮ የሕዝብ ቁጥሯ 633,000 የሚጠጋ ሲሆን 4,124 ሲጋራዎች በየቀኑ በአዋቂዎች ይጨሳሉ።
ምንም እንኳ በአደባባይና ሕዝብ በተሰበሰበባቸው ቦታዎች ማጤስ በአገሪቱ ሕግ የተከለከለ ቢሆንም ሕዝቦቿ ግን በቢሮዎች፣ በምግብ ቤቶች፣ ብሎም በሕዝብ መጓጓዣ ውስጥ እንደልብ ትምባሆን ይምጋሉ።
3. ግሪክ
ግሪክ 3ኛው ከፍተኛ የአጫሽ ቁጥር እድገት ያስመዘገበች አገር ናት። ከወንድ ዜጎቿ ግማሹ ትምባሆን ከአፋቸው አይነጥሉም። የሚገርመው 35 በመቶ የሚሆኑ ግሪካዊያን ሴቶችም ቢሆን ማጤስን ማዘውተራቸው ነው።
ምንም እንኳ ከ2008 ጀምሮ በሕዝብ አደባባዮች ሲጃራ ማቡነን በሕግ የተከለከለ ቢሆንም ሕጉ ትዝ የሚለው አጫሽ ግን የለም። ብዙ ግሪካዊያን ዛሬም በየአደባባዩ ትምባሆን ያምቦለቡላሉ።
ከግሪክ ቀጥሎ ኢስቲሞርና ራሺያ በርካታ አጫሾች ያሉባቸው አገራት ናቸው።
ራሺያ
ራሺያ በዓለም አጫሾች ዝርዝር አምስተኛዋ አገር ናት። 60 ከመቶ የሚሆኑ ለአቅመ ማጤስ የደረሱ ወንድ ዜጎቿ ትምባሆ አይለያቸውም። የሴቶች ድርሻ 23 ከመቶ ነው።
ሥራ ቦታና የሕዝብ መጓጓዣዎች ላይ ማጤስ ክልክል ቢሆንም የማያቋርጥ የሲጃራ ማስታወቂያዎች መበራከታቸው የአጫሾችን ቁጥር ሳያሳድገው አልቀረም።
በአንዳንድ የራሺያ ሱቆች ፓኮ ሲጋራ ከአንድ ዶላር በታች ይገኛል። የራሺያ የትምባሆ ገበያ 22 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ይገመታል።
ጥቂት አጫሾች የሚገኙባቸው አገራት
እንደመታደል ሆኖ ከነዚህ አገራት ውስጥ ኢትዯጵያ አንዷ ሆናለች። ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ጎረቤት ኤርትራና ፓናማም በዝርዝሩ ይገኙበታል።
ከአፍሪካዊያን 14 ከመቶዎቹ አጫሾች ሲሆኑ የወንዶች ድርሻ እስከ 80 ከመቶ ይደርሳል። የሴቶች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑ የኢኮኖሚ ጥገኛ ከመሆናቸው ጋር ይያያዛል ተብሏል።
የሴቶች ሲጃራ ማጤስ እንደ ማኅበረሰብ ነውር መታየቱ የአፍሪካ ሴት አጫሾችን ቁጥር ሳይቀንሰው አልቀረም።
ከሲጃራ ይልቅ ጫት በአፍሪካ ቀንድ ተወዳጅ እየሆነ መምጣቱ የትምባሆ ወዳጆች ቁጥር በቃሚዎች ሳይተካ አልቀረም። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው በዓለም 10 ሚሊዮን የሚሆኑ ሕዝቦች ጫት ይቅማሉ።
ሴት አጫሾች
ዴንማርክ በሴት አጫሾች ቁጥር የሚስተካከላት የለም። በዚያች አገር ትምባሆን በመማግ ከወንዶች ይልቅ የሴቶች ቁጥር ይበልጣሉ። 19.3 ከመቶ የሚሆኑ ዴንማርካዊያን ሴቶች ትምባሆን የሙጥኝ ብለዋል።
በየዓመቱ ትምባሆ 7 ሚሊዮን የዓለም ዜጎችን ይገድላል።