ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማንበብ ስፓ ከመግባት ይሻላል?
ስለ ዮጋና ስፓ የእረፍት ቦታዎች ሰምተን እናውቅ ይሆናል በተጨማሪም ለሥነ-ጽሑፍና ለሥዕል ተብለው የተዘጋጁም አሉ። ለንባብ ብቻ ተብሎ የተዘጋጀ የእረፍት ቦታስ?
ኤማ ጄን መጽሐፍቶቻቸውን ይዘው እረፍት የወጡ ሰዎችን ለማግኘት ወደዚህ የእረፍት ቦታ አምርታ ነበር።
ክሬሲዳ ዳውኒንግ እራት ለአምስት ደቂቃ መተላለፉን አሳወቀች። እሱም አኒ የጀመረችውን ምዕራፍ እስክትጨርስ ነው በማለት መብራሪያ ሰጠች።
ቢሆንም ግን ማንም ልብ ያለ አልነበረም።
ሔለንና ኒንክ ስለሚያነቡት መጽሐፍ የአጻጻፍ ዘይቤ እየተነጋገሩ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ኒና እና ፔኒ 'ማዳም ቦቫሪ' የተሰኘው መጽሐፍ ልጅነታቸውን ምን ኣህል እንደቀየረው እየተወያዩ ነው። ሮቢ ግን የጀመረውን መጽሐፍ ማስቀመጥ አቅቶት እራት በመኝታ ቤቱ እንዲቀርብለት ጠይቋል።
የንባብ የእረፍት ቆይታ ይህን ይመስላል። የሚመጡት እንግዶች ለሦስት ሌሊት እስከ 450 ፓውንድ ከፍለው እራሳቸውን በመኝታ ቤት ዘግተው ሳይረበሹ በሰላም የሚያነቡበት ቦታ ነው።
'ለእራሴ መብት እየሰጠሁት ነው'
በትርፍ ጊዜዋ አርታዒ የሆነችው ክሬሲዳ የዚህ የንባብ እረፍትን ከመሰረቱት መካከል ናት እሷም ''ሃሳቡ የመጣልኝ በጣም ከባድ ወቅት ላይ በነበርኩበት ጊዜ ባለቤቴ 'ለምን ስፓ አትሄጅም' ሲለኝ ነበር። ስፓ ብሄድ ደስ እንእደሚለኝ ግን መጽሐፎቼን ይዤ ብሄድ ግን እንደሚረጥቡብኝ አስቤ ነው'' ትላለች።
''በጣም አስፈልጎኝ የነበረው ያለ ረብሻ ማንበብ ነበር። ግን ለንባብ ተብሎ የተዘጋጀ ቦታ ማግኘት ሲያቅተኝ የንባብ እረፍት ፈላጊ ብቸኛዋ ሰው ልሆን አልችልም ብዬ አስብኩ።''
ስለዚህ ሣራ ኖኤል ከተሰኘችው በሙያዋ ፎቶግራፈር ከሆነችው የሥራ አጋሯ ጋር በመሆን ጊዜያዊ የሆነ የንባብ ብቻ እረፍት ቦታ አቋቋመች።
ይህ የንባብ እረፍት ቦታ ከከተማ ራቅ ያለ ሲሆን፤ በዚያም አንድ ሕግ ብቻ ነው ያለው እሱም የንባብ ክፍል ውስጥ በማንኛውም ሰዓት ፀጥታ መጠበቅ ብቻ ነው።
አኒ የተሰኘችው እንግዳ የዩኒቨርስቲ የቅሬታ ክፍል ኃላፊ ስትሆን በንባብ እረፍት ላይ ስትሳተፍ ይህ የሁለተኛ ጊዜዋ ነው። ኤማ ጄን፤ አኒ ቤቷን ዘግታ ብታነብ ገንዘብ ታተርፍ እንደነበር ስትነግራት ከት ብላ ሳቀች።
''ይሄ እኮ ለንባብ ቅድሚያ መስጠት እንድችል ለእራሴ እየፈቀድኩኝ ነው'' ብላ በመቀጠልም '' ቤት ብሆን ኖሮ ሌሎች ስለሚሠሩ ነገሮች ማሰቤ አይቀርም። ጓደኞቼን ማግኘት፣ መጻፍ፣ ማፅዳትና ሸራብ መሥራት'' አለችኝ።
''እዚህ ግን እሳቱ አጠገብ ቁጭ ብዬ ለሰዓታት ያለምንም ረብሻ መጽሐፌ ውስጥ መጥፋት እችላለሁ።''
ለአኒ ክሬሲዳ ናት የምታነባቸውን መጽሐፍት ሃሳብ ያቀረበችላት እንግዶች ግን የፈለጉትን መርጠው ማንበብ ይችላሉ።
ከዲጂታል መፅዳት
ጊዜ እያጠረ በመጣበት ዓለም ውስጥ ለንባብ ብቻ ተብለው የሚዘጋጁ የእረፍት ቦታዎች በቁጥር እየበዙ መጥተዋል። የተለያዩ ድርጅቶችም የተለያዩ የኪስ አቅምን ያገናዘቡ አቅርቦቶች ማሰናዳት ጀምረዋል።
አንዳንድ የንባብ እርፍት ቦታዎች ለጥሞናም አመቺ ናቸው። አንዳንዶቹ ቤተ-መንግሥት የሚመስሉ ቦታዎች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ የምንኩስና ሕይወትን የሚያስታውሱ ራቅ ያሉ ቦታዎች ናቸው።
ሁሉም ግን ዓላማቸው አንድ ነው። አንባቢያን በሕዝብ ማመላለሻ ላይ ለ20 ደቂቃ ብቻና በሚያገኙት አጋጣሚ ከሚያነቡ፤ ሙሉ ሃሳባቸውን ሰብስበውና ጊዜ ሰጥተው እንደፈለጉ ማንበብ እንዲችሉ ነው።
ሔለን የሥነ-ልቦና ባለሙያ ስትሆን አጋታ ክሪስቲ የተሰኘችውን ደራሲ በጣም ስለምትወዳት የሌሊት ልብሷን ሳትቀይር ሙቅ ውሃ ታቅፋ በመጽሐፏ ውስጥ ሰምጣለች።
እዚህ ስትመጣ በመኝታ ቤቷ ተቆልፋ የምትውል መስሏት ነበር። ሆኖም ግን ከሌሎች አንባብያን ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ በፀጥታ ማንበቡን ወዳዋለች።
''ይህ የሳምንት መጨረሻ የቅንጦት ነው'' ብላ በሳቅ ፈነደቀች። በመቀጠልም ''ሆቴል ውስጥ ቢሆን ደስ አይለኝም ነበር። ምክንያቱም ብቸኝነት የሚሰማኝ ይመስለኛል። እዚህ ግን ስፈልግ ፀጥታ ስፈልግ ደግሞ እራት እየበላን ስለተለያዩ መጽሐፍት መወያየት እንችላለን'' ትላለች ሔለን።
እ.አ.አ በ2014 የተደረገ የመንግሥት ጥናት እንደመዘገበው 41% የሚሆኑ ከ25 እስከ 39 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ በውዴታ የሚያነቡት ሰዎች ቁጥር እንደቀነሰ ይናገራሉ። ባለፈው ዓመት ውስጥም በእንግሊዝ ሃገር ካሉ ሰዎች መካከል እሩብ የሚያክሉት መጽሐፍ በውዴታ እንዳላነበቡ ተጠቅሷል።
ሱዛን ሂል እና ሃዋርድ ጃኮብሰን የተሰኙት ታዋቂ ደራስያን እንዳስጠነቀቁት እየበዛ የመጣው የዲጂታል ሱስ ያለንን የትኩረት አቅም እየቀነሰ በመሄዱ ረዘም ያሉ ጽሑፎችን የማንበብ አቅማችንን እየቀነሰ ነው።
በዚህ የንባብ እረፍት ላይ ስልኮችና ታብሌቶች ባይከለከሉም እንኳን፤ ክሬሲዳና ሣራ እንግዶቻቸው ከረብሻ ነፃ እንዲሆኑ ወስደው አንዲቆልፉበት ያበረታታሉ። አንባቢያኑም አይናቸው ችግር እንዳይገጥመው በየተወሰነ ጊዜ ወጣ እያሉ ነፋስ እንዲቀበሉም ይበረታታሉ።
'ከስፓ የተሻለ'
የሮቢ ባለቤት ይህን የንባብ እረፍት ለገና ነበር እንደ ስጦታ ያበረከተችለት። እሱም ሁሌም ማንበብ የሚመኛቸውን መጽሐፍት አምጥቶ በእራስጌው ደርድሯቸዋል።
''ቤት ስሆን ተዘግቼ ባነብ ቤተሰቤን ትቼ ለእራሴ ብቻ የማስብ ያህል ነው የሚሰማኝ። እዚህ የተለየ አስተሳሰብ ነው፤ ምክንያቱም እየከፈልኩበትም ነው። ከሰው ጋር የመገናኘት ግዴታም የለብኝም''
እንደውም ገበታ ላይ እራሱ ማንበብ ይቻላል።
''ለምን አይቻልም'' ትላለች ክሬሲዳ። ''ዋናው ነጥብ እኮ ማንም ከጓደኛውና ከሥራ ባልደረባው ጋር ስለማይመጣ 'ይቅርታ ባነብ ቅር አይላችሁም አይደል' ማለት አያስፈልግም። እዚህ ምን ጊዜም የማንበብ ፈቃድ አለን።''
እራት ቀርቦም ገበታ ላይ ውይይቱ ባንድ ጊዜ ተቋረጠና ከቀረቡት ጣፋጮች መካከል የትኛውን እንደሚወስዱ መነጋገር ጀመሩ። አኒ ስለ ንብ ጀምራ ነበረውን መጽሐፍ ለመጨረስ ሹልክ ብላ ወጣች። ሔለንና ሣራ ከአጋታ ክሪስቲ መጽሐፍት መካከል የትኛው እንደሚበልጥ ይከራከራሉ።
ቀጥላም ''ንባብ እኮ በደመነፍስ የሚደረግ አይደልም። ንባብ ተሳትፎና ከመጽሐፉም ጋር መቆራኘትን ይጠይቃል። ደግሞ ሳይንቲስቶች እንደደረሱበት ንባብ ለአዕምሮና ለዕድሜ ርዝመትም አስተዋጽዖ ያደርጋል ስለዚህ ከስፓ የተሻለ የእረፍት ጊዜ ነው።''
በማግስቱም ለቁርስ የወረደችው የቢቢሲዋ ኤማ ጄን ብቻ ነበረች። ሌሎቹ በጠቅላላ መጽሐፍ ውስጥ ተደብቀው ነበር።