አውስትራሊያዊው ተፅዕኖ ፈጣሪ ቤተሰብ የማኅበራዊ ሚዲያ እገዳን ሽሽት ዩናይትድ ኪንግደም ገባ

የፎቶው ባለመብት, YouTube Empire Family
በይነ መረብ ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አድናቂዎች ያሏቸው አውስትራሊያውያን የቤተሰብ አባላት በአገራቸው የተጣለውን የማኅበራዊ ሚዲያ እገዳ ሽሽት ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ገቡ።
ቤተሰቡ መኖሪያውን በዩኬ ለማድረግ የወሰነው ከመጪው ታኅሣሥ ጀምሮ ተግባራዊ በሚሆነው እና ከ16 ዓመት በታች በሆኑ ታዳጊዎች ላይ በተጣለው የማኅበራዊ ሚዲያ እገዳ ምክንያት ነው።
"ኢምፓየር ፋሚሊ" የሚል መጠሪያ ያለው ቤተሰቡ አራት አባላት ያሉት ሲሆን፣ ቤክ እና ቤክ ሊ በተባሉ እናቶች፣ በ17 ዓመቱ ወንድ ልጅ ፕሪስሊይ እና በ14 ዓመቷ ሴት ልጅ ሻርለት የተፈጠረ ነው።
የቤተሰብ አባላቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያጋሩት የቀን ውሏቸውን ነው።
ቤተሰቡ ኢንተርኔትን ለበጎ ዓላማ እንደሚጠቀምበት በመጥቀስ አባላቱ በዩኬ ኑሯቸውን ለማድረግ ያሳለፉት ውሳኔ ልጃቸው ይዘቶችን እንድትፈጥር እንደሚያስችላት በማኅበራዊ ሚዲያ ባጋራው ጽሑፍ ገልጿል።
በዓለም የመጀመሪያው ነው በተባለው የአውስትራሊያ እገዳ መሠረት ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ስናፕቻት፣ ቲክቶክ፣ ኤክስ እና ዩቲዩብ ከ16 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎች አካውንት እንዳይከፍቱ መጠበቅ እና ከዚህ ቀደም የተከፈቱትንም የማጥፋት "ምክንያታዊ እርምጃ" መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።
እገዳው የተጣለው ታዳጊዎችን ማኅበራዊ ሚዲያ ከሚያስከትለው ጎጂ ተፅዕኖ ለመጠበቅ ሲሆን፣ ይህንን ሕግ ያላከበሩ የቴክኖሎጂ ካምፓኒዎች 32.5 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ቅጣት ይጣልባቸዋል።
ሕጉ እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን ግልጽ ባይሆንም መታወቂያን፣ የወላጆችን ፈቃድ እና የፊት መለያ ቴክኖሎጂን፣ ግላዊ መረጃን እና የዕድሜ ትክክለኛነትን የሚያረጋግጡ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችሉ ስልቶች አሉ።
ዩቲዩብ መጀመሪያ ላይ በእገዳው ውስጥ አልተካተተም ነበር። ሆኖም በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ መንግሥት ውሳኔውን ቀልብሷል።
እገዳው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች በዩቲዩብ ቪዲዮዎችን መመልከት ቢችሉም ይዘቶችን የሚጭኑበት ወይም ሃሳብ ለመለዋወጥ የሚጠቀሙት ገጽ እንዳይኖራቸው ይከለክላል።
ቤክ፣ ቤተሰቡ ከሚኖርበት ምዕራብ አውስትራሊያ ፐርዝ ወደ ለንደን ሄዶ ለመኖር የደረሰበትን ውሳኔ ሲያስረዱ የማኅበራዊ ሚዲያውን እገዳ እንደማይቃወሙ ተናግረዋል።
"ታዳጊዎችን በኢንተርኔት ከሚደርስባቸው ጉዳት ለመጠበቅ እንደሆነ እንረዳለን፤ ሆኖም እኛ ኢንተርኔትን የምንጠቀመው ለበጎ ዓላማ ነው" ብለዋል።
ጨምረውም በማኅበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚደርስባቸው ታዳጊዎች እንዳሉ እንደሚገነዘቡ እና ይህንን እንደማይክዱ ገልጸዋል።
ሆኖም መንግሥት እገዳው እንዴት ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል በግልጽ አለማስቀመጡ ስጋት እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል።
"ሕጉን ተፈፃሚ ለማድረግ ውጣ ውረዶች ይኖራሉ ብዬ ስለማስብ ይህ እኛን ይሸፍነናል" ብለዋል።
የቤክ ባለቤት በበኩላቸው ማኅበራዊ ሚዲያ ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በብዙ በመለወጡ በርካታ ታዳጊዎች መድረኩን ለጥሩ ዓላማ በመጠቀም ልዩነት እየፈጠሩ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ሁሉም የቤተሰቡ አባላት የብሪታኒያ እና የአውስትራሊያ ጥምር ዜግነት ያላቸው በመሆኑ እንዲሁም ሴት ልጃቸው ሻርለት በቅርቡ ትምህርቷን በኦንላይን ለመከታተል በመወሰኗ የፈለጉት ቦታ መኖር ስለሚችሉ ወደ ዩኬ ለመሄድ መወሰናቸውን ተናግረዋል።
በኦንላይን ቻርሊ በሚል ስም ይዘቶችን የምታጋራው ሻርለት ግማሽ ሚሊዮን ገደማ የዩቲዩብ ተከታዮች ያሏት ሲሆን፣ በቲክቶክ 300 ሺህ፣ በኢንስታግራም ደግሞ ወደ 200 ሺህ ገደማ አድናቂዎች አሏት። የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቿን የሚያስተዳድሩት ወላጆቿ ናቸው።
ቤተሰቡ በዋናነት ይዘቶችን የሚያጋራው በወንድ ልጃቸው ፕሪስሊይ የዩቲዩብ ገጽ ሲሆን፣ 2.8 ሚሊዮን ሰብስክራይበሮችን ማግኘት ችሏል። የቤተሰቡ የዩቲዩብ ገጽ ደግሞ 1.8 ሚሊዮን ተከታዮች አሉት።
ቤተሰቡ ከሚያጋራቸው ቪዲዮዎች መካከል የሜካፕ አጠቃቀም ትምህርት፣ ጨዋታዎች እና የቤተሰቡ የእረፍት ጊዜ እና ሽርሽር ይገኝበታል።















