አውስትራሊያ እድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች ዩቲዩብን ልትከለክል ነው

የዩቲዩብ ሎጎ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ አውስትራሊያውያን ከታህሳስ ወር ጀምሮ የዩቲዩብ አካውንት እንዳይኖራቸው ሊከለከሉ ነው።

በአውስትራሊያ አዲሱ የማኅበራዊ ሚዲያ እገዳ መሠረት ዩቲዩብ ለታዳጊዎች የተከለከሉ የማኅበራዊ ድረ ገጾች ዝርዝር ውስጥ በመካተቱ ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት ሊከለከል ነው።

መንግሥት ከዚህ በፊት ማኅበራዊ ሚዲያው ለታዳጊዎቹ እንዲከለከል ቀርቦ የነበረውን ሐሳብ ውድቅ አድርጎ ነበር።

ከዚህ ቀደም የቪዲዮ ማጋሪያ የሆነው ዩቲዩብ ከእገዳው ውጪ ተደርጎ የነበረ ሲሆን ቲክ ቶክ፣ ኢንስታግራም፣ ፌስቡክን፣ ኤክስ እና ስናፕቻት ግን ከታሕሳስ ወር ጀምሮ እንዲገደቡ ተወስኗል።

በእገዳው መሠረት ታዳጊዎች ዩቲዩብ ቪዲዮዎችን ማየት ቢችሉም፣ የራሳቸው አካውንት ኖሯቸው ይዘቶችን መጫን ወይም መድረኩ ከሌሎች ጋር ግንኙነትን መፍጠር አይችሉም።

በጎግል ባለቤትነት የተያዘው ዩቲዩብ መድረኩ "ለታዳጊ አውስትራሊያውያን ጥቅም እና እሴቶችን ስለሚሰጥ" በማለት መታገድ እንደሌለበት ተከራክሯል።

ረቡዕ ዕለት በሰጠው መግለጫ "[ዩቲዩብ] ማኅበራዊ ሚዲያ አይደለም" ብሏል።

የአውስትራሊያ ሕጎች የተለያዩ አገራት መሪዎች በከፍተኛ ትኩረት እየተከታተሉት ሲሆን ኖርዌይ ተመሳሳይ እገዳን ስታውጅ፣ ዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ ይህንኑ ለመከተል እንደምታስብ ተናግራለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ማኅበራዊ ሚዲያ በልጆቻችን ላይ ማኅበራዊ ጉዳት እያደረሰ ነው፤ እናም የአውስትራሊያ ወላጆች ከጎናቸው እንዳለን እንዲያውቁ እፈልጋለሁ" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔሴ ረቡዕ ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

ስለ እገዳው "ይህ ብቸኛው መፍትሄ እንዳልሆነ እናውቃለን፤ ነገር ግን ለውጥ ያመጣል" ብለዋል።

የአውስትራሊያ የኢሴፍቲ ኮሚሽነር ጁሊ ኢንማን ግራንት፣ ዩቲዩብ ከ10 እስከ 15 ዓመት ያሉ ልጆች "ጎጂ ይዘት" እያዩበት መሆኑ "በጣም በተደጋጋሚ የተጠቀሰ መድረክ" በመሆኑ ወደ እገዳው እንዲካተት ጠይቀዋል።

ረቡዕ ዕለት የመንግሥት እርምጃ ይፋ ከተደረገ በኋላ የዩቲዩብ ቃል አቀባይ "ቀጣዮቹን እርምጃዎች እናጤናለን" በማለት ከመንግሥት ጋር "መነጋገራችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት በርካታ የአውስትራሊያ ሚዲያዎች ጎግል ዩቲዩብ በእገዳው ውስጥ የሚካተት ከሆነ የፖለቲካ ነፃነትን እንደሚገድብ በመግለጽ መንግሥትን ፍርድ ቤት ለመገተር መዛቱን ዘግበው ነበር።

የፌደራል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አኒካ ዌልስ ለማኅበራዊ ሚዲያ የሚሆን ቦታ ቢኖርም "ሕፃናት ላይ ለሚያነጣጥር አዳኝ አልጎሪዝም የሚሆን ቦታ የለም" ብለዋል።

ልጆችን ከኢንተርኔት ጉዳት ለመጠበቅ መሞከርን ሲገልፁት "ልጆቻችሁ በውቅያኖስ ውስጥ በሞገዶች መካከል ከሻርኮች እንዲዋኙ ለማስተማር ከአነስተኛ መዋኛ ገንዳ ጋር ለማነጻጸር እንደመሞከር" ነው ብለዋል።

"ውቅያኖሱን መቆጣጠር አንችልም፤ ነገር ግን ሻርኮችን መከታተል እንችላለን፤ ለዚያም ነው ይህ ለአውስትራሊያ ልጆች ደህንነት የሚደረግ እውነተኛ ትግል ላይ የሕግ ማስፈራርያ የሚደርስብን፤ ግን አንፈራም" ሲሉ ተናግረዋል።

ዌልስ "የኦንላየን ጨዋታዎች፣ መልዕክት መላላክ፣ የትምህርት እና የጤና መተግበሪያዎች ከ16 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎች ላይ አነስተኛ የማኅበራዊ ሚዲያ ጉዳቶች ስለሚያስከትሉ" በእገዳው ውስጥ አልተካተተሉም ብለዋል።

በእገዳው መሠረት የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የእድሜ ገደቦችን ካላከበሩ እስከ 32.5 ሚሊዮን ዶላር ሊቀጡ ይችላሉ።

ነባር መለያዎችን እንዳይሰሩ ማድረግ እና አዲስ መለያዎችን እንዳይከፈቱ መከላከል እንዲሁም በዙሪያው ያሉ ሥራዎችን ማቆም እና ስህተቶችን ማስተካከል አለባቸው።

አዲሱ እገዳ እንዴት እንደሚሰራ ተጨማሪ ዝርዝሮች የፊታችን ረቡዕ ለፌደራል ፓርላማ ይቀርባል።