ለኢንስታግራም 'ፕራንክ' ሙሽራ ሆና ተውና ጋብቻው የእውነት ሆኖ የተጭበረበረችው 'ሙሽሪት'

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውስትራሊያ የምትኖር አንዲት ሴት ለማኅበራዊ ሚዲያ ፕራንክ በሚል በጓደኛዋ አማካኝት ሙሽራ ሆና የተወነችበት የሰርግ ሥነ ሥርዓት ኋላ ላይ የእውነት ነው ተብሎ ጉዳዩ ፍርድ ቤት ደርሷል።
ነገሩ እንዲህ ነው በአውስትራሊያ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ያሉ ሁለት የውጭ አገር ዜጋ የሆኑ ወንድ እና ሴት የቅርብ ጓደኛሞች መጀመሪያ ለኢንስታግራም ፕራንክ በሚል ነበር የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ በወንዱ የተዘጋጀው።
ምን እንደተደገሰላት ያላወቀችው የፕራንክ 'ሙሽሪት' ጓደኛዋ በኢንስታግራም የማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች እንዳሉት ስለምታውቅ ነገሩ ቀልድ እንደሆነ በማመን በ'ፕራንክ' ሰርጉ ላይ ሙሽራ ሆና ለመሳተፍ ተስማምታ ነበር።
ነገር ግን የሰርግ ሽርጉዱ በወንዱ የተዘጋጀው መረጃውን በመጠቀም በአውስትራሊያ ውስጥ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ሊጠቀምበት ሲሞክር 'ፕራንክ' የተባለው ሰርግ ተታላ የገባችበት እውነተኛ ጋብቻ መሆኑን ለማወቅ ችላለች።
ይህ እንግዳ ሁኔታ የተጀመረው ከሁለት ዓመት በፊት ሁለቱ ጥንዶች በበይነ መረብ የፍቅር ግንኙነት መመሥረቻ መድረክ ላይ ሲተዋወቁ ነው። ይህንንም ተከትሎ በጊዜው ይኖሩባት በነበረችው ሜልበርን አዘውትረው መገናኘት ጀመሩ።
በዚያው ዓመት በታኅሣሥ ወር ደግሞ ሰውየው ለሴቲቱ እንዲጋቡ ጥያቄ አቀርቦላት እርሷም ተቀብላው ነበር።
ከሁለት ቀናት በኋላም ሴቷ ግለሰቡ ሲድኒ ውስጥ በሚደረግ በአንድ ዝግጅት ላይ እንድትሳተፍ ጋበዛት። እሷም ዝግጅቱ "ነጭ ፓርቲ" የሚባል እንደሚሆን ተነግሯት ታዳሚዎቹ ነጭ ለብሰው የሚሳተፉበት በመሆኑ ነጭ ቀሚስ አዘጋጅታ እንድትገኝ ነግሯታል።
ነገር ግን ከዝግጅቱ ስፍራ ስትደርስ ያገኘችው በርከት ያሉ ታዳሚዎችን ሳይሆን ፎቶግራፍ አንሺ፣ የፎቶግራፍ አንሺው ጓደኛ እና አንድ ግለሰብ ብቻ በመሆናቸው "መደንገጧን" እና "መናደዷን" ለፍርድ ቤት ባቀረበችው የክስ ሰነድ ላይ ጠቅሳለች።
"ከቦታው ስደርስ ነጭ የለበሰ ማንም ሰው አላየሁም፣ እናም 'ምን እየሆነ ነው?' ስል ጠየቅሁት። እሱም ወደጎን ጎትቶ በመውሰድ በኢንስታግራም አካውንቱ ላይ የሚያቀርባቸውን ነገሮች በማስፋት ከገጹ ገንዘብ ለማግኘት ሲል ያዘጋጀው የፕራንክ [ሐሰተኛ] ሰርግ ነው ሲል ነገረኝ" ብላለች።
ኢንስታግራም ላይ ከ17 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ጓደኛዋ የሶሻል ሚዲያ ሰው በመሆኑ ያቀረበላትን ሰበብ አምና ተቀበለችው። በተጨማሪም የትኛውም የፍትሐ ብሔር ጋብቻ በፍርድ ቤት አማካይኝት ካልተካሄደ ተቀባይነት አይኖረውም የሚል እምነት ስለነበራት በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ሆነች።
ቢሆንም ግን ነገሩ ሳያሳስባት አልቀረም። ከዚያም ለጓደኛዋ ደውላ ጭንቀቷን ተናገረቻት፣ ነገር ግን ጓደኛው በሁኔታው በመሳቅ ምንም ችግር እንደሌለው ምክንያቱም እውነት ከሆነ መጀመሪያ የጋብቻ ማስታወቂያ ለሚመለከተው አካል ማስገባት እንደሚያስፈልግ፣ እነሱ ግን ይህንን ባለማድረጋቸው አሳሳቢ አለመሆኑን በመግለጽ አረጋጋቻት።
ከዚህ በኋላም በሙሉ ልብ 'ፕራንክ' በተባለው የሰርግ ሥነ ሥርዓት ላይ ተሳተፈች። ከዚያም ሁለቱ ጥንዶች የጋብቻ ቃል ኪዳን ተለዋውጠው በካሜራ ፊት ተሳሳሙ። እሷም በዚያን ጊዜ ነገሩን "እውነተኛ ለማስመሰል" ደስተኛ ሆና ለመቅረብ እንደሞከረች ተናግራለች።
ከጀርባዋ በጓደኛዋ የተደገሰላት ጉድ ይፋ መውጣት የጀመረው 'ፕራንክ' የተባለው ጋብቻ ከተከናወነ ከሁለት ወራት በኋላ ነበር። በዚህም ጓደኛዋ የአውስትራሊያን ቋሚ የነዋሪነት ፈቃድ ለማግኘት ባቀረበችው ማመልከቻ ላይ እሱንም እንደ አጋሯ እንድታካትተው ጠየቃት።
እሷም እስከዚያ ድረስ ሕጋዊ ጋብቻ ባለመፈጸማቸው የጠየቃትን ማድረግ እንደማትችል ስትነግረው፣ ሲድኒ ውስጥ ለኢንስታግራም በሚል የተካሄደው ሥነ ሥርዓት እውነተኛ ሰርግ ነበር በማለት ደባውን እንዳረዳት ለፍርድ ቤት በሰጠችው ቃል ገልጻለች።
ኋላ ላይ ደግሞ የጋብቻ የምሥክር ወረቀት እንዲሁም ሲድኒ ውስጥ 'ፕራንክ' በሚል ከተዘጋጀው የጋብቻ ሥነ ሥርዓት አንድ ወር በፊት የቀረበ እሷ ያልፈረመችበት የጋብቻ ማስታወቂያ መውጣቱን ደረሰችበት። በፍርድ ቤት ሰነዶች መሠረት ጋብቻ በማስታወቂያው ላይ ያለው ፊርማ ከእሷ ጋር በትንሹ ተመሳሳይነት ያለው ነው።
"ፕራንክ ነው የተባለው ጋብቻ እውነተኛ መሆኑን ቀድሜ ባለማወቄ፣ እሱም ከመጀመሪያው መዋሸቱ እና ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት በማቀርበው ማመልከቻ ውስጥ እንዳስገባ በመፈለጉ በጣም ተናድጃለሁ" ስትል ተናግራለች።
የተጭበረበረ ጋብቻ በማዘጋጀት ክስ የቀረበበት ግለሰብም "ሁለታችንም በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ተስማምተናል" እንዲሁም ያቀረበላትን የጋብቻ ጥያቄን ተከትሎ ሴቷ ሲድኒ ውስጥ "ግላዊ በሆነ ሥነ ሥርዓት" ጋብቻቸውን ለመፈጸም በመስማማቷ የተከናወነ ነው ሲል ተከራክሯል።
ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ እንስቷ "የተካሄደውን የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ሁኔታን በተመለከተ እንድትሳሳት ተደርጓል" በማለት በጋብቻ ውስጥ ለመሳተፍ "ትክክለኛውን ፍቃዷን አልሰጠችም" በማለት ብይን ሰጥተዋል።
'ሙሽሪት' ይህንን እንዳወቀች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዳ በተጭበረበረ ሁኔታ ጋብቻ ውስጥ መግባቷን ጉዳዩን የተመለከቱትን ዳኛ ማሳመን በመቻሏ ጋብቻው ውድቅ እንዲሆን ተወስኖላታል።
"ለፕራንክ ሲባል በተደረገ ትወና ላይ እንደተሳተፍች አምናለች። ዝግጅቱንም ቀልድ ነበር ብላለች። በሕጋዊ መንገድ የተረጋገጠ ጋብቻን የሚያሳይ ቪዲዮ ተዓማኒነት ለመፍጠር ሥነ ሥርዓቱ ላይ በሁሉም ነገር የሙሽራዋን ማንነት መያዟ ፍጹም ምክንያታዊ ነበር" በማለት ነገር ግን በማጭበርበር የተፈጸመ ጋብቻ ስለሆነ ፍርድ ቤቱ ጋብቻውን ውድቅ አደርጎታል።












