የሰባተኛው አገራዊ ምርጫ ድምጽ መስጫ ቀን ሰኞ ግንቦት 24 ሆነ

ድምጽ የምትሰጥ ሴት
የምስሉ መግለጫ, በብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይፋዊ የጊዜ ሠሌዳ መሠረት የሰባተኛው አገራዊ ምርጫ ይፋዊ ውጤት የሚገለጸው ሰኔ 4 2018 ዓ.ም. ነው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰባተኛው አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ መስጫ ቀን ግንቦት 24/2018 ዓ.ም. መሆኑን አስታወቀ።

በዚህ የቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ድምጽ የሚሰጠው ሰኞ ዕለት ይሆናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማክሰኞ ኅዳር 30/2018 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሠረት የዕጩዎች ምዝገባ ከጥር 1 እስከ የካቲት 1/2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ አስታውቋል።

ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄደው የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻ ከጥር 1 እስከ ግንቦት 19/2018 ዓ.ም እንደሚሆን የወጣው የጊዜ ሰሌዳ ያስረዳል።

ቦርዱ የመራጮች ምዝገባን በተመለከተ በቴክኖሎጂ ራስን በራስ መመዝገብ ከጥር 15 እስከ መጋቢት 7/2018 ዓ.ም. የሚካሄድ ሲሆን፣ የመራጮች ምዝገባ ደግሞ ከየካቲት 7 እስከ መጋቢት 7 ለአንድ ወር እንደሚካሄድ አስታውቋል።

የቴክኖሎጂ ምዝገባው በስልክ፣ በድረ ገጽ እና በምዝገባ ታቢያዎች በታብሌት አማካኝነት የሚደረግ ምዝገባ መሆኑን የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ተናግረዋል።

ምርጫ ከሚደረግበት ቀደም ብለው ያሉት አራት ቀናት ከግንቦት 20 እስከ ግንቦት 23/2018 ዓ.ም. ቅስቀሳ ማድረግ የማይቻልባቸው የጥሞና ጊዜያት መሆናቸው በጊዜ ሠሌዳው ላይ ተገልጿል።

የምርጫ ውጤት በምርጫ ጣቢያ ደረጃ ይፋ የሚሆነው ግንቦት 24 እና ግንቦት 25/2018 ዓ.ም ሲሆን፣ በክልል ደረጃ ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት ይፋ የሚሆነው ከግንቦት 25 እስከ ግንቦት 29/2018 ዓ.ም. ነው።

በብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይፋዊ የጊዜ ሠሌዳ መሠረት የሰባተኛው አገራዊ ምርጫ ይፋዊ ውጤት የሚነገረው ሰኔ 4/2018 ዓ.ም. መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በግንቦት ወር የሚያካሄደው ሰባተኛው አገራዊ ምርጫ አስቻይ ሁኔታ ባለባቸው የአገሪቱ ክፍሎች ሁሉ እንደሚካሄድ አስታውቋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በበኩሉ ሰባተኛው አገራዊ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት አገራዊ ምክክር መቅደም እንዳለበት መጥቀሱ ይታወሳል።

አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የሰላም እና የፀጥታ ጉዳዮችን በማንሳት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ምርጫ ለማካሄድ አመቺ ሁኔታ አለመኖሩን ይናገራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከዚህ ቀደም የተደረገው ምርጫ ጦርነት በነበረበት ጊዜ መካሄዱን በማንሳት ምርጫው እንደሚካሄድ አረጋግጠዋል።

በአገሪቱ ባለው የሰላም ሁኔታ ላይ የተነሳ ስጋታቸውን የገለጹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልሎች ግጭቶች ባሉበት ሁኔታ ምርጫ ለማካሄድ የጊዜ ሠሌዳ መውጣቱ ላይ ቅሬታቸው ገልጸው ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም ሕገመንግሥቱን ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎች የቀረቡለት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጥረቶች ባልተቋጨችበት ሁኔታ ምርጫ እንዴት ሊካሄድ ይችላል የሚሉ ስጋቶችም ያነሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ይህ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ የተዘጋጀው ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሲቪል ማኅበረሰብ አባላት ጋር በመወያየት መሆኑን ተናግረዋል።