ቻይና 30 የፕሮቴስታንት ቤተ እምነት አባላትን አሰረች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ባለፈው ሳምንት ጂን ድሬክሴል ቻይና ከሚገኙት አባቷ ጂን ሚንግሪ፣ አንድ ፓስተር መጥፋታቸውን ተከትሎ እንድትፀልይላቸው የሚጠይቅ የጽሑፍ መልዕክት መቀበሏን ትናገራለች።
የጽሑፍ መልዕክቱ ሴንዜሄን የምትባል ከተማን ለመጎብኘት የሄደ ሌላ ፓስተር በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ይገልጻል።
"ይህ መልዕክት ከደረሰኝ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ እናቴ ደውላ አባቴን ልታገኘው እንዳልቻለች ነገረችኝ" ስትል አሜሪካ የምትኖረው ጂን ድሬክሴል ለቢቢሲ ተናግራለች።
በሰዓታት ውስጥ ጂን አባቷ በቻይና የፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተሰማ።
አክቲቪስቶች ይህንን የቻይና መንግሥት እርምጃ ባለፉት አስር ዓመታት ከታየው ሁሉ ትልቁ ነው ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ብቻ በፓስተር ጂን ሚንግሪ ከሚመራው ከጽዮን ቤተክርስትያን ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ 30 ክርስትያኖች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ጽዮን ቤተክርስትያን የተመሠረተችው በፓስተር ጂን ሚንግሪ ነው።
የቻይና መንግሥት በቤት ለቤት አምልኮ የሚታወቁት የክርስትያን ኅብረት አባላትን እያደኑ በቁጥጥር ሥር ማዋል መጀመራቸው እየተገለፀ ነው።
በቻይና በኅቡዕ የሚንቀሰቀሱ ቤተ እምነቶችን የሚመለከት አዲስ ሕግ ማውጣቷን አክቲቪስቶች ይገልጻሉ።
ይህንንም ተከትሎ ከቅርብ ወራት ወዲህ በእነዚህ ቤተ ክርስትያን አባላት ላይ ከፍተኛ ጫና እየደረሰ መሆኑን አስታውቀዋል።
ቻይና ምንም እንኳን እምነት የለሽ በሆነ የኮሚኒስት ፓርቲ የምትመራ ቢሆንም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የክርስትና እምነት ተከታይ ሕዝብ አላት።
በቅርቡ መንግሥት ይፋ ያደረገው አሃዝ እንደሚያሳየው በአገሪቱ ውስጥ 38 ሚሊዮን ፕሮቴስታንቶች እና 6 ሚሊዮን የሚጠጉ ካቶሊኮች ይኖራሉ።
ይህ ቁጥር ግን የሚያሳየው በይፋ ለቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ታማኝነታቸውን ገልጸውና ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱት ካቶሊክ ፓትሪዮት አሶሲየሺን እና ዘ ፕሮቴስታንት ስሪ ሰልፍ ፓትሪዮቲክ ሙቭመንት አባላት ብቻ ነው።
የመብት ተሟጋቾች እና ምሑራን አገሪቱ የምትመራባቸውን ርዕዮተ ዓለሞች የማይቀበሉ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ያልተመዘገቡ ቤተ እምነቶች እና የቤት ለቤት ኅብረት በሚል የሚታወቁ ይኖራሉ ሲሉ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
በርካታ እነዚህ ቤተ እምነቶች የቻይና መንግሥት በሃይማኖታዊ ቡድኖች ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር ለማጠናከር ለዓመታት በሚወስዳቸው እርምጃዎች የተለያየ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ከእነዚህም መካከል የቤተ ክርሰትያኖች ሕንጻዎች ፈራርሰዋል፤መስቀሎች ከሕዝብ ዕይታ እንዲነሱ ተደርገዋል።
ሃይማኖታዊ መጻሕፍት እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁሶች ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሲሆን የተወሰኑ ክርስትያናዊ መተግበሪያዎች በቻይና እገዳ ተጥሎባቸዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2005 እና እንደገና በ 2018 መንግሥት በሃይማኖት ቡድኖች ላይ ያሉትን መመሪያዎችን በማሻሻል ጥብቅ አድርጎታል።
እአአ በ 2016 ፣ የቻይና መሪ ዢ ጂንፒንግ የክርስትያን ሃይማኖት ተከታዮች "ወደ ቻይና ባሕል እንዲዋሃዱ" ጠይቀዋል።
እንደ ጽዮን ያሉ በኅቡዕ የሚንቀሳቀሱ ቤተ እምነቶች እአአ በ2018 የወጣው እና በይፋ ለማምለክ የመንግሥትን ይሁንታ ማግኘት የሚጠይቀው ደንብ ተጠቂዎች ናቸው።
በርካቶች በይፋ የሚያደርጓቸውን የአምልኮ ተግባራት እንዲያቆሙ እና በኦንላይን ላይ ብቻ አገልግሎታቸውን እንዲያቀርቡ ወይንም እንዲዘጉ አድርጓል።
በቀጣዩ ዓመትም ጥቂት ስመ ጥር ፓስተሮች በቁጥጥር ሥር ውለው እስራት ተፈርዶባቸዋል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ የቻይና ባለሥልጣናት ዳግም ደንቦቹን በማጥበቅ እርምጃ መውሰድ መጀመራቸውን አጠናክረው መቀጠላቸው ታይቷል።
ባለፈው ዓመት በግንቦት ወር የጽዮን ብርሃን የተሰኘ ቤተ እምነት ፓስተር የሆኑት ጋኦ ኩዋንፉ "የሕግ ተግባራዊነት ለማደናቀፍ የመናፍስት አሰራርን በመጠቀም" በሚል በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
በሚቀጥለው ወር ደግሞ የሊንፌን ጎልደን ላምፕስታንድ ቤተክርስትያን በርካታ አባላት በቁጥጥር ሥር ውለው በማጭበርበር ወንጀል እስር ተፈርዶባቸዋል።
የመብት ተሟጋቾች ግን እስሩ በሐሰት ወንጀል ላይ የተመሰረተ ነው ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።
በመስከረም ወር እንዲሁ ባለሥልጣናት የኦንላይን የሥነ ምግባር መመሪያ ለሃይማኖት ሰዎች ማስተዋወቃቸውን ይፋ አድርገዋል።
ይህ ደንብ በኦንላይን የሚሰጡ የአምልኮ ተግባራት ተመዝግቦ ፈቃድ ባለው ቡድን ብቻ መሆን እንዳለበት የሚደነግግ ነው።
ይህ በኅቡዕ የሚንቀሳቀሱ ቤተ ዕምነቶችን እንቅስቃሴ ለመግታት ያለመ መሆኑን ብዙዎች ያምናሉ።
ባለፉት ጥቂት ወራት የጽዮን ቤተክርስትያን አባላት በፖሊስ ጥያቄ እየቀረበላቸው እንደነበር ጂን ድሬክሴል ትናገራለች።
ባለፈው አርብ እና ቅዳሜ በአገሪቱ 10 ከተሞች፣ ቤይጂንግ እና ሻንጋይን ጨምሮ በሃይማኖት ተቋማት ላይ ዘመቻዎች ማካሄዳቸውን ጀምረዋል።
በጓንግዚ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ቤይሃይ ከተማ ከሚገኘው ዋና የአምልኮ ሥፍራቸው ከተወሰዱት ጂን በተጨማሪ ሌሎች ፓስተሮችን፣ አገልጋዮች እና ምዕመናን መታሰራቸውን ቤተክርስቲያኒቱ ገልጻለች።
ቢቢሲ በቤይሃይ የሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ለጂን ይፋዊ የእስር ማዘዣ ያወጣውን ግልባጭ አግኝቷል።
ጂን በአሁኑ ጊዜ በቤይሃይ ቁጥር ሁለት እስር ቤት እንደሚገኙ እና "በሕገወጥ የመረጃ መረቦች አጠቃቀም" መጠርጠራቸውን ይገልጻል።
ቢቢሲ እስራቱን ለማረጋገጥ የአካባቢ ባለስልጣኖችን ጠይቋል።
የተወሰኑ የታሰሩ የቤተ ክርስትያኑ አባላት የተለቀቁ ቢሆንም በርካቶቹ አሁንም በማረሚያ ቤት ይገኛሉ።















