ቻይና በታይዋን አቅራቢያ አዲስ ወታደራዊ ልምምድ አካሄደች

የቻይና የጦር ጀቶች ባለፉት ቀናት በተካሄዱት ወታዳራዊ ልምምዶች ተሳትፈዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቻይና የጦር ጀቶች ባለፉት ቀናት በተካሄዱት ወታደራዊ ልምምዶች

የቻይና ጦር በታይዋን አቅራቢያ አዲስ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ልምምድ ማካሄድ መቀጠሉን አስታወቀ።

ቻይና ይህንን አዲስ ወታደራዊ ልምምድ ማካሄድ የጀመረችው ቀደም ሲል በቀጥታ ስታካሂድ የነበረውን የተኩስ ልምምድ እሁድ ዕለት ማጠናቀቋን ካስታወቀች በኋላ ነው።

የቻይና ጦር የምሥራቅ ዕዝ፣ የፀረ-ሰርጓጅ መርከብ ጥቃቶችን እና የባሕር ላይ ወረራዎችን ልምምድ እንደሚያካሂድ ገልጿል።

ቀደም ብሎ ለአራት ቀናት ሲካሄድ የነበረው ልምምድ የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ በታይዋን ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ከቤይጂንግ የተሰጠ ምላሽ ነበር።

ታይዋን፣ ቻይና ወታደራዊ ልምምዱን የምታካሂደው በደሴቲቱ ላይ ወረራ ለመፈፀም ነው ስትል ትከሳለች።

ነገር ግን ቻይና እስካሁን በምታካሂደው ልምምዶች የቻይና የጦር አውሮፕላን እና መርከቦች ከባሕር ዳርቻ 22 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘውና በግዛቷ በሚገኘው የውሃ አካል እንዳልገቡ ታይዋን ሰኞ ዕለት ገልጻለች።

አሜሪካ፣ አውስትራሊያ እና ጃፓን ቻይና እያካሄደች ያለውን ወታዳራዊ ልምምድ “ዓላማው በዋናው መሬት እና በደሴቷ መካከል ያለውንና 180 ኪሎ ሜትር ስፋት የሚሸፍነውን የታይዋን ሰርጥ ሁኔታ መለወጥ ነው” ሲሉ አውግዘውታል።

በወታደራዊ ልምምዱ ወቅት የቻይና አውሮፕላን እና መርከቦች በተደጋጋሚ የባህር ሰርጥ ድንበሯን አቋርጠዋል።

የታይዋን የመከላከያ ሚኒስትር ሰኞ ዕለት የባህር ሰርጥ ድንበሩ ከ1950ዎቹ ጀምሮ የነበረ መሆኑን ተናግረዋል።

ቻይና ለአፈ ጉባዔዋ ናንሲ ፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያላትን ትብብር በማቋረጧ በአሜሪካ ወቀሳ ቀርቦባታል።

ቤይጂንግ ታይዋንን የምታያት እንደ ተገንጣይ ግዛት እና አስፈላጊ ከሆነም በኃይል የራሷ ማድረግ እንደምትችል ነው።

በተቃራኒው ታይዋን ግን ራሷን የምታስተዳደር ደሴት እንደሆነች ነው የምታምነው። የዓለም መሪዎች ለዚህ እውቅና እንደሚሰጡ የሚያሳዩ ማንኛውም ፍንጮችም ቻይናን ያስቆጣሉ።

በታይዋን አቅራቢያ እንደ አዲስ የታየው እንቅስቃሴ የተጀመረው የቻይና የባሕር ላይ ባለሥልጣናት ልምምዶች በሌሎች ቦታዎችም እንደሚካሄዱ ካሳወቁ በኋላ ነው።

በቻይና እና በኮሪያ ሰርጥ መካከል በሚገኘው በቢጫ ባሕር አዲስ ዕለታዊ ወታደራዊ ልምምዶች ከቅዳሜ ጀምሮ እስከ ነሐሴ ወር አጋማሽ ድረስ እንደሚካሄዱም ተገልጿል። ይህም የቀጥታ የተኩስ ልምምድን ይጨምራል ተብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ ከቢጫ ባሕር ሰሜናዊ አቅጣጫ በሚገኘው በቦሃይ ባሕር አካባቢ ለአንድ ወር የሚዘልቅ ቅዳሜ ዕለት ተጀምሯል።

ሰኞ ዕለት ቻይና በደቡብ ቻይና በሚገኘው ባሕር የቀጥታ የተኩስ ልምምድ መጀመሯን አስታውቃለች።