ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ወራት 50 የረድዔት ሠራተኞች ሕይወታቸውን እንዳጡ ተገለጸ
ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ 50 የረድዔት ሠራተኞች በኢትዮጵያ በሰብዓዊ ተግባራት ላይ ተሰማርተው እያሉ ሕይወታቸውን እንዳጡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ፕሮግራም አስታወቀ።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ኢትዮጵያን አስመልክቶ ሰኔ 9/2016 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርቱ የፀጥታ ችግር በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚያደርገው ሰብዓዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ገልጿል።
በቅርቡ የዓለም የምግብ ፕሮግራም አጋር የሆነው ሜዲካል ቲምስ ኢንተርናሸናል የተሰኘው የረድዔት ድርጅት አሽከርካሪ በአማራ ክልል እንደተገደለ ሪፖርቱ ጠቅሶ፣ ሕወታቸው የጠፋ የእርዳታ ሠራተኞች ቁጥር ሃምሳ ማድረሱንም አክሏል።
የረድዔት ሠራተኞችን ይዞ የነበረው መኪና በጥይት መመታቱን ተከትሎ አሽከርካሪው መገደሉን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ግንቦት 20/2016 ዓ.ም. መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ያለው የፀጥታ ሁኔታ ለሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞች ጭምር ፈታኝ መሆኑንም ኮሚሽኑ በወቅቱ ገልጿል።
የአውሮፓውያኑ 2024 ከገባ ጀምሮ 50 የረድዔት ሠራተኞች ሕይወታቸው እንዳለፈ ያስታወቀው ተቋሙ፣ በምን ሁኔታ እና የት ቦታ እንደሞቱ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
ከፀጥታ ችግር በተጨማሪ የነዳጅ እጥረት፣ የመንገድ መዘጋት እና ደካማ መሠረተ ልማት በእርዳታ አቅርቦት ሰንሰለት ላይ ችግር መደቀኑንም የዓለም ምግብ ፕሮግራም አመልክቷል።
በኢትዮጵያ ከ2019 ጀምሮ እስከ 2023 ባሉት ዓመታት 36 የረድዔት ሠራተኞች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ( ዩኤን ኦቻ) ባለፈው ዓመት ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።
በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ባሉ ጦርነቶች እና ግጭቶች ምክንያት ሰብዓዊ ተደራሽነት ፈታኝ መሆኑንም ማስተባበሪያ ቢሮው በዘንድሮው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ባወጣው ሪፖርት ጠቅሷል።
ዩኤን ኦቻ በአማራ ክልል በቀጠለው ግጭት ምክንያት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ እና በርካታ ጉዳቶች ማጋጠማቸውን ገልጿል።
የረድዔት ሠራተኞች በታጠቁ አካላት ቀጥታ ዒላማ ባይሆኑም “ባለው የፀጥታ ሁኔታ ተለዋዋጭነት፣ የአካባቢ ሚሊሻዎችን ጨምሮ መሳሪያ ያነገቱ ዜጎች በአጠቃላይ የታጠቁ አካላት መበራከት ለረድዔት ሠራተኞች እና ለሰብዓዊ እርዳታ ሥራዎች ከፍተኛ ስጋትን ደቅነዋል” ብሏል።
የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ በረድዔት ሠራተኞች ላይ ዕገታ፣ ዝርፊያ እና ጥቃትን ጨምሮ 93 ክስተቶችን በአውሮፓውያኑ 2023 መዝግቤያለሁ ብሏል።
በጥር እና የካቲት ወራትም አምስት የረድዔት ሠራተኞች በሦስቱ ክልሎች መገደላቸውንም አካቷል።
በትግራይ የሰሜናዊ ክፍል ሪፖርቱ በስም ያልጠቀሳቸው የውጭ ኃይሎች መኖራቸው ችግሮችን እንዳባባሱ ጠቅሷል።
የረድዔት ሠራተኞች መገደልም ሆነ ጥቃት መድረስ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አገራትም በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ዩኤን ኦቻ ከወር በፊት ባወጣው ሪፖርት ገልጿል።
በዚህ ሪፖርት መሠረትም ባለፈው ዓመት በዓለማችን የተገደሉ የረድዔት ሠራተኞች ቁጥር ከሁለት ዓመት በፊት ከነበረው በእጥፍ ጨምሮ 261 ደርሷል ብሏል።
በዚሁ ዓመትም 78 የረድዔት ሠራተኞች መታገታቸው እንዲሁም 196 ደግሞ መቁሰላቸውን በዚሁ ወቅት የወጣው ሪፖርት ያስረዳል።