በአሜሪካ የካቶሊክ ትምህርት ቤት በቅዳሴ ወቅት በተከፈተ ተኩስ ሁለት ህጻናት ተገደሉ

በሚኒያፖሊስ የሚገኘው የካቶሊክ ትምህርት ቤት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በአሜሪካዋ ግዛት ሚኒያፖሊስ በአንድ የካቶሊክ ትምህርት ቤት በቅዳሴ ወቅት በተከፈተ ተኩስ ሁለት ህጻናት ሲገደሉ፤17 ቆሰሉ።

ተማሪዎቹ በትምህርት ቤቱ በሚገኘው ቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ ስነ ስርዓት እየተከታተሉ በነበረበት ወቅት ጥቃት እንደተከፈተባቸው ተገልጿል።

የተኩስ ጥቃቱ በጸረ-ካቶሊክነት የጥላቻ ወንጀል ምርመራ እንደተከፈተበት የአሜሪካ የፌደራል የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይ አስታውቋል።

"ኤፍቢአይ ይህንን የተኩስ ጥቃት እንደ የሃገር ውስጥ ሸብርተኝነት እና በካቶሊክ ላይ የተነሳ የጥላቻ ወንጀልነት እየመረመረው ነው" ሲሉ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ካሽ ፓቴል በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።

ጥቃት አድራሹ በከተማዋ በሚገኘው 'አኑሲዬሽን [የወንጌል ] በተሰኘው ቤተክርስቲያን ረቡዕ ማለዳ በቅዳሴ ወቅት በመስኮት በኩል ተኩስ ከፍቶ የ8 እና የ10 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ህጻናት ገድሏል።

አጥቂው ራሱ በከፈተው ተኩስ ህይወቱ ያለፈ ሲሆን ፖሊስ የ23 ዓመት ዕድሜ ያለው ሮቢን ዌስትማን የተባለ እንደሆነ ገልጿል።

በጥቃቱ "ከፍተኛ ኃዘን እንደተሰማቸው" የሮማው ካቶሊክ ሊቃነ ጳፓስ ፖፕ ሊዮ ገልጸዋል።

"ይህ ሆን ተብሎ በንጹሃን ህጻናት እና በአምልኮ ላይ በነበሩ ምዕመናን ላይ ሆን ተብሎ የተፈጸመ ጥቃት ነው" ሲሉ የፖሊስ ኃላፊ ብሪያን ኦሃራ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"በህጻናት በተሞላ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተኩስ መክፈት የሚያሳየውን ጭካኔ እና ቦቅቦቃነት ለመረዳት የሚከብድ ነው" ሲሉ አክለዋል።

ባለስልጣናቱ የጠረጠሩትን የጥቃት መንስኤ እስካሁን ይፋ አላደረጉም።

ፖሊስ በቤተ ክርስቲያኑ ተኩስ መከፈቱ ሪፖርት የተደረገለት ረቡዕ ጥዋት ከሁለት ሰዓት በፊት ነበር።

ጥቃት አድራሹ ትምህርት ቤት በግቢው ውስጥ ባለው ቤተክርስቲያ በመስኮት በኩል ሶስት ጠመንጃዎችን በመጠቀም ተኩስ ከፍቷል። ፖሊስ በስፍራው የጪስ ቦምብ አግኝቷል።

ፖሊስ ጥይቱ የተተኮሰው በቤተ ክርስቲያኑ ውጭ ወይስ ውስጥም ተተኩሷል የሚለውን እያጣራ ስለመሆኑ አስታውቋል።

"ዷ፣ ዷ" የሚል ድምጽ ረቡዕ ማለዳ መጀመሪያ እንደሰሙ ለዋል ስትሪት ጆርናል የተናገሩት በቤተ ክርስቲያኗ አቅራቢያ የሚኖሩ ፒጄ መድ በኋላ ተኩስ መከፈቱን መረዳታቸውን ገልጸዋል።

ግለሰቡ ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ሮጠው ሲሄዱም የጥይት ማስቀመጫ በግቢው እንደተመለከቱ ተናግረዋል።

ከጥቃቱ የተረፈ አንድ የአስር ዓመት ልጅ ጓደኛው ከላዩ ላይ ተኝቶ ከጥቃቱ እንዳዳነው ለሲቢኤስ አጋር ሚዲያ ደብልዩ ሲሲኦ አገልጿል።

ጓደኛው እሱን ከላዩ ላይ ሆኖ ቢያተርፈውም እሱ በጥይት መመታቱን ተናግሯል።

"ጓደኛዬ ከኋላ ተመትቶ ሆስፒታል ሄዷል። ለህይወቱ በጣም ፈርቼ ነበር አሁን ግን ደህና ይመስለኛል" ብሏል።

በደቡባዊ ሚኒያፖሊስ የሚገኘው አኑንሲዬሽን ቤተ ክርስቲያን ዕድሜያቸው ከ5-14 ለሆኑ ህጻናት ትምህርት ቤት አለው።

የጥቃት አድራሹ እናት ሜሪ ግሬስ ዌስትማን በትምህርት ቤቱ ውስጥ ሰራተኛ እንደነበረች እና ከአራት ዓመት በፊት ጡረታ መውጣቷ ተነግሯል።

ፖሊስ ጥቃት አድራሹ በጥቃቱ ወቅት በማህበራዊ ሚዲያ ሊያወጣው ያሰበውን ልጥፍ ያገኘው ሲሆን መርማሪዎች ልጥፉን ሰርዘውታል።

የከተማዋ ገዥ ቲም ዋልዝ እንዲሁም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል።

ትራምፕ የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንደሚውለበለብም ተናግረዋል።