ትራምፕ ቢቢሲን የመክሰስ "ግዴታ" አለብኝ አሉ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቢቢሲ በፓኖራማ ዘጋቢ ፊልም ላይ የንግግራቸው ክፍል ስለቆራረጠበት መንገድ ክስ የመመሥረት "ግዴታ" አለብኝ አሉ።

ፕሬዝዳንቱ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወቅት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥር 6/2021 ያደረጉት ንግግር "ተቆራርጧል" እና የቀረበበት መንገድ ተመልካቾችን "ያጭበረበረ" ነበር ብለዋል።

የትራምፕ ጠበቆች ቢቢሲ ካላስተባበለ፣ ይቅርታ ካልጠየቀ፣ እንዲሁም ካሳ ካልከፈለ የ1 ቢሊየን ዶላር ክስ እንደሚመሠርቱ ከጻፉ በኋላ ፕሬዝዳንቱ በጉዳዩ ላይ ሲናገሩ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።

የቢቢሲ ቦርድ ሊቀ መንበር ሳሚር ሻህ ከዚህ ቀደም በአርትዖቱ ላይ ለተፈጠረው "የውሳኔ ስህተት" ይቅርታ ጠይቀዋል።

ፎክስ ኒውስ 'ዘ ኢንግራሃም አንግል' የተሰኘው ፕሮግራም ላይ የቀረቡት ፕሬዝዳንቱ ክስ በመመሥረቱ አቋማቸው ይገፉበት እንደሆን ተጠይቀው ሲመልሱ "እንግዲህ ግዴታ ያለብኝ ይመስለኛል፤ ለምን አላደርገውም? ምክንያቱም ሕዝቡን አጭበርብረዋል፤ ይህንንም አምነዋል" ብለዋል።

ትራምፕ አክለውም "ጥር 6 ያደረኩትን ንግግር ቀይረውታል፤ በጣም ምርጥ ንግግር ነበር ያደረግኩት። በጣም የሰከነ ንግግር ነበር፤ እና እነርሱ ጽንፈኛ ንግግር አደረጉት።

"እና ለወጡት። የሠሩት ሥራ የሚገርም ነው።"

በድጋሚ በሕጋዊ መስመር መሄዱን ይገፉበት እንደሆነ የተጠየቁት ፕረዝዳንቱ " እንግዲህ ያንን ለማድረግ ግዴታ አለብኝ፤ ምክንያቱም ዝም ብለህ መልቀቅ የለብህም፤ ሰዎች ያንን እንዲያደርጉ መፍቀድ የለብህም።"

የፎክስ ኒውስ ቃለ መጠይቅ የተቀረፀው ሰኞ ዕለት ሲሆን፣ ቢቢሲን የሚመለከተው ምላሻቸው በአሜሪካ ውስጥ እስከ ማክሰኞ ምሽት ድረስ አልተላለፈም ነበር።

እሁድ ዕለት ቢቢሲ ከትራምፕ ጠበቃዎች ደብዳቤ ደርሶታል።

ደብዳቤው ቢቢሲ ዘጋቢ ፊልሙን "ሙሉ በሙሉ እና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ እንዲያወርድ" ይቅርታ እንዲጠይቅ እንዲሁም "ፕሬዝዳንት ትራምፕ ላይ ለደረሰው ጉዳት ተገቢውን ካሳ እንዲከፍል" ይጠይቃል።

ጠበቆቹ በደብዳቤያቸው ላይ እስከ አርብ ኅዳር 5/2018 ዓ.ም. ድረስ ቀነ ገደብ ሰጥተዋል።

ይህ የማይፈጸም ከሆነም የአንድ ቢሊዮን ዶላር ክስ እንደሚመሠርቱ አስጠንቅቀዋል።

ቢቢሲ በተገቢው መንገድ ምላሽ እንደሚሰጥ አስታውቋል።

ቢቢሲ ኒውስ ቢቢሲ በትራምፕ አስተያየት ላይ ምላሽ ጠይቋል።

ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ከተመለሱ በኋላ በሌሎች መገናኛ ብዙኃን ላይ ስለ እርሳቸው በሠሯቸው ዘገባዎች የተነሳ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል።

ከሲቢኤስ እና ኤቢሲ ጋር የነበራቸው ውዝግብ ከፍተኛ ክፍያ ከተቀበሉ በኋላ ከስምምነት የደረሱ ሲሆን፣ ኒውዮርክ ታይምሰ ላይ ደግሞ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል።

የቢቢሲ የፓኖራማ ዘጋቢ ፊልም የተላለፈው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከመደረጉ ጥቂት ቀናት በፊት አውሮፓውያኑ ኅዳር 2024 ነው።

ነገር ግን ሾልኮ የወጣ የቢቢሲ ማስታወሻ ባለፈው ሳምንት በዴይሊ ቴሌግራፍ ጋዜጣ ላይ መታተሙን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ መነጋገሪያ ሆኗል።

በማስታወሻው ውስጥ፣ የቢቢሲ የኤዲቶሪያል ስታንዳርድ ኮሚቴ የቀድሞ ገለልተኛ የውጭ አማካሪ የንግግሩ አንድ ክፍል በጥር 2021 የካፒቶል አመፅን በሚያበረታታ መልኩ ተስተካክሏል የሚል ስጋታቸውን ሰፍሮ ይገኛል።

ትራምፕ በንግግራቸው "ወደ ካፒቶል እንሄዳለን፤ እንዲሁም ጀግና ሴናተሮቻችን እና የኮንግረስ አባላቶቻችንን እንደግፋቸዋለን" ብለዋል።

ይሁን እንጂ ፓኖራማ በዘጋቢ ፊልሙ ላይ ያስተላለፈው "ወደ ካፒቶል እንሄዳለን. . . እንዲሁም እዚያ ከእናንተ ጋር ነኝ። እንታገላለን፤ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እንታገላለን" የሚል ነው።

"እንታገላለን" ወይም "ትግል" የሚለውን ቃል በዚህ ንግግራቸው ወቅት ከ20 ጊዜ በላይ ተጠቅመዋል።

የፓኖራማ ዘጋቢ ፊልም ያስነሳው ቅሬታ ዋና ዳይሬክተሩን ቲም ዴቪን አንዲሁም የዜና ክፍሎች ኃላፊዋን ዴብራ ተርነስ አንዲለቅቁ አድርጓል።

ይህ ጉዳይ ሾልኮ መውጣቱን ተከትሎ ከኃላፊነት ከለቀቁ አመራሮች አንዱ የሆኑት የቢቢሲ ኒውስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴብራህ ተርነስ መገናኛ ብዙኃኑ "ተቋማዊ መልድዎ" የለበትም ሲሉ ተከላክለዋል። የቢቢሲ ዋና ዳይሬክተር ቲም ዴቪም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኃላፊነታቸውን ለቅቀዋል።

ሁለቱ አመራሮች እሑድ ዕለት እንደሚለቅቁ ያስታወቁት የእንግሊዙ ዘ ቴሌግራፍ ጋዜጣ ሾልኮ የወጣ የቢቢሲ የውስጥ ማስታወሻን በማጣቀስ ያወጣውን ዘገባ ተከትሎ ጫና ከተፈጠረባቸው በኋላ ነው። ማስታወሻው የቢቢሲ ኤዲቶሪያል ስታንዳርድ ኮሚቴ ገለልተኛ የውጭ አማካሪ በነበረው ማይክል ፔስኮት የተዘጋጀ ነው።

የቀድሞው አማካሪ ማስታወሻ፤ የጋዛ ዘገባዎችን በተመለከተ እንዲሁም ጸረ ትራምፕ እና ጸረ እስራኤል ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች በመጥቀስ ቢቢሲን በአድሏዊነት ይከስሳል።

ወደ አንድ ወገን ያደላ የፆታ ቅየራ አዘጋገብ እና ሌሎች "የሚረብሹ ጉዳዮችም" ተጠቅሰዋል። በቢቢሲ ፓናሮማ ፕሮግራም ዘጋቢ ፊልም ላይ የተደረገው የአርትኦት ጉዳይንም አንስቷል።

የቢቢሲ ቦርድ ሊቀ መንበር ሳሚር ሻህ የዘጋቢ ፊልሙ ዝግጅት ላይ "የውሳኔ አሰጣጥ ስህተት" መፈጸሙን አምነዋል። የትራምፕ ንግግር አርትኦት የተደረገበት መንገድም "እርምጃ እንዲወሰድ ቀጥታ ጥሪ የተላለፈ" አስመስሎ እንዳቀረበ ተናግረዋል። ቢቢሲ ይቅርታ እንደሚጠይቅም አክለዋል።