ጋዜጠኛዋን ስለ ጋዛ ጦርነት ባጋራችው ጽሑፍ ያባረረው የአውስትራሊያ ሚዲያ ቅጣት ተጣለበት

የአውስትራሊያ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን የፕሮግራም አቅራቢዋን ስለ ጋዛ ጦርነት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋራችው ጽሑፍ የተነሳ ማባረሩ ተገቢ አይደለም በሚል 99,200 የአሜሪካን ዶላር ቅጣት እንዲከፍል ተወሰነ።

አውስትራሊያን ብሮድካስቲንግ ከርፖሬሽን (ኤቢሲ) የሬዲዮ ፕሮግራም አቅራቢዋን አንቶኔቴ ላቶፍን እአአ ከታሕሳስ 2023 ጀምሮ የፖለቲካ አመለካከቷን የሚያንጸባርቅ ልጥፎችን በማጋራቷ መባረሯ ተገቢ አይደለም በሚል የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ወስኗል።

ላቶፍ ለደረሰባት የጉዳት ካሳ 70ሺህ የአውስትራሊያ ዶላር እንዲከፈላት የተደረገ ሲሆን ረቡዕ ዕለት ደግሞ ኤቢሲ ከጥፋቱ እንዲማር "ተጨባጭ" የሆነ የገንዘብ ቅጣት ሊጣልበት ይገባል ሲሉ ዳኛ ዳሪል ራንጊያህ ወስነዋል።

የመገናኛ ብዙኃኑ በይፋ የፕሮግራም አቅራቢዋን ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን አድማጮቹን እና ሠራተኞቹን በዚህ የተነሳ ቅር ማሰኘቱንም ገልጿል።

የላቶፍ መባረር ከፍተኛ የሆነ የሕዘብ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን በመገናኛ ብዙኃኑ ኤቢሲ ውስጥ ደግሞ ውዝግብ ፈጥሯል።

የድርጅቱ ጋዜጠኞች በመገናኛ ብዙኃኑ ነጻነት እና ሠራተኞቹን በተለይ ደግሞ ከተለያየ ባሕል የመጡትን አንዴት እንደሚደግፍ ጥያቄ አንስተዋል።

ዳኛ ራንጊያህ ረቡዕ ዕለት "ኤቢሲ የመብት ተሟጋቾችን ለማስደሰት በሚል የሠራተኞቹን መብት አሳልፎ ሲሰጥ የአውስትራሊያን ሕዝብ ክፉኛ አስቀይሟል" ብለዋል።

"ኤቢሲ ያጋጠመው ሕዝባዊ ቁጣ ተገቢ ያልሆነ ምግባሩ ተቀባይነት እንደሌለው እንዳስገነዘበው የተረዳ ይመስለኛል። ይሁን እንጂ መልዕክቱን መቀበሉን እና ማዳመጡን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ቅጣቶች አስፈላጊ እንደሆኑ እገምታለሁ።"

ላቶፍ በአውስትራሊያ ሚዲያዎች ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ስትሰራ የቆየች ናት።

ከዚያም ባሻገር ሚዲያ ውስጥ ስላለ የዘር መድልዖ፣ እንዲሁም ማግለል እና የአእምሮ ጤና ላይ በመቀስቀስ ስሟን ተክላለች።

በሲድኒ የሚገኛው የኤቢሲ ቢሮ ማለዳ ለሚያቀርበው ዝግጅቱ በአቅራቢነት የቀጠራት ቢሆንም ጥቂት ጊዜ እንደሰራች ቅጥሯ ተቋርጧል።

ከአቅራቢነት መነሳቷን የሚገልጸው ዜና ሾልኮ ከወጣ በኋላ በአውስትራሊያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል።

ከመባረሯ ሰዓታት ቀደም ብሎ ላቶፍ ሂውመን ራይትስ ዎች እስራኤል ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያ አድርጋ ትጠቀማለች ሲል ያቀረበውን ሪፖርት አጋርታ ነበር።

ኤቢሲ በችሎት ላይ ላቶፍ በማኅበራዊ ሚደያ ገጾቿ ላይ ስለ ጦርነቱ እንዳታወራ አስቀድሞ ተነግሯት ነበር ሲል ተከተራክሯል።

አክሎም የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፉ የተቋሙን ኢዲቶሪያል ፖሊሲ ይጥሳል ሲል አስረድቷል።

ራንጊያህ በመጀመርያው ውሳኔያቸው ላይ ጋዜጠኛዋ እንደዚያ ዓይነት ይዘት ያላቸው ልጥፎችን እንዳታጋራ እንዳልተነገራት ገልጸዋል።

አክለውም የኢንስታግራም ገጿ "ተገቢው ምክር ያልተሰጠበት" ቢሆንም ፖሊሲዎችን ጥሳለች በሚል "ጥርጣሬ ብቻ እንድትባረር" ተደርጋለች፤ በርግጥ ፖሊሲዎችን እና መመሪያዎችን ጥሳ "ሊሆን ይችላል" ግን ራሷን የመከላከል መብት አልተሰጣትም ብለዋል።

ጋዜጠኛዋ ከሥራዋ እንድትባረር ለእስራኤል ውግንና ባላቸው አካላት "የተቀነባበረ" ዘመቻ ተከፍቶ ነበር። እናም ኤቢሲ የቀረበበትን ትችት ለመመከት "መስዋዕት" አድርጓታል ሲሉ ረቡዕ ዕለት ዳኛ ራንገያህ ተናግረዋል።

"ኤቢሲ እና ሌሎች ትችትን ለመሸሽ ቅጣትን እንደ ተገቢ ዋጋ እንዲቀበሉት መፍቀድ የለብንም" ብለዋል።

አክለውም ኤቢሲ አድማጩን እና ሠራተኞቹን ይቅርታ በመጠየቁ ትንሽም ቢሆን መጸጸቱን አሳይቷል ያሉት ዳኛው የላቶፍን መረጃ ለመገናኛ ብዙኃን ያሾለከውን ግለሰብ መመርመር ላይ ግን ሳይችል ቀርቷል ብለዋል።

ኤቢሲ የተጣለበትን ቅጣት በ28 ቀናት ውስጥ እንዲከፍል ተወስኖበታል።