ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከኢትዮጵያ እስከ አርጀንቲና - ሩሲያ የምዕራባውያንን ተጽዕኖ ለማሸነፍ የምትሞክርባቸው መገናኛ ብዙኃን
ሃቪየር ጋላርዶ በቴሌቪዥን የሚተላለፍ የክላሲካል የሙዚቃ ፕሮግራም በማየት ቀኑን መጀመር የሚያስደስተው የዘውትር ልማዱ ነው። የከባድ መኪና የማሽከርከር ስራውን ከመጀመሩ አስቀድሞ ይህንን አይነት ሙዚቃ መስማት ስሜቱን ያስተካክለዋል።
በሰኔ ወር አንድ ሰኞ ቴሌቪዥኑን ሲከፍት የተመለከተው ግን ከዚህ ቀደም የለመደው አልነበረም።
ቴሌቪዥን ጣቢያው በሙዚቃ ፋንታ የጦርነት ምስሎች እያሰራጨ ነበር። ቴሌቪዥን ጣቢያው የሚተላለፈው ዘገባ ከዚህ ፈጽሞ ሰምቶ የማያውቀው አይነት ነበር።
"የተፈጠረው ምንድን ነው?" ብሎ ራሱን ጠየቀ። ከ20 ደቂቃ በኋላ ቴሌቪዥኑን አጠፋው። እየተላለፈ ከነበረው ስርጭት ጋር ሊግባባ እንዳልቻለ ይናገራል።
በቴሌቪዥኑ የታችኛው ጥግ ላይ በአረንጓዴ ቀለም የተጻፉ "አር ቲ" (RT) የሚሉ ሁለት ቃላቶችን ተመልክቷል።
"አር ቲ" የሩስያ ቴሌቪዥን ቻናል መሆኑን የተገነዘበው ኢንተርኔት ላይ መረጃ ለማግኘት ከሞከረ በኋላ ነበር።
ሃቪየር የሚኖረው ቺሊ ውስጥ ነው። በቴሌቪዥን ያየው ዘገባ የተላለፈው የግል ጣቢያ የሆነው 'ቴሌካናል' የስርጭት መስመሩን በሩስያ መንግሥት ድጋፍ ለሚደረግለት እና ከዚህ ቀደም "ራሺያን ቱዴይ" ተብሎ ይጠራ ለነበረው አር ቲ አሳልፎ ከሰጠ በኋላ እንደሆነ ተገልጿል።
የአገሪቱ የብሮድካስት ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት፤ የብሮድካስቲንግ ሕግን ጥሷል ባለው ቴሌካናል ላይ ቅጣት ለመጣል የቴሌቪዥን ጣቢያውን ምላሽ እየተጠባበቀ ነው።
ቴሌካናል በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
በዚህ ሁሉ መሃል የጣቢያው ተመልካቾች ግራ ተጋብተዋል።
ሃቪየር "በጣም ተናድጄ ነበር" ሲል በወቅቱ የተሰማውን ይገልጻል። "ምንም ነገር አስቀድመው አልተናገሩም፤ ለምን ይህ እንደተደረገ አልገባኝም" በማለትም ቅር መሰኘቱን ያክላል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት የሩሲያ መንግሥት የሚደግፋቸው የዜና አውታሩ አር ቲ እንዲሁም የዜና ወኪል እና ሬዲዮ ጣቢያ የሆነው ስፑትኒክ ዓለም አቀፍ ተደራሽነታቸውን አስፋፍተዋል።
በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ፣ በባልካን፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በደቡብ ምሥራቅ እስያ እና በላቲን አሜሪካ ስርጭታቸውን እያስተላለፉ ይገኛሉ።
ይህ የሩሲያው መገናኛ ብዙኃን አካሄድ ምዕራባውያን አገራት ከጣሉት እገዳ ጋር የሚያያዝ ነው።
ሩሲያ በየካቲት 2022 ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ ከወረረች በኋላ አር ቲ በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ፣ በካናዳ እና በመላው አውሮፓ ኅብረት ሲያስተላልፋቸው የነበሩ ስርጭቶች ታግደዋል። ትላልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችም ስለ ጦርነቱ የተሳሳተ መረጃ እያሰራጨ ነው በሚል እገዳ ጥለውበታል።
በመገናኛ ብዙኃኑ ላይ የሚጣለው እገዳ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው ባለፈው ዓመት ነበር።
አሜሪካ በ2024 ሕዝብ አገሪቱ ተቋማት ላይ ያለውን "አመኔታን" ለመጉዳት ሙከራ አድርገዋል ባለቻቸው እንደ የአር ቲ ዋና አዘጋጅዋ ማርጋሪታ ሲሞኒያንን ያሉ የጣቢያው አመራሮች ላይ ማዕቀብ ጥላለች።
አሜሪካ ይህንን እርምጃ የወሰደችው፤ ክሬምሊን በፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ላይ ጣልቃ ለመግባት በማሰብ የተቀናጀ ሰፊ ዘመቻ አካሂዷል የሚል ክስ ካቀረበች በኋላ ነው።
አር ቲ በዚህ ጉዳይ ውስጥ አለው የተባለውን ተሳትፎ አስተባብሏል።
በሌሎች አካባቢዎች ግን የአር ቲ ተጽዕኖ እየተስፋፋ መጥቷል።
አር ቲ ከ2023 ጀምሮ አልጄሪያ ውስጥ ቢሮ ከፍቷል፣ በሰርቢያ ቋንቋ ደግሞ የቴሌቪዥን ስርጭት ጀምሯል። ከአፍሪካ፣ ከደቡብ ምሥራቅ እስያ፣ ከሕንድ እና ከቻይና የተውጣጡ ጋዜጠኞች ላይ ትኩረት ያደረጉ ነጻ የስልጠና ፕሮግራሞችን አስጀምሯል።
ሕንድ ውስጥም ቢሮ እንደሚከፍት አስታውቋል። ስፑትኒክ የካቲት ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ያቋቋመውን የዜና ክፍል ክፍል ስራ አስጀምሯል።
አር ቲ ከብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያው ኢቢሲ ጋር በጋራ ለመስራትም ስምምነት ፈጽሟል።
ጥቅምት ወር ላይ አር ቲ የአፍሪካ ዲፓርትመንት ዋና ኃላፊ ሺያቶስላቭ ሼግሌቭ ኢቢሲን በጎበኙበት ወቅት "ሁለቱ ሚዲያዎች ይዘት እንዲለዋወጡ" ተስማምተው ነበር።
የልምድ ልውውጥ እና አር ቲ የሚሰጥ "የአቅም ግንባታ" ስልጠናም የስምምነቱ አካል ነበሩ። በግንቦት ወር መጨረሻም ሁለቱ መገናኛ ብዙኃን "በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት" ተፈራርመዋል።
ሌላኛው የሩስያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን 'ስፑትኒክ' ደግሞ የካቲት ላይ የአፍሪካ ቢሮውን አዲስ አበባ ውስጥ ከፍቷል።
በቢሮው መክፈቻ ስርዓት ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የተገኙ ሲሆን የሩሲያ ፌዴሬሽን ፌዴራል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቫለንቲና ማትቪዬንኮም ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው ነበር።
በመዲናዋ የተከፈተው ስፑትኒክ አፍሪካ "የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥት ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት የሚያስከብር የኤዲቶሪያል ፖሊሲ" እንዳለው ተዘግቦ ነበር።
ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኞችን የቀጠረው መገናኛ ብዙኃኑ፤ ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ በከፈተው የቴሌግራም ቻናል መረጃዎችን እያቀረበ ይገኛል።
የሩስያ መገናኛ ብዙኃን መስፋፋት፤ ምዕራባውያን ሚዲያዎች በአንዳንድ ቀጣናዎች እየታየባቸው ካለው መዳከም ጋር የሚያያዝ ነው።
የተወሰኑ ምዕራባውያን የዜና ማሰራጫዎች በበጀት ቅነሳ ምክንያት እና የአገራቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መቀየር የተነሳ ተደራሽነታቸውን የቀነሱ ሲሆን አንዳንዶቹም በተወሰኑ የዓለም ክፍሎች የነበራቸውን እንቅስቃሴ አቋርጠዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት ቢቢሲ ፊቱን ወደ ዲጂታል አገልግሎት በማዞር የአረብኛ የሬዲዮ ስርጭቱን ዘግቷል። ከዚያ ጊዜ በኋላ ግን የጋዛ እና የሱዳን ጉዳዮችን የሚዘግቡ የአደጋ ጊዜ የሬዲዮ አገልግሎቶችን ጀምሯል።
በዚሁ ተመሳሳይ ዓመት የሩሲያው ስፑትኒክ በሊባኖስ 24 ሰዓት አገልግሎት መስጠት የጀመረው፤ ቢቢሲ አረብኛ ይሰራጭበት የነበረውን የአየር ሞገድ በመጠቀም ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሜሪካ መንግሥት የሚደገፈው ዓለም አቀፍ የብሮድካስት አገልግሎት አሜሪካ ድምጽ (ቪኦኤ) አብዛኛዎቹን ሠራተኞቹን ቀንሷል።
በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ካትሪን ስቶነር "ሩሲያ እንደ ውሃ ናት፤ በሲሚንቶ ውስጥ ስንጥቅ ካለ ወደ ውስጥ ትገባለች" ሲሉ አካሄዱን አነጻጽረው ያቀርቡታል።
ይሁን እንጂ አሁንም የሚነሳው ጥያቄ፤ የሩሲያ የጨዋታ ግብ ምንድን ነው? የሚለው ነው።
የዓለም ስርዓት እየተቀየረ ባለበት በዚህ ጊዜ የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን በእነዚህ ቀጠናዎች ያላቸው ኃይል እየጨመረ መምጣቱስ ምንን ያመለክታል?
ተመልካቾቹ በሙሉ "በሴራ ትንታኔ" የናወዙ አይደሉም
በማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ የሩሲያ ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ስቲቨን ሀቺንግስ፤ "[የምዕራቡ ዓለም አካል ያልሆኑ አገራት] ባላቸው ፀረ አሜሪካ፣ ፀረ ምዕራባውያን እና ፀረ ኢምፔሪያሊዝ ስሜት የተነሳ በእውቀት፣ በባህል እና በርዕዮተ ዓለም ምቹ ለም መሬት ናቸው" ይላሉ።
የሩሲያ ፕሮፓጋንዳም ብልጠት የተሞላበት አካሄድ ይከተላል በማለትም ይከራከራሉ። የሚቀርበው ይዘት ለተወሰነ ታዳሚ ተብሎ የተቀረጸ ነው። በተለያዩ ቀጠናዎች የተለያዩ ርዕዮተ ዓለማዊ አቋሞችን ሊይዙ እንደሚችሉም ይገልጻሉ።
አር ቲን በተመለከተ ያለውን አመለካከት እናንሳ። በምዕራቡ ዓለም ብዙውን ጊዜ የሚቆጠረው እንደ "የሩሲያ መንግሥት አካል እና የሀሰት መረጃ አሰራጭ" ነው። በሌሎች የዓለም ክፍሎች ግን ብዙውን ጊዜ የሚታየው የራሱ ኤዲቶሪያል መመሪያ እንዳለው ብሮድካስተር ነው።
ይህ ዕይታ ደግሞ የተመልካቾችን አመኔታ ለማግኘት አመቺ ያደርገዋል። መገናኛ ብዙኃኑን የሚከታተሉ በሙሉ "በቀላሉ በሀሰተኛ መረጃ የሚጠለፉ የሴራ ተንታኞች አይደሉም" ይላሉ።
በግላስጎው ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ዶ/ር ራይስ ክሪሌይ ደግሞ የአር ቲ ዘገባዎች ሰፊ ተመልካች የሚያገኙት ምዕራባውያን ላይ ካለው ምልከታ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ይጠቁማሉ።
"በዓለም አቀፍ ደረጃ የፍትህ መጓደል ወይም የተለያዩ ክስተቶች የሚያሳስባቸው ሰዎች የሚረዱት [በእነዚህ ጉዳዮች ውስጥ] ምዕራባውያን ተሳታፊ እንደሆነ ነው" ሲሉም ሀሳባቸውን ያብራራሉ።
"ጥንቃቄ የተሞላበት ማጭበርበር"
የአር ቲ ዓለም አቀፍ ድረ ገጽ እንዲሁ ሲታይ መደበኛ ዜና የሚያቀርብ ገጽ ይመስላል፤ "አንዳንድ" ዘገባዎችንም በትክክል ያቀርባል።
በኦፕን ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ እና ዓለም አቀፍ ጥናቶች መምህር የሆኑት ዶ/ር ፕሪሺየስ ቻተርጄ ዶዲ፤ "በጣም ጥንቃቄ የተሞላበት ማጭበርበር ነው" ይላሉ።
ዶ/ር ፕሪሺየስ ከሌሎች ሁለት አጥኚዎች ጋር በመሆን አር ቲን የተመለከተ መጽሐፍ አሳትመዋል። ጥናቱን ሲያዘጋጁም ከግንቦት 2017 እስከ ግንቦት 2019 ባለው የሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የተላለፉ የአር ቲ የዓለም አቀፍ ዘገባዎችን ተንትነዋል።
ይህ ትንተናቸው፤ የሚዘገቡ ጉዳዮች መረጣ እና የሚዘገቡበት መንገድ አንድ ትርክትን ለመሙላት ያለመ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ አድርሷቸዋል።
የተመራማሪዎቹ ግኝት እንደሚያመለክተው ለምሳሌ፤ በአውሮፓ አገራት የሚከሰት የሕዝብ አለመረጋጋት የሚዘገበው ቅድሚያ ተሰጥቶት ነው።
የሩስያን የአገር ውስጥ ጉዳዮች በተመለከተ ደግሞ በተደጋጋሚ ለዘገባ የሚመረጠው የአገሪቱ ሠራዊት ወታደራዊ ልምምድ ነው።
የቴሌቪዥን ጣቢያው ሀሰተኛ መረጃዎችን ያሰራጨባቸው ጊዜያትም ነበሩ። ሩስያ በ2014 የፈጸመችውን የክሬሚያ ግንጠላ ሰላማዊ "መልሶ መዋሃድ" ብሎ በማቅረብ የሠራዊቱ ተሳትፎ እንደነበረ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ይክዳል።
ዩክሬን ላይ ወረራ ከተካሄደበት 2022 ጀምሮም ሩሲያ ወታደሮች የፈጸሟቸውን የጦር ወንጀሎች የሚያሳዩ ማስረጃዎችን በስልታዊ መንገድ አስተባብሏል።
ሩስያ እንደ አዲስ ትኩረቷን አፍሪካ ላይ ያደረገችው ለምንድን ነው?
በማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ የሩሲያ ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ስቲቨን ሀቺንግስ እንደሚናገሩት የሩሲያ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በቅርቡ ትልቅ መስፋፋት ያደረጉት በአፍሪካ ውስጥ ነው።
የካቲት ላይ የሩሲያ ባለስልጣናት በአዲስ አበባ የተከፈተውን የስፑትኒክ ቢሮ በይፋ ስራ ለማስጀመር ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው ነበር።
የስፑትኒክ የአፍሪካ ክፍል ከዚህ ቀደም በእንግሊዝኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ስርጭቱን ሲያስተላልፍ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ አማርኛን አገልግሎት ከሚሰጥባቸው ቋንቋዎች አንዱ አድርጎታል።
የአር ቲ ዋና አዘጋጅ እንደምትናገረው ጣቢያው የፈረንሳይኛ ቋንቋ ስርጭቱ ትኩረቱን ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ወደ ሆኑ የአፍሪካ አገራት አዙሯል። ለለንደን፣ ፓሪስ፣ በርሊን እና አሜሪካ ፕሮጀክቶች ተመድቦ የነበረ ገንዘብንም ወደ አፍሪካ እያዘዋወረ ይገኛል።
አር ቲ በአፍሪካ ሰባት ቢሮዎች እንዳሉት የሩሲያ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ባለፈው ዓመት ዘግቦ ነበር። ይህ መረጃ ግን በገለልተኛ አካል አልተረጋገጠም።
ብዙ አፍሪካውያን ቀድሞውንም ለሩሲያ ቀና አመለካከት አላቸው። ፀረ ቅኝ ግዛት እና ፀር ኢምፔሪያሊስት ስሜቶች፤ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የሶቪየት ኅብረት ለነፃነት እንቅስቃሴዎች ከነበራት ድጋፍ ጋር ተዳምሮ ብዙዎቹ አፍሪካውያን ስለ ሩሲያ ያላቸው አመለካከት ወዳጃዊ እንዲሆን አድርጓል።
ሩሲያ ይህንን አዲስ ትኩረት፤ በአፍሪካ የምዕራባውያንን ተጽዕኖ ለማዳከም፣ ለእርምጃዎቿ ድጋፍ ለመፍጠር እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመገንባት እንደምትጠቀምበት ዶክተር ክሪሊ ይናገራሉ።
የአፍሪካውያን ጋዜጠኞች ምልከታም ከዚሁ ጋር የሚጣጣም ነው። አንዳንድ ጋዜጠኞች አር ቲ እንደ ሲኤንኤን ወይም አልጀዚራ ዓይነት መደበኛ ዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው ብለው እንደሚያምኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቃለ መጠይቅ የተደረገለት አንድ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ፤ በተባበሩት መንግስታት ጭምር ማስረጃ የቀረበበትን በዩክሬን ቡቻ ከተማ በሩሲያ ኃይሎች የተፈጸመ የንጹኃን ጅምላ ግድያን "የተቀነባበረ ክስተት" ሲል ጠርቶታል። የማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ፕሮፋይል ምስልም የፑቲን ምስል ነበር።
ሌላ የሴራ ሊዮን ጋዜጠኛ ደግሞ የተሳሳተ እና ሀሰተኛ መረጃ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ቢገነዘብም፤ እያንዳንዱ የመገናኛ ብዙሃኃን የራሱ የሆነ "የዜና ምዘና እና አዘጋገብ ዘዴ" እንዳለው ተናግሯል።
ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ ላቲን አሜሪካ
በመካከለኛው ምሥራቅ እንደ አር ቲ አረብኛ እና ስፑትኒክ አረብኛ ያሉ የሩሲያ መንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃን፤ የእስራኤል እና የጋዛ ጦርነትን የሚዘግቡት የፍልስጤም ደጋፊ ለሆኑ ተመልካቾቻቸው እንደሆነ ፕሮፌሰር ሀቺንግስ ገልጸዋል።
አር ቲ ላቲን አሜሪካን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች ተደራሽነቱን ለማስፋት እየሞከረ ነው።
የመገናኛ ብዙኃኑ በድረ ገጽ እንደሚያስረዳው ጣቢያው በቀጠናው ባሉ 10 አገሮች በነፃ እየተላለፈ ይገኛል። ከእነዚህ አገራት መካከል አርጀንቲና፣ ሜክሲኮ እና ቬንዙዌላ ይገኙበታል። በተጨማሪም በ10 ሌሎች አገራት የኬብል ቴሌቪዥን ስርጭቶች አሉት።
በዓለም አቀፍ ዜናን በስፓኒሽ ቋንቋ በነጻ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ማሰራጨቱ "ከስኬቶቹ አንዱ" እንደሆነ የኩባ እና ሜክሲኮ ዘር ሀረግ ያላቸው የታሪክ ጸሐፊ እና የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪ ዶ/ር አርማንዶ ቻጉዋሴዳ ይናገራሉ።
አር ቲ በዓለም ዙሪያ ከዩቲዩብ ቢታገድም፤ ከመጋቢት 2022 ጀምሮ በአንዳንድ አካባቢዎች ወደ ቪድዮ ማሰራጫ መድረኩ እየገባ ነው።
አርጀንቲና ውስጥ የ52 ዓመቱ አኒባል ባይጎሪያ የአር ቲ ዘገባዎችን ከቴሌቪዥን በመቅዳት በዩቲዩብ ቻናሉ ላይ ይለጥፋቸዋል።
"ቦነስ አይረስ ውስጥ የዜና ዘገባዎች በብዛት የሚያተኩሩት ከተማዋ ላይ ብቻ ነው" በማለት ይከራከራል። "አር ቲ በላቲን አሜሪካ ያሉ ሌሎች አገራት [ምን እየተካሄደ እንዳለ] እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ዜናዎችን ያቀርባል" ሲልም ያስረዳል።
"እያንዳንዱ ሰው እውነት ነው ብሎ የሚያምንበትን ነገር የመወሰን መብት አለው" ሲሉም አቋሙን ይገልጻል።