ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቢቢሲ ዋና ዳይሬክተር እና የዜና ሥራ አስፈፃሚ በትራምፕ ዙሪያ በተሰራ ዘጋቢ ፊልም ምክንያት ሥራቸውን ለቀቁ
የቢቢሲ ዋና ዳይሬክተር ቲም ዴቪ እና የዜና ኃላፊዋ ዴብራ ተርነስ በዶናልድ ትራምፕ ዙሪያ በተሰራ ዘጋቢ ፊልም ንግግር በመቆራረጥ ትችት ከደረሰባቸው በኋላ ሥራቸውን በፈቃዳቸው ለቀዋል።
ለአምስት ዓመታት በኃላፊነት የቆዩት ዋና ዳይሬክተሩ ዴቪ በበርካታ ውዝግቦች እና የአድሏዊ ክሶች ጫና በርትቶባቸው ነበር።
ዘ ቴሌግራፍ ባለፈው ሰኞ ሾልኮ የወጣ ውስጣዊ ማስታወሻ ዝርዝርን ያተመ ሲሆን፤ ዘገባው ሁለት የፕሬዝዳንት ትራምፕ ንግግሮችን ቆርጦ በመቀጠል የ2021ን የካፒቶል ሂል አመፅ እንደደገፉ አድርጎ ማሳየቱን ጠቁሟል።
የዩናይትድ ኪንግደም የፖለቲካ መሪዎች የሥራ መልቀቅ ዜናውን ለውጥ ለማምጣት መንገድ ይመራል የሚል ተስፋ ሲይዙ፤ ትራምፕ ደግሞ ውሳኔውን ተቀብለዋል።
የቢቢሲ ዋና ዳይሬክተሩ እና የዜና ሥራ አስፈፃሚ በአንድ ቀን ስራ መልቀቃቸው ታይቶ የሚታወቅ አይደለም።
ውሳኔያቸውን እሁድ ምሽት ያሳወቁት ቲም ዴቪ "እንደ ሁሉም የሕዝብ ድርጅቶች ሁሉ ቢቢሲም ፍፁም አይደለም። ሁሌም ቢሆን በራችን ክፍት፣ ግልፅ እና ተጠያቂ መሆን አለብን" ብለዋል።
"ይሄ ብቸኛው ምክንያት ባይሆንም ወቅታዊው የቢቢሲ ኒውስ ውዝግብ ለውሳኔዬ አስተዋፅኦ አድርጓል" ሲሉ አክለዋል።
"በአጠቃላይ ቢቢሲ ጥሩ እየሰራ ነው፤ ነገር ግን አንዳንድ ስህተቶች ተሰርተዋል እናም እንደ ሥራ አስኪያጅነቴ ትልቁን ኃላፊነት እኔ መውሰድ አለብኝ።"
የዜና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ዴብራ ተርነስ እሁድ ባወጡት መግለጫ በዘጋቢ ፊልሙ ዙሪያ የተነሳው ውዝግብ "ቢቢሲ ላይ ጉዳት የማድረስ ደረጃ ላይ ደርሷል" ያሉ ሲሆን፤ "ጫናው እኔ ጋር ይቆማል" ብለዋል።
"በሕዝባዊ ሕይወት መሪዎች ሙሉ ለሙሉ ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው። እናም ለዚህ ነው ሥራዬን የምለቀው። ስህተቶች ቢሰሩም እንኳ ግልፅ ማድረግ የምፈልገው ቢቢሲ እንደ ተቋም አድሏዊ ነው የሚለው ከእውነት የራቀ ነው" ሲሉም አክለዋል።
ዴብራ ተርነስ ባለፉት ሦስት ዓመታት የቢቢሲ ዜና እና ወቅታዊ ጉዳዮች ሥራ አስፈፃሚ ነበሩ።
በቴሌግራፍ የታተመው የውስጥ ማስታወሻ በእስራኤል ጋዛ ጦርነት የቢቢሲ አረበኛ ሽፋን "ስልታዊ ችግር" ተብሎ የተገለፀውን ለመፍታት እርምጃ አለመወሰዱ አሳሳቢነቱን ከፍ ያደረገ ነው።
ዋሽንግተን ዲሲ እ.አ.አ ጥር 6/2021 ትራምፕ ባደጉት ንግግር "ወደ ካፒቶል ሂል እንራመዳለን፤ እና ጠንካራ ሴናተሮቻችንን እና የምክር ቤት አባሎቻችንን እና ሴቶቻችንን እናበረታታለን" ይላሉ።
ነገር ግን በዘጋቢ ፊልሙ የታየው "ወደ ካፒቶል እንራመዳለን. . .እናም ከእናንተ ጋር እዚያው እገኛለሁ። እናም እንፋለማለን። እስከ መጨረሻው ድረስ እንፋለማለን።"
ከተለያየ ቦታ ተቆርጠው የተቀጠሉት ሁለቱ ክፍሎች በመካከላቸው የ50 ደቂቃ ክፍተት አላቸው።
የውስጥ ማስታወሻው ከታተመ በኋላ "መቶ በመቶ የውሸት ዜና" ብሎ ኮርፖሬሽኑን የገለፀው ዋይት ሐውስን ጨምሮ ቢቢሲ ላይ ትችት ተነስቷል።
ትራምፕ የሥራ መልቀቂያውን በተመለከተ የቢቢሲ ሰዎች እየለቀቁ ወይም እየተባረሩ ያሉት "የጥር 6 በጣም ምርጥ ንግግሬን በመቆራረጣቸው ተይዘው ነው" ብለዋል።
"እነዚህ ውሸታም ሰዎች በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ላይ ራሳቸውን ከፍ ለማድረግ የሞከሩ ናቸው" ያሉት ትራምፕ፤ "ለዲሞክራሲ ምን ያህል የሚያሳዝን ሥራ ነው" ብለዋል።
የሁለት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መልቀቅ ዛሬ ሰኞ የቢቢሲ ሊቀ መንበር ሳሚር ሳህ በፓርላማ ኮሚቴ ከመቅረባቸው በፊት የመጣ ነው።
በሥራ መልቀቂያው ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ሊቀ መንበሩ፤ "ለቢቢሲ የሀዘን ቀን" ያሉ ሲሆን ቲም ዴቪ በሥራ ቆይታው "ከእኔ እና [ከቢቢሲ] ቦርዱ ሙሉ ድጋፍ ነበረው" ብለዋል።
"ይሁን እንጂ በግልም በሙያም የበረታበትን ግፊት እረዳለሁ፤ ለዛሬው ውሳኔ አድርሶታል፤ ሁሉም የቦርድ አባላት ውሳኔውን እና የውሳኔውን ምክንያት ያከብራል" ሲሉ አክለዋል።