የአሜሪካ ፍርድ ቤት 'የ9/11 ጥቃት አቀናባሪዎች' የፍርድ ማቅለያ ስምምነትን ውድቅ አደረገ

የአሜሪካ የፌደራል ይግባኝ ፍርድ ቤት በአገሪቱ የተፈጸመውን የ9/11 ጥቃት በማቀናበር የተከሰሱት ካሊድ ሼክ መሐመድ እና ሌሎች ተከሳሾች የፍርድ ማቅለያ ስምምነትን ውድቅ አደረገ።

ካሊድ ሼክ መሃመድ እና ሌሎች ሁለት ተከሳሾች የሞት ፍርድ እንዳይፈረድባቸው ለማስቀረት፤በምትኩ የተከሰሱባቸውን ወንጀሎች በሙሉ አምነው ለመቀበል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

የይግባኝ ፍርድ ቤቱ ተከፋፍሎ ነበር የተባለ ሲሆን፤ ጥቃቱን ያቀናበሩት ግለሰቦችን በጽኑ የእድሜ ልክ እስራት የሚያስቀጣውን ስምምነት የዋሽንግተን ዳኞች 2ለ1 በሆነ ድምጽ ውድቅ አድርገውታል።

መሐመድ በአውሮፓውያኑ መስከረም 11፣ 2001 የመንገደኞች አውሮፕላን ጠለፋን በማቀነባበር እና በመምራት ተከሷል።

የተጠለፈው አውሮፕላን በኒውዮርክ የዓለም ንግድ ማዕከል እና ከዋሽንግተን ወጣ ብሎ በሚገኘው ፔንታጎን ላይ ተከስክሶ 3 ሺህ ያህል ሰዎች ሞተዋል።

ሌላኛው አውሮፕላን ውስጥ አንድ መንገደኛ በመታገላቸው በፔንስልቫንያ በሚገኝ ሜዳ ላይ ተከስክሷል።

ይህንን ጥቃት በማቀናበር ክስ የተመሰረተባቸው ሶስቱ ግለሰቦች ከ20 ዓመት በላይ በአሜሪካ በእስር ላይ ቆይተዋል። የቅድመ ችሎት ሰሚም ከአስር ዓመት በላይ ቆይቷል።

በዚህ ወቅትም ሶስቱ ግለሰቦች ጥፋተኛ ነን ብለው ያመኑት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በሲአይኤ ለረጅም ጊዜ በደረሰባቸው የከፋ ማሰቃየት በኋላ ነው የሚሉ ክርክሮች ተሰምተዋል።

በአውሮፓውያኑ 2003 በቁጥጥር ስር የዋለው መሃመድ በሚስጥራዊ የሲአይቤት ከታሰረ በኋላ 183 ጊዜ ያህል በውሃ እንዲሰጥም እና እንዲታፈን የማድረግ ስቃይ ተፈጽሞበታል።

እሱን ጨምሮ ሌሎች ደግሞ እርቃናቸውን ማጋለጥ ጨምሮ፣ እንቅልፍ ማሳጣት እና ሌሎች "የረቀቁ የምርመራ ዘዴዎች" ተግባራዊ ሆኖባቸዋል ተብሏል።

በአሁኑ ወቅት መሐመድን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾች በኩባ፣ ጓንታናሞ ቤት በአሜሪካ እስር ቤት ይገኛሉ።

በስምምነቱ መሰረት በ9/11 ጥቃት ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ግለሰቦች ለመሐመድ ጥያቄ እንዲያቀርቡ የሚፈቀድላቸው ሲሆን እሱም "ጥያቄዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ እውነተኛ በሆነ መልኩ እንዲመልስ" ይጠበቅበት እንደነበር ጠበቆች ተናግረዋል።

ተጎጂ ቤተሰቦች በስምምነቱ መከፋፈል እንደታየባቸው የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘግቧል።

ስምምነቱን የተቃወሙ ሰዎች የፍርድ ሂደቱ ስለ ጥቃቱ የበለጠ መረጃ ለማግኘት እንዲሁም ለፍትህ የተሻለ መንገድ እንደሆነ ያምናሉ።

ስምምነቱን የደገፉ በበኩላቸው ይህንን ለረጅም ዘመናት የቆየውን ፈታኝ ምዕራፍ መቋጫ ነው ይላሉ።

የፍርድ ማቅለያ ስምምነቱ ሁለት ዓመት በወሰደ ድርድር የተደረሰ ሲሆን ወታደራዊ አቃብያነ ህግ እና በጓንታናሞ ቤይ ከፍተኛ የፔንታጎን ባለስልጣን የጸደቀ ነው።

በቅድመ ችሎት ከአስር ዓመታት በላይ የቆዩት መሐመድ እና ሌሎች ተከሳሾች በአሜሪካ እና በጓንታናሞ ቤይ እንግልት እና ስቅይት በከፍተኛ ሁኔታ የተፈጸመባቸው ከመሆኑ አንጻር ከተከሳሾቹ የተገኙ መረጃዎችን ያወሳሰቡ እና ጥያቄዎች ያጫሩ ሆነዋል።

ባለፈው ዓመት የባይደን አስተዳደር ከመሐመድ እና ሌሎች ሶስት ተከሳሾች ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን አስታውቆ ነበር።

ነገር ግን የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን ከሁለት ቀናት በኋላ እንዲህ አይነት ስምምነት ውስጥ የመግባት ስልጣን ያላቸው እሳቸው መሆናቸውን ጠቅሰው ሽረውት ነበር።

ነገር ግን ወታደራዊ ፍርድ ቤት ሚኒስትሩ ያሳለፉትን ውሳኔ ውድቅ አድርጎ ይህንን የፍርድ ማቃለያ ስምምነት መልሶት ነበር።

ነገር ግን አርብ ዕለት የፌደራሉ ይግባኝ ፍርድ ቤት ቤተሰቦች እና የአሜሪካ ህዝብ የወታደራዊ ፍርድ ሂደትን የማየት እድል ሊሰጣቸው ይገባቸዋል በሚል ውሳኔ አሳልፈዋል።