በእስራኤል ኤምባሲ ጥቃት ላይ ኢራን እጇ ሳይኖርበት አይቀርም ስትል ስዊድን ከሰሰች

ሳፖ የተባለው የስዊድን ደኅንነት መሥሪያ ቤት በእስራኤል ኤምባሲ አቅራቢያ በተፈጸመው ፍንዳታ የኢራን እጅ ሳይኖበት አይቀርም ሲል ከሰሰ።

በዚህ ሳምንት መባቻ ስቶክሆልም እና ኮፐንሀገን በሚገኙ የእስራኤል ኤምባሲዎች አቅራቢያ ፍንዳታ እና የተኩስ ለውውጥ ተሰምቶ ነበር።

የሳፖ ኃላፊ ፍሬድሪክ ሀልስቶርም እንዳሉት የፍንዳታው ዓላማ እና ጥቅም ላይ የዋለው መንገድ የኢራን እጅ እንዳለበት ይጠቁማል ብለው “ነገር ግን ይህ ጥርጣሬ እንጂ የተጨበጠ ማስረጃ የለንም” ሲሉ አክለዋል።

ባለፈው ሰኞ ስቶክሆልም በሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ የተኩስ ልውውጥ ድምፅ ቢሰማም ሰው ላይ ጉዳት አልደረሰም።

ረቡዕ ጥዋት ደግሞ በዴንማርክ ዋና ከተማ ኮፐንሀገን ማዕከላዊ ክፍል ውስጥ በሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ አቅራቢያ ሁለት ፍንዳታዎች ተሰምተዋል።

በተመሳሳይ ቀን ከሰዓት ሁለት የ16 እና 19 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ስዊድናውያን ታዳጊዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። አንደኛው ታዳጊ ወደ አምስተርዳም ለመሄድ የባቡር ቲኬት ገዝቶ ነበር።

ሁለቱ ታዳጊዎች ሐሙስ ዕለት የእጅ ቦምብ በመያዝ እና ኤምባሲው አካባቢ በማፈንዳት ክስ ተመሥርቶባቸዋል።

ታዳጊዎቹ የተመሠረተባቸውን ክስ ያስተባበሉ ሲሆን ፍርድ ቤቱ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 30 ቀጠሮ ሰጥቶ እስከዚያው በቁጥጥር ሥር እንዲቆዩ አዟል።

እስራኤል ኤምባሲ አካባቢው በቁጥጥር ሥር የዋለ ሦስተኛ የስዊድን ዜጋ መለቀቁ ተሰምቷል።

የዴንማርክ ፖሊስ ኮፐንሀገን በደረሰው ፍንዳታ ምክንያት በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች ስለመኖራቸው የገለፀው ነገር የለም።

ባለፈው ጥር ስቶክሆልም በሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ ደጃፍ “አደገኛ ቁስ” ተገኝቶ ከጥቅም ውጪ እንዲሆን መደረጉ ይታወሳል።

የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ኡልፍ ክሪስቴርሰን በእስራኤል ኤምባሲ እና በአይሁዳውያን ተቋማት አካባቢ የሚደረገው ጥበቃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ባለፈው ግንቦት ኤምባሲው አቅራቢያ የተኩስ ድምፅ ተሰምቶ በክስተቱ ተሳትፈዋል የተባሉ ታዳጊዎች በቁጥጥር ሥር ከቆዩ በኋላ መለቀቃቸው አይዘነጋም።

ባሳለፍነው ሳምንት ከተሰሙት ክስተቶች በኋላ የስዊድን ደኅንነት መሥሪያ ቤት የኢራን መንግሥት ስዊድናውያን ወሮበሎችን እየቀጠረ አመፅ እያስፋፋ ነው ሲል ወቅሷል።

መሥሪያ ቤቱ፤ ባለፈው ወር የኢራን ደኅንነት ሰዎች የመልዕክት መለዋወጫውን ጠልፈው ለ15 ሺህ ሰዎች የፅሑፍ መልዕክት ልከዋል ሲል ማስጠንቀቂያ ማውጣቱም ይታወሳል።

ለስዊድናውያን የተላኩት መልዕክቶች በሕዝቡ ዘንድ መከፋፈልን የሚፈጥሩ እና ስዊድንን እንደ እስልምና ጠል አገር የሚስሉ ናቸው ይላል።

ፀረ-እስልምና አቋም ያላቸው ስዊድናውያን የእስልምና ቅዱስ መፅሐፍ (ቁርዐን) ቅጂን ባቃጠሉበት ወቅት ነው የፅሑፍ መልዕክቶቹ የተስፋፉት።

ስቶክሆልም የሚገኘው የኢራን ኤምባሲው ወቀሳዎቹን “ውሀ የማያነሱ” ሲል አስተባብሎ፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነትም እንዲሚጎዳው አስጠንቅቋል።