ፑቲን ጦርነቱን ለማብቃት ፍላጎት እንዳላቸው የቱርኩ ፕሬዝዳንት ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ዩክሬን ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት እንዲያበቃ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፍላጎት እንዳላቸው እንደሚያምኑ ተናገሩ።
ኤርዶዋን በቅርቡ ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ባደረጉት ውይይት የሩሲያው መሪ “በአስቸኳይ ጦርነቱ እንዲቆም” ፍላጎት እንዳላቸው መረዳታቸውን ገልጸዋል።
ከወራት በፊት በሩሲያ የተፈጸመባትን ወረራ ተከትሎ ተይዞባት የነበሩ ግዛቶቿን መልሳ መያዟን ዩክሬን በዚህ ወር አሳውቃለች።
የቱርኩ መሪ እንዳመለከቱት አንዳንድ ነገሮች ለሩሲያ “ችግር ፈጥረዋል” ሲሉ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ባለፈው ሳምንት ኡዝቤክስታን ውስጥ በነበረው ጉባኤ ወቅት ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር “በጣም ሰፊ ውይይት” ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የቱርኩ መሪ ከአሜሪካው ቴሌቪዥን ፒቢኤስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወቅት እንደተናገሩት፣ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲያበቃ ፍላጎት እንዳላቸው መረዳታቸውን አመልክተዋል።
“ነገሮች እየሄዱበት ያለው ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ መሆናቸው ምክንያት ፑቲን ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲያበቃ ፍላጎቱ እንዳላቸው ለመረዳት ችያለሁ” ብለዋል ኤርዶዋን።
ጨምረውም በሁለቱ ተዋጊ ወገኖች መካከል 200 “የታጋቾች” ልውውጥ በቅርቡ ይደረጋል ያሉ ሲሆን፣ በዚህ ውስጥ የትኞቹ አስረኞች እንደሚካተቱ ግን ምንም አይነት ዝርዝር አልሰጡም።
የሩሲያ እና የቱርክ ፕሬዝዳንቶች ባለፈው መስከረም 06/2015 ዓ.ም. የሻንጋይ ትብብር ድርጅት በተባለው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ተገናኝተው ነበር።
ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን የሩሲያን ወረራ ተከትሎ ጦርነቱን እንዲቆም ለማሸማገል በተደጋጋሚ ጠይቀው ነበር። የኔቶ አባል የሆነችው ቱርክ “ሚዛናዊ” አቋም በመያዝ ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ የጣሏቸውን ማዕቀቦች ተቃውመዋል።
ኤርዶዋን ከዩክሬን የእህል ምርት ወደ ቀሪው ዓለም እንዲላክ ለማስቻል በተባበሩት መንግሥታት አማካይነት የተደረሰው ስምምነት ፍሬያማ እንዲሆን አግዘዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሩሲያ ኃይሎች ምሥራቃዊውን የሉሀንስክ ክልልን ሙሉ ለሙሉ ከተቆጣጠሩ ከሁለት ወራት በኋላ ዩክሬን ግዛቷን ማስመለሷን ገልጻለች።
ከጥቂት ሳምንት በፊት ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ምዕራቡ ዓለም ከሩሲያ አንጻር በሚያራምደው “የጸብ ጫሪነት” አቋም ምክንያት ጦርነቱ “በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊቆም አይችልም” በማለት ተናግረው ነበር።
ባለፈው ሳምንት የሩሲያው መሪ የዩክሬኑን ፕሬዝዳንት ለማግኘት ዝግጁ መሆናቸው ቢገልጹም ዜሌንስኪ ግን ፈቃደኛ አልሆኑም። ፑቲን ለሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጦርነቱ “በአስቸኳይ” እንዲበቃ እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር።
ነገር ግን እስካሁን ዩክሬን የሩሲያ ሠራዊት ከአጠቃላይ ግዛቷ እንዲወጣ ያቀረበችው ቅድመ ሁኔታን ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን የሚያመለክት ምንም አይነት ነገር የለም።
ከስምንት ዓመት በፊት በሩሲያ ቁጥጥር ስር የገባችው ክራይሚያ እንዲሁም ፑቲን እያካሄዱት ያለው ወታደራዊ ዘመቻ የዶምባስ ክልልን “ነጻ ማውጣት” መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል። የሉሀንስክ እና የዶምባስ አካባቢዎች በሩሲያ በሚደገፉ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ይገኛል።
የቢፒአስ ቴሌቪዥን ይደረጋል በተባለው የሰላም ድርድር ላይ ከየካቲት ወዲህ ሩሲያ በቁጥጥሯ ስር ያስገባቻቸው የዩክሬን ግዛቶች በይዞታዋ ስር እንዲሆኑ ይፈቅድ እንደሆነ የተጠየቁት ኤርዶዋን፣ ይህ እንደማይሆን አመልክተዋል።
ጨምረውም “ከዩክሬን በወረራ የተያዙ መሬቶች ይመለሱላታል” ያሉ ሲሆን፣ ነገር ግን ይህ በአውሮፓውያኑ 2014 ሩሲያ የያዘችውን ቦታ ይመለከት እንደሆነ ያሉት ነገር የለም።












