ናይጄሪያ በሃገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ የተባለውን ኮኬይን መያዟን ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, NDLEA NIGERIA
የናይጄሪያ የአደንዛዥ ዕጽ ተቆጣጣሪ ድርጅት በሃገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ የተባለለትን ኮኬይን መያዙን ገለጸ።
የተያዘው 1.8 ቶን ኮኬይን ሲሆን 278 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ እንዳለው ተገምቷል። ነደአዕጹ በሰሜን ምስራቅ ሌጎስ ኢኮሮዱ በሚባል አካባቢ በሚገኝ መጋዘን መያዙ ተገልጿል።
አደንዛዥን ዕጹን በ10 ሻንጣዎች እና በ13 ከበሮዎች ውስጥ መከማቸታቸውን ብሔራዊ የመድሃኒት ህግ ማስከበር ኤጀንሲ ገልጿል። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ አራት ናይጄሪያዊያን በሌጎስ የተለያዩ አካባቢዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
አንድ የውጭ ሃገር ዜጋም ተይዟል። ኤጀንሲው ለሁለት ቀናት የተካሄደው "ጥሩ የተቀናጀ እና የስለላ ስራ" መከናወኑን አስታውቋል።
ኤጀንሲው እንዳስታወቀው ግለሰቦቹ አደንዛዥ ዕጹን በአውሮፓ፣ በእስያ እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች ለመሸጥ አቅደው ነበር።
የኤጀንሲው ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል መሐመድ ቡባ ማርዋ ከአሜሪካ አቻዎቻቸው ጋር ዘመቻውን ያከናወኑትን መኮንኖቻቸውን አድንቀዋል።
እንደ ኤጀንሲው መግለጫ “ይህ ለአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች ታሪካዊ ውድቀት ነው። ጨዋታው መቀየሩን ካልተገነዘቡ ሁሉም እንደሚወድቁ የሚያሳይ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ነው" ብሏል።








