ኢትዮጵያ የዓለም ከ20 አመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በታሪኳ ከፍተኛ የተባለውን ውጤት አስመዘገበች

በኮሎምቢያ ካሊ ለስድስት ቀናት ከሐምሌ 25- ሐምሌ 30 2014 ዓ.ም በተካሄደው የዓለም ከ20 አመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ12 ሜዳሊያዎች ከአፍሪካ አንደኛ ከአለም ሶስተኛ ሆና አጠናቀቀች።

ኢትዮጵያ በስድስት ወርቅ፣ በአምስት ብር እና አንድ ነሃስ ሜዳሊያ በአጠቃላይ በ12 ሜዳሊያዎች አሜሪካንና ጃማይካንም ተከትላ ነው በሶስተኛነት ያጠናቀቀችው።

ይህም ውጤት እስከ ዛሬ ከተካሄዱት የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ የተመዘገበ ውጤት ከፍተኛው እንደሆነ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።

 “ዘንድሮ የተመዘገበው ውጤት ከፍተኛው ሲሆን ከተሳተፍንበት ውስን የውድድር ተግባራት አንፃር እጅግ የሚያኮራ ውጤት ነው” ብሏል ፌዴሬሽኑ

በትናንትናው ዕለት በተጠናቀቀው በዚህ ውድድር አሜሪካ በሰባት ወርቅ፣ በአራት ብርና በአራት ነሐስ ሜዳሊያ በ15 ሜዳሊያዎች በአንደኛነት አጠናቃለች።

እሷንም ተከትላ ጃማይካ በስድስት ወርቅ፣ በሰባት ብርና በሶስት ነሃስ በአጠቃላይ 16 ሜዳሊያዎች በማግኘት ከፍተኛውን የሜዳሊያ ቁጥር ብትይዝም በአሜሪካ በወርቅ ተበልጣ በሁለተኛነት አጠናቃለች።

አፍሪካዊቷ አገር ኬንያ ሶስት ወርቅ፣ ሶስት ብርና አራት ነሐስ በማግኘት በአጠቃላይ በአስር ሜዳሊያዎች በአራተኛነት ውድድሩን ማጠናቀቋን ከአለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘው መረጃ ያሳያል።

በዚህ በተካሄደው የዓለም ከ20 አመት በታች አትሌቲክስ የሻምፒዮና ውድድር ላይ ኤርምያስ ግርማ በ800 ሜትር ወርቅ በማግኘት እንዲሁም በ1500 ሜትር ብር በማግኘት የጥምር ሜዳሊያዎች ባለቤት ሆኗል።

በአንድ ሺህ ሜትር የሴቶች ፍጻሜ ውድድር ብርቄ ሃየሎም የሻምፒዮኑንሺፕ ክብረ ወሰን በማሻሻል በአንደኛነት ወርቅ አስመዝግባለች።

ሴት አትሌቶች በደመቁበትና በቅርቡ በተደረገው የኦሪጎን አትሌቲክሽ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በአስር ሜዳሊያዎች በታሪኳ ከፍተኛውን ሜዳሊያ ማስመዝገቧ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በ4ወርቅ፣ በ4ብርና በ2 ነሃስ ከአዘጋጇ አሜሪካ በመቀጠል ከዓለም 2ኛ ደረጃ ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃ በመያዝ ማጠናቀቋ ይታወሳል።

የዓለም ከ20 አመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ወይም የአለም ጁኒየር የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ20 አመት በታች ባሉ አትሌቶች የሚደረግ አለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር ነው።

ባለፈው አመት በነበረው ውድድር ኬንያ በስምንት ወርቅ በአጠቃላይ በአስራ ስድስት ሜዳሊያ በአንደኛነት ነበር ያጠናቀቀችው፣ ኢትዮጵያ በወቅቱ ሶስት ወርቅ፣ ሰባት ብር፣ ሁለት ነሐስ በአጠቃላይ 12 ሜዳሊያ በማግኘት ውድድሩን በአራተኝነት ነበር ማጠናቀቋ ይታወሳል።

በዘንድሮው አመት በ5000 ሜትር ብር ያስገኘችው መልክናት ውድ ባለፈው አመት ሁለት ሜዳልያዎችን አስገኝታ ነበር።

ከ20 አመት በታች ለተደረገው የሻምፒዮንሺፕ ውድድር ኢትዮጵያ 19 አትሌቶችን መላኳን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ የሚያስረዳ ሲሆን በሁለቱም ጾታዎች በአስር አይነት ውድድሮች ተሳትፈዋል።

ወርቅ ያስገኙ አትሌቶች

  • ኤርምያስ ግርማ በ800 ሜትር
  • ብርቄ ሐየሎም በ1500 ሜትር
  • ሳሙኤል ዱግና በ3000ሜትር መሰናክል
  • መልኬነህ አዘዘ በሶስትሺህ ሜትር
  • አዲሱ ይሁኔ በ5000 ሜትር
  • መዲና ኢሳ በ5000 ሜትር

ብር ያስገኙ አትሌቶች

  • ኤርምያስ ግርማ በ1500 ሜትር ብር
  • ፅዮን አበበ በ3000 ሜትር
  • ሲንቦ አለማየሁ በ3000 ሜትር
  • ሳሙኤል ፍሬው በ3000 ሜትር መሰናክል
  • መልክናት ውድ በ5000ሜትር

ነሐስ ያስገኘችው አትሌት

  • መሰረት የሻነህ በ3000 ሜትር ነሃስ

ለስድስት ቀናት በካሉሊ ኮሎምቢያ በተደረገው ውድድር በአጠቃላይ 41 ሃገራት ቢያንስ አንድ ሜዳሊያ ሲያሸንፉ 24 ሃገራት ደግሞ ቢያንስ አንድ ወርቅ ማግኘታቸውን ከአለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።