ቼልሲ ሞይሰስ ካይሴዶን ክብረ-ወሰን በሆነ 115 ሚሊዮን ፓውንድ ለመግዛት ተስማማ

ቼልሲ የብራይተኑን አማካይ ሞይሰስ ካይሴዶ የብሪታኒያ ክብረ-ወሰን በሆነ 115 ሚሊዮን ፓውንድ ለመግዛት ተስማማ።

ባለፈው አርብ ሊቨርፑል ተጫዋቹን በ111 ሚሊዮን ፓውንድ ለማስፈረም ተስማምቶ እንደነበር አይዘነጋም።

ነገር ግን ካይሴዶ ወደ ቼልሲ መሄድ ነው የምሻው ማለቱን ተከትሎ ቼልሲ ተጫዋቹን 115 ሚሊዮን ፓውንድ አውጥቶ ለማስፈረም ወስኗል።

ይህ ማለት ቼልሲ አርጀንቲናዊውን አማካይ ኤንዞ ፈረንናንዴዝ በፈረንጆቹ 2023 በ107 ሚሊዮን ፓውንድ የገዙበትን ክብረ-ወሰን ዋጋ ራሱ ሰብሯል ማለት ነው።

ቅዳሜ ዕለት ብራይተን ከሉተን ታውን የውድድር ዘመኑን መጀመሪያ ጨዋታ ሲያደርግ ካይሴዶ አልተካተተም።

ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ከሽያጩ ዋጋ 100 ሚሊዮን ፓውንድ ቀድሞ የሚከፈል ሲሆን ቀሪው ደግሞ እንደሁኔታዎች የሚከፈል ነው።

ብራይተን በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከ100 ሚሊዮን ፓውንድ ባላነሰ ዋጋ ለመሸጥ ቢወስንም ማንም ይህን ገንዘብ ይከፍላል ብሎ አላሰበም።

ቼልሲ ከዚህ ቀደም ካይሴዶን ለመግዛት 80 ሚሊዮን ፓውንድ አቅርቦ እንደነበር ተገልጧል።

ከሉቶን ታውን ጋር ከነበረው ግጥሚያ በፊት የብራይተን አሠልጣኝ ሮቤርቶ ዲ ዘርቢ ስለካይሴዶ ተጠይቀው “ረስቼዋለሁ” ብለው “ታላላቅ ክለቦች ተጫዋቾቻችንን መግዛት ቢችሉም ነብሳችንን ግን መግዛት አይችሉም” የሚል አስተያየት አክለው ነበር።

ካይሴዶ ከኤኳዶሩ ክለብ ኢንዲፔንዴንቴ ድል ቫሌ ጥር 2021 በ4 ሚሊዮን ፓውንድ ነበር ብራይተንን የተቀላቀለው።

ወጣቱ አማካይ ለብራይተን ቦፕሪሚዬር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰለፈው ሚያዚያ 2022 ነበር።

ካይሴዶ ቼልሲ በያዝነው የክረምት ዝውውር መስኮት ያስፈረመው ስምንተኛው ተጫዋች ሆኗል።

አክስል ዲሳሲ፣ ክሪስቶፈር ንኩንኩ፣ ኒኮላስ ጃክሰን፣ ሌዝሊ ኡጎቹክዉ፣ አንጀሎ ጋብርዔል፣ ሮቤርት ሳንቼዝ እና ዲዬጎ ሞሬራ ሌሎች ለቼልሲ የፈረሙ ተጫዋቾች ናቸው።

አዲሱ የቼልሲ አሠልጣኝ ማሪሲዮ ፖቼቲንሆ ቡድኑን ከመሬት አንስተው ከፍ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ባለፈው የውድድር ዘመን 12ኛ ደረጃን ይዞ ነው ያጠናቀቀው።

ማቴዎች ኮቫቺች፣ ኤድዋርዶ ሜንዲ፣ ካሊዱ ኩሊባሊ፣ ንጎሎ ካንቴ፣ ሜሰን ማውንት፣ ካይ ሃቨርትዝ፣ ክሪስቲያን ፑሊሲች፣ ሩብን ሎፍተስ ቺክ፣ ኢታን አምፓዱ፣ ኦባሜያንግ፣ ራህማን ባባ እና የቀድሞው አምበል ሴዛር አዝፕሊኩዌታ በክረምቱ ዝውውር ቼልሲን የለቀቁ ተጫዋቾች ናቸው።

ቼልሲ በፕሪሚዬር ሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ሊቨርፑልን አስተናግዶ 1-1 ተለያይቷል።