ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፕሪሚዬር ሊግ የመጀመሪያው ሳምንት ሃላንድ ሲደምቅ፤ ኒውካስል ‘አስፈሪ’ መሆኑን አሳይቷል
አርብ ምሽት የተጀመረው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የውድድር ዘመን የአምናው ዋንጫ ባለቤት ማንቸስተር ሲቲ ዘንድሮም አስጊ መሆኑን አሳይቷል።
ከሜዳው ውጭ አዲስ ያደገውን በርንሊ የገጠመው ማንቸስተር ሲቲ 3-0 አሸንፎ ተመልሷል።
የጎል ማሽኑ ኧርሊንግ ሃላንድ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ጎሎች በማስቆጠር የፔፕ ጉዋርዲዮላ ቡድን ድል እንዲቀናው አግዟል።
በጨዋታው የመሐል ሜዳ ሞተሩ ኬቪን ደ ብረይነ ተጎድቶ ሲወጣ ከቼልሲ ሲቲን የተቀላቀለው ማቴዎ ኮቫቺች ከቡድኑ ጋር ተጣምሮ አምሽቷል።
ቅዳሜ ከሰዓት የመጀመሪያው ጨዋታውን በሜዳው ያደረገው አርሰናል ደግሞ ኖቲንግሃም ፎረስትን 2-1 ረትቷል።
ባለፈው ሳምንት በነበረው የኮሚኒቲ ሺልድ ጨዋታ ያልተሳተፈው ኤዲ ንኬቲያህ ለአርሰናል የመጀመሪያዋን ጎል አስቆጥሯል።
ከጨዋታው በኋላ አሠልጣኝ ማይክል አርቴታ ለ24 ዓመቱ እንግሊዛዊ አጥቂ ያላቸውን አድናቆት ገልጠዋል።
ጉልበቱ ላይ በገጠመው ጉዳት ምክንያት ቀዶ-ጥገና ማድረግ አለበት የተባለው የአርሰናል ቁጥር አንድ አጥቂ ጋብርኤል ጄሱስ ከሁለት ሳምንት በኋላ ሊመለስ ይችላል።
ለአርሰናል ሁለተኛዋን ጎል ግሩም አድርጎ ያስቆጠረው ኮከቡ ቡካዮ ሳካ ነው።
የ21 ዓመቱ ሳካ ከፍፁም ቅጣት መምቻው ሳጥን ውጭ አክርሮ በመጠቅለል የመታት ኳስ ጎል ሆናለች።
በክረምቱ አርሰናል የተቀላቀሉት ካይ ሃቨርትዝ፣ ጁሪዬን ቲምበር እና ዴክለን ራይስ ለመድፈኞቹ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አድርገዋል።
ኖቲንግሃም ፎረስት በጨዋታው መገባደጃ አንድ ጎል አስቆጥሮ ሁለተኛ ለመድገም ቢሞክርም አርሰናል ውጤቱን አስጠብቆ ወጥቷል።
ሌላው ምሸት የተደረገው ጨዋታ በቅርብ ዓመታት ጠንካራ እየሆኑ የመጡት ኒውካስል እና አስተን ቪላ ያደረጉት ነው።
በሜዳው ሴይንት ጄምስ ፓርክ አስተን ቪላን ያስተናገደው ኒውካስል 5-1 በመርታት አዲሱን የውድድር ዘመን ጀምሯል።
ለኒውካስል የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደረጉት ሳንድሮ ቶናሊ እና ሃርቪ ባርንስ አንድ አንድ ጎል አስቆጥረዋል።
ከትውልደ ኤርትራዊያን ቤተሰቦች የተገኘው አሌክሳንደር ኢሳክ ደግሞ ሁለት ኳሶች ከመረብ በማገናኘት የኒውካስል ቁጥር አንድ አጥቂ መሆኑን አሳይቷል።
ባለፈው የውድድር ዘመን በተለይ በሁለተኛው የውድድሩ አጋማሽ እጅግ መሻሻል ያሳየው አስተን ቪላ አሳፋሪ ሸንፈት ቀምሷል።
ከኒውካስል የመጀመሪያ ጎል በኋላ ፈረንሳዊው የክንፍ መስመር ተጫዋች ሙሳ ዲያቢ ለአስተን ቪላ በማስቆጠር አቻ ቢያደርግም ከሽንፈት አልታደጋቸውም።
በሌሎች ጨዋታዎች ቦርንመዝ ከዌስትሃም 1 አቻ ሲወጣ ፉልሃም ከሜዳው ውጭ ኤቨርተንን 1-0፤ በተመሳሳይ ክሪስታል ፓላስ ሼፊልድ ዩናይትድ 1-0 አሸንፈው ሶስት ነጥብ ይዘው ተመልሰዋል።
በአሠልጣኝ ዲ ዘርቢ ድንቅ ጨዋታ እያሳየ ያለው ብራይተን ደግሞ አዲስ መጭውን ሉቶን ታውን አስተናግዶ 4-1 ረትቷል።
ሊጉን ኒውካስል በጎል ልዩነት መምራት ሲጀምር፤ ብራይተን ሁለተኛ፤ ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
እሑድ ከሰዓት ብሬንትፈርድ ቶተንሃምን ሲያስተናግድ ምሽት 12፡30 ደግሞ ቼልሲ ከሊቨርፑል ይጫወታሉ።
ነገ ሰኞ ምሽት ደግሞ ማንቸስተር ዩናይትድ ዎልቭስን ያስተናግዳል።