ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጣሊያን ለዓመታት ሲፈለግ የነበረው ወንጀለኛ ለክለቡ ድጋፍ ሲሰጥ በፎቶ ከታየ በኋላ ተያዘ
በጣሊያን ለዓመታት በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው የአደገኛ ቦዘኔ ቡድን አባል ለእግር ኳስ ክለቡ ድጋፍ ሲሰጥ በፎቶ ከታየ በኋላ በቁጥጥር ሥር ዋለ።
ቪንቼንዞ ላ ፖርታ የተባለው የ60 ዓመቱ ወንጀለኛ በጣሊያኗ ኔፕልስ ከተማ ካሞራ ከተባለ የተደራጀ ወንጀለኛ ቡድን ጋር ጥብቅ ቁርኝነት አለው ተብሎ ሲፈለግ ነበር።
ይህ ለናፖሊ እግር ኳስ ክለብ ጥልቅ ፍቅር አለው የተባለው ወንጀለኛ ለ11 ዓመታት በጣሊያን ፖሊስ በጥብቅ ሲፈለግ ነበር።
በቅርቡ ታዲያ እራሱን ሸሽጎ በሚኖርባት በግሪኳ ኮርፉ ከተማ ክለቡ ናፖሊ ያገኘውን ድል ተከትሎ ከሌሎች ደጋፊዎች ጋር ደስታውን ሲገልጽ የሚያሳይ ምስል ከወጣ በኋላ በቁጥጥር ሥር ውሏል።
የኔፕልስ ፖሊስ፤ “ክህደት የፈጸመበት ለእግር ኳስ እና ለናፖሊ ያለው ፍቅር ነው” ብሏል።
የፖሊስ ባለስልጣናት በወንጀል ሲፈለግ የነበረውን ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ለማዋል የረዳው ፎቶ የተነሳው ናፖሊ እግር ኳስ ክለብ ከ30 ዓመታት በኋላ የጣሊያን ሻምፒዮን መሆኑን ተከትሎ ደጋፊዎች ድጋፋቸውን በገለጹ ወቅት ነው።
“ናፖሊ ሻምፒዮን መሆኑን ተከትሎ ላ ፖርታ በአደባባይ ደስታውን ከመግለጽ መቆጠብ አልቻለም” ብሏል የጣሊያን ፖሊስ።
ላ ፖርታ በጣሊያን በሌለበት በወንጀለኛ ቡድን በመዳረጀት፣ በታክስ ስወራ እና በማጭበርበር የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎበት የእስር ጊዜ ተበይኖበታል።
ፖሊስ የላ ፖርታ ምስልን መሠረት በማድረግ ክትትል አድርጎ ከትናንት በስቲያ አርብ በግሪኳ ደሴት ላይ አነስተኛ የኤሌክትሪክ ሞተሩን እያሸከረከረ ይዞታል።
ወደ ጣሊያን ተላልፎ ለመሰጠት በመጠባበቅ ላይ የሚገኘው ላ ፖርት አገሩ ሲደርስ የ14 ዓመት ከ4 ወር እስር ይጠብቀዋል።
የላ ፖርት ጠበቃ ለአሶሲዬትድ ፕሬስ ሲናገሩ፤ “በግሪክ አዲስ ቤተሰብ መሠርቷል . . . የ9 ዓመት ወንድ ልጅ አለው። ሕይወቱን ለመደገፍ ምግብ አብሳይ ሆኖ እየሰራ ነው። ከልብ ጋር የተያያዘ ሕመም አለበት። ተላልፎ የሚሰጥ ከሆነ የቤተሰቡ ሕይወት የተመሰቃቀል ይሆናል” ብለዋል።
የጣሊያን ባለስልጣናት ይህን በወንጀል ክስ በሌለበት እስር የተላለፈበትን ግለሰብ ለመያዝ ሳይታክቱ ሲሰሩ ቆይተዋል። የግለሰቡን የገንዘብ ዝውውር እና ኦንላይን እንቅስቃሴውን በመፈለግ “ስህተት እስኪሰራ ሲጠብቁ ነበር” ተብሏል።
የፖሊስ ጥረት ፍሬ አፍርቶ ግንቦት ወር ላይ ናፖሊ ከ33 ዓመታት በኋላ የጣሊያን ሴሪአ አ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ በግሪክ ካለ ከአንድ ምግብ ቤት አቅራቢያ ከሌሎች ደጋፊዎች ጋር ድጋፉን ሲገልጽ የሚያሳይ ምስል ከእጃቸው ገብቷል።
የጣሊያን ፖሊስ ምስሉን ከተመለከተ በኋላ ወደ ግሪክ በማምራት ከአገሪቱ ፖሊስ ጋር በመተባበር በቁጥጥር ሥር አውሎታል።