ኡጋንዳ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ቢሮን ልትዘጋ ነው

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፣ መንግሥታቸው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ ሥራውን እንዲያቋርጥ መወሰኑን ገለጹ።

ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት በፕሪቶሪያ በተካሄደው የኡጋንዳ እና ደቡብ አፍሪካ ኢንቨስትመንት ፎረም ጋዜጣዊ ላይ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ኡጋንዳ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሥራን ለማቋረጥ ስለመወሰኗ ከጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው።

ፕሬዝዳንቱ፣ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በሚመራው የቴሌቪዥን ጣቢያ - ኤስኤቢሲ በተላለፈው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ምላሽ ሲሰጡ “ኡጋንዳ በሕገ መንግሥቷ የሚመራ የራሷ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አላት። በመሆኑም በመጀመሪያ ደረጃ የሕገ መንግሥት ሥርዓታችን አካል ያልሆነ ሌላ ተቋም እንዲኖር መፍቀድ አስፈላጊ አይደለም፤ ጣልቃ ገብነትም ነው” ብለዋል።

“ጥሰቶችን እርምጃ ወደሚወስድ አካል ሪፖርት በማድረግ ፋንታ ወደ ተመድ ይሄዳሉ። ተመድ ኡጋንዳ ውስጥ ምን ማድረግ ይችላል? ሕግ የማስፈጸም ሥልጣን የለውም” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ የመንግሥታቸውን ውሳኔ ደግፈው ተከራክረዋል።

በአውሮፓውያኑ የካቲት ወር መጀመሪያ ላይ የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ መንግሥት መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ የሚያበቃውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ቢሮ ፈቃድን እንደማያድስ አስታውቆ ነበር።

ሚኒስቴሩ ለዋናው መሥሪያ ቤት በላከው ደብዳቤ፣ ኡጋንዳ ያለምንም የውጭ እርዳታ ሰብዓዊ መብቶችን የመጠበቅ፣ የመከታተል እና የማሳደግ አቅም እንዳዳበረች ገልጿል።

ይሁን እንጂ የመብት ተሟጋቾች ኡጋንዳ የተመድ ቢሮን የመዝጋት ውሳኔን ያወገዙ ሲሆን፣ ውሳኔውን “አሳፋሪ” ብለውታል።

ተቺዎች የመንግሥት እርምጃ በአገሪቷ እየጨመረ የመጣውን እንደ ማሰቃየት፣ በግዳጅ መሰወር፣ አፈና፣ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እስር እና በፍርድ ቤት በሕጋዊ መንገድ የተፈቱ ሰዎችን እንደገና ማሰርን ጨምሮ ለሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መንግሥት የሚሰጠው ምላሽ ነጸብራቅ ነው ሲሉ ተቃውመውታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያም ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር በተያያዘ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ምርመራ እንዲቋረጥ ጥረት እያደረገች እንደሆነ ዓለም አቀፍ ሲቪል ማኅበራት እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ለተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል።

የመብት ተሟጋች ድርጅቶቹ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረት እንዲያስቆምም በጋራ ጠይቀዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዋችን ጨምሮ ሌሎችም ከስድሳ በላይ የሚሆኑት ተቋማት ለተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ፣ ኢትዮጵያ በተመድ የሚከናወነው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ እንዲቋረጥ ለማድረግ የውሳኔ ሃሳብ ለማቅረብ ማቀዷ አሳስቦናል ብለዋል።