ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሆነው ተሾሙ

ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ

የፎቶው ባለመብት, BBC/Amensisa Ifa

የምስሉ መግለጫ, የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት እና አሁን ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ

ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ሆነው መሾማቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ይፋ እንዳደረጉት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ የፕሬዝዳንትነት ሥልጣኑን ከአቶ ጌታቸው መረከባቸውን ተናግረዋል።

"ዛሬ በይፋ እና በሰላማዊ መንገድ በአዲስ ባህል የሥልጣን ሽግግሩን እና ቅብብሎሹን ለማካሄድ የተዘጋጀ ፕሮግራም አከናውነናል" ሲሉ የሥልጣን ርክክብ መደረጉን አስታውቀዋል።

ይህ ሹመት የተሰጠው መጋቢት 12/2015 ዓ.ም. የመጀመሪያው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት አቶ ጌታቸው ረዳ ከኃላፊነት መሰናበታቸው ከተገለጸ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

አቶ ጌታቸው ሥልጣን በተረከቡበት ጊዜ 27 አባላት ያሉት የጊዜያዊ አስተዳደራቸው ካቢኔ አዋቅረው የነበረ ሲሆን፣ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በተደገው ጦርነት የትግራይ ኃይሎችን ሲመሩ የነበሩት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ እና ቀድሞው የአገሪቱ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ሌተናንት ጄኔራል ጻድቃን ገ/ትንሳኤን በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ ተሹመው ነበር።

ሌ/ጄነራል ታደሰ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ በመሆን ጊዜያዊ አስተዳደሩን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ለሁለት ዓመት ያህል በሥልጣን ላይ የቆዩት አቶ ጌታቸው ረዳ የህወሓት አመራሮች በሁለት ጎራ መከፈላቸውን ተከትሎ ሥልጣናቸው አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል።

በፓርቲው ሊቀመንበር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ቡድን በክልሉ የሚገኙ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር ጽህፈት ቤቶችን የተቆጣጣረ ሲሆን፣ አቶ ጌታቸው ረዳም ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እርሳቸው ለሚሾሙት ጊዜያዊ የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት የክልሉ ሕዝብ ዕጩዎችን እንዲጠቁማቸው መጋቢት 17/2017 ዓ.ም. በኤክስ ገፃቸው ጥሪ አቅርበው ነበር።

ያንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ መጋቢት 30/2017 ዓ.ም. ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሆነው መሾማቸውን አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሌ/ጄነራል ታደሰን መሾም በገለፁበት ጽሁፋቸው "አሁን ትግራይ ውስጥ ያለውን ክፍተት ሞልተው ወደ ፊት ሊወስዱ ይችላሉ" የሚል እምነት በበርካታ ወገኖች ዘንድ መኖሩን ተናግረዋል።

አክለውም "የትግራይ ሕዝብ የጠማውን ሰላም እና ልማት፣ እንደ ሌሎች ወንድሞቹ ወጥቶ የመግባት መሻት ስናሳካ፣ ለኢትዮጵያም ለአፍሪካም እጅግ ጠቃሚ የሆነ ነገር ሠርቶ ለማለፍ ታሪክ የሰጣቸውን ዕድል እንደሚጠቀሙበት ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የቆይታ ዘመን መጠናቀቁን ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በክልሎች የሚቋቋም ጊዜያዊ አስተዳደር የሥልጣን ዘመን፤ለሁለት ጊዜ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ እንዲራዘም የሚያስችል የአዋጅ ማሻሻያ መጋቢት 23/2017 ዓ.ም. ማጽደቁ ይታወሳል።

አዲሱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ሥልጣናቸውን በተረከቡበት ወቅት ከተገኙ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ዲፕሎማቶች በተጨማሪ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማሕሙድ አሊ ዮሱፍ፣ የኢጋድ ዋና ጸኃፊ ወርቅነህ ገበየሁ ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ተገኝተዋል።

ሌ/ ጄነራል ታደሰ ወረደ ማን ናቸው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ለሁለት ዓመታት ያህል በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የተደረገውን ደም አፋሳሽ ጦርነትን የመሩት ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ፣ ህወሓት ለ17 ዓመታት በዘለቀው የትጥቅ ትግል ወቅት ከተራ ተዋጊነት እስከ ጦር አዛዥነት ደርሰዋል።

በክልሉ ዋና ከተማ በሆነችው መቀለ የተወለዱት ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአፄ ዮሐንስ ትምህርት ቤት ነው።

በ1968 ዓ.ም. ወደ ትግል ሜዳ የወጡት ሌ/ጄነራል ታደሰ፣ ከ1969 ዓ.ም. እስከ 19 72 ዓ.ም. በተለያዩ የህወሓት ሠራዊት የአመራር እርከኖች ላይ ተሳትፈዋል።

ከ1972 መጨረሻ እስከ 1974 ዓ.ም. ድረስ የኮር አዛዥ ሆነው ያገለገሉት ሌ/ጄነራል ታደሰ፣ የ73ኛ ክፍለ ጦር መሪ በመሆን በተለያዩ ውጊያዎችን መርተዋል።

ህወሓት ከደርግ ወታደራዊ መንግሥት ጋር ውጊያ እያደረገ በነበረበት በዚህ ወቅት፣ የ43ኛ ብርጌድ አዛዥ በመሆን በኤርትራ በቀይ ኮከብ ዘመቻ ተሳተፈዋል።

ከኤርትራ ከተመለሱ በኋላ በዓዲ ጎዞሞ ጦርነት የተሳተፉት ሌ/ጄነራሉ፣በመቀጠልም የህወሓት እና የደርግ ወታደራዊ መንግሥት ወሳኝ ከሆኑት ጦርነቶች መካከከል አንዱ በሆነው 'የሽሬ ጦርነት' የዕዝ አዛዥ ነበሩ።

ጦርነቱ ወደ መሀል ኢትዮጵያ ሲቃረብ ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ የክንፍ አንድ ወይም 'ሬጅመንት' አዛዥ ሆነው እየተዋጉ ወደ አዲስ አበባ ገብተዋል።

በግንቦት ወር 1983 ደርግ ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ፣ የደቡብ ምዕራብ አዛዥ ሆነው የተሾሙት ሌ/ጄነራል ታደሰ፣ በመቀጠልም በ1987 የአዋሽ አርባ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል።

በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት በቡሬ ግንባር የኮር አዛዥ በመሆን የተሳተፉት ሌ/ጄነራሉ፡ በመጨረሻም የግንባሩ ዋና ኣዛዥ ነበሩ።

ለዘጠኝ ዓመት ያህል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ማሠልጠኛ ጄነራል ዳይሬክቶሬት በመሆን ከ2003 መጨረሻ እስከ 2004 ኣ.ም. መጨረሻ ድረስ 'የግዳጅ ኃይል' አዛዥ እንዲሁም በደቡብ ሱዳን የአብዬ ሰላም አስከባሪ ኃይል የተልዕኮው ከፍተኛ መሪ ነበሩ።

በመደበኛው ጦር ሠራዊት በኮሎኔልነት ማዕርግ የጀመሩት ታደሰ ወረደ፣ በ1991 ብርጋዴር ጄነራል ሲሆኑ፣ በጡረታ ሲሰናበቱ የሌተናንት ጄነራልነት ማዕረግ ነበራቸው።

ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ የትግራይ ክልል እና የፌደራል መንግሥቱ ፍጥጫ ውስጥ ሲገቡ የ'ትግራይ ልዩ ኃይልን' እንዲያደራጁ በወቅቱ የትግራይ ክልል መሪ በነበሩት ደብረፂዮን (ዶ/ር) መመረጣቸው ይነገራል።

ከዚያ በኋላም ለሁለት ዓመት በዘለቀው ደም ኣፈሳሹ የትግራይ ጦርነት የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ በመሆን መርተዋል።

ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የትግራይ ጦርነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ በተደረሰው ስምምነት ከቆመ በኋላ በናይሮቢ የማስተግበሪያ ስምምነትን ከኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ፊ/ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር ተፈራርመዋል።

በመቀጠል የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሲቋቋም በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ በመሆን ተሹመዋል።