አርቴታ እና አርሰናል ከፒኤስጂ ጨዋታ ምን ተማሩ?

አርሰናል በሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ጨዋታ በፒኤስጂ አንድ ለምንም ተሸንፏል።

መድፈኞቹ በጋብርኤል ማርቲኔሊ እና ሊያንድሮ ትሮሳርድ ጥሩ ዕድሎችን ቢያገኝም አቻ መሆን አልቻለም።

ቡድኑ ከመጀመሪያው ጨዋታ ምን ተማረ?

የፓርቴ አለመኖር ክፍተት የፈጠረበት አርሰናል

ቡድኑ በቅጣት ያጣውን ቶማስ ፓርቴን እንዴት ይተካል የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነበር።

በጉዳት የሳሳውን የአጥቂ መስመር ለመሸፈን ድግሞ ቡድኑ ሚኬል ሞሪኖን እያሰለፈ ነው።

ሜሪኖ ወደ መደበኛ የመሃል ተጫዋችነቱ ሲመለስ ዴክላይ ራይስ ደግሞ የፓርቴን ቦታ ሸፍኖ ወደ ሜዳ ገብቷል።

ፒኤስጂ በኳስ ቁጥጥር የበላይነት ጀምሯል። በመጀመሪያው 15 ደቂቃ 75 በመቶ ኳስ ተቆጣጥሯል።

በአራተኛው ደቂቃ ደግሞ ኡስማን ዴምቤሌ ኳስ እና መረብን አገናኘ።

ዴምቤሌ ደጋግሞ በአርሰናል አማካይ እና ተከላካይ መሃል በመግባት ደጋግሞ ችግር ሲፈጥር ባመሸበት ወቅት ነው ጎል ያስቆጠረው።

ፓርቲ ቢኖር ዴምቤሌን ማቆም ይችል ነበርን ሚለውን ጥያቄ አርቴታ መጠየቁ አይቀርም።

ጋናዊው ባለፉት ጨዋታዎች ድንቅ አቋሙን ደጋግሞ አሳይቷል።

የቪቻ ክቫራቴሊያ እና የቲምበር ፍልሚያ

የፓሪሱ ክለብ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾችን መያዙ ለአርሰናልም ለአርቴታም የማይጠበቅ አልነበረም።

ቡድኑ አስቶን ቪላን እና ሊቨርፑልን ጥሎ ነው ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰው።

ሁለቱ ቡድኖች ጥቅምት ላይ ሲገናኙ ቪቻ ክቫራቴሊያ ቡድኑን አልተቀላቀለም ነበር።

ዩሪየን ቲምበር ደግሞ ወጥ በሆነ አጨዋወቱ፣ በማጥቃት እና በመከላከል መስመር ላይ ባለው አቋም ቡድኑ የዘንድሮ ኮከብ ተጫዋች ከሆኑት አንዱ ነው።

ሆላንዳዊው በመጀመሪያው አጋማሽ ከክቫራቴሊያ ጋር በነበረው ፍልሚያ ተበልጦ ታይቷል።

ክቫራቴሊያ ኳስ ለጎል አመቻችቶ ሰጥቷል።

ጆርጂያዊው ደጋግሞ ማጥቃቱን ሲቀጥል ቡካዮ ሳካ ጭምር ወደ ኋላ ተመልሶ ቲምበርን ሲያግዘው ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ አርሰናል ኳሱን የተሻለ መቆጣጠር ሲጀምር ቲምበርም የበለጠ መንቀሳቀስ ችሏል።

አንድ አጥቂ የአርሰናሉን ተከላካይ በዚህ ደረጃ ሲያስቸገር ያመሸው ከረዥም ጊዜ በኋላ ነው።

"ኳሱን ካልያዝን ያልቅለናል"- ራይስ

ራይስ ይህንን ሲል ካሜራዎች የቀለቡት ከጨዋታው በፊት ነው።

አርሰናል በፈለገው መንገድ ኳሷን መስርቶ አለመጫወቱ እና በመጀመሪያው አጋማሽ እንግዳው ቡድን በኳስ ቁጥጥር በልጦ ታይቷል።

አርሰናል በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽሎ ቀርቦ 52 በመቶ ኳስ ተቆጣጥሯል።

ሚኬል አርቴታ 95 ደቂቃ በሙሉ ፒኤስጂን ተቆጣጥሮ "እንደማይቻል" እና "ጥቃቅን ጉዳዮች" ቡድኑ የተሻለ ውጤት እንዳያስመዘግብ ማድረጋቸውን ተናግሯል።

"ይህ ቡድኑ እንግሊዝ ውስጥ ያሉ ጠንካራ ቡድኖችን ያሸነፈ ነው" ብሏል።

"ስለዚህ 95 ደቂቃ በሙሉ አትበልጠውም። ይህ አይቻልም። የማይታሰብ ነው።"

"ስለዚህ እነሱን መብለጥ እና በየትኛው የሜዳ ክፍል ማለት እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል" ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

"ልዩነቱ ጠባብ ነበር"

ገና ቀሪ ጨዋታ አለ። ቡድኑ ማድሪድን 3 ለምንም በመምራት ወደ ቤርናባው በሄደበት መንገድ እንደሚጫወት አርቴታ አስታውቋል።

"ወደ ፓሪስ አቅንተን ማሸነፍ አለበን። ይህንን የማድረግ ብቃት አለን" ብሏል።

"ሁለት ጥሩ ቡድኖችን ተመልክቻለሁ። ልዩነቱ ጠባብ ነው። ጎል አጠገብ እነሱ የተሻለ ውጤታማ ነበሩ። ለውጤቱ ግብ ጠባቂውም ሚና ነበረው"

"ቁጥሩን ባላውቀውም ወደ ፍጻሜው የሚያደርሰን በርካታ ዕድል አለን። ለፍጻሜ ለመድረስ ትክክለኛ ውሳኔዎች ያስፈልጋሉ። ይህ የሚሆነው ደግሞ ፓሪስ ላይ ነው።"

ሊዊስ ኤንሪኬ ደግሞ ፒኤስጂ "ይፈተናል" ይላል

ዶናሩማ ሁለት ጥሩ ዕድሎችን ማምከን የቻለ ሲሆን ፒኤስጂም ጨዋታውን መጨረስ የሚችልባቸውን ዕድሎች አምክኗል።

ከግብ ጠባቂው ጋር የተገናኙት ብራድሊ ባርኮላ እና ጎናሉካ ራሞስ ዕድላቸውን ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።

አሰልጣኝ ሊዊስ ኤንሪኬ ቡድኑ ፒኤስጂ በሜዳው "ይፈተናል" ብሎ ያምናል።

"በዚህ ዓይነቱ ጨዋታ ስሜት ከፍ ስለሚል ለማመዛዘን ይከብዳል። ድባቡ ጥሩ የነበረ ቢሆንም ቡድናችንን አሳይተናል።"

"በአጨዋወታችን ጸንተን በፍጥነት ጎል አስቆጥረናል። አንዳንዴ ብንፈተንም ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር እንችል ነበር። ሁለተኛው ጨዋታ ከባድ ይሆናል" ብሏል።

"ሁለተኛው ጨዋታ ከባድ ስለመሆን እንዘጋጃለን። ውጤቱ ለእኛ በትንሹም ቢሆን ያደላ ነው። እንደምንፈትን እናውቀዋለን። ወደ ፍጻሜው እንደምናልፍ ብናውቀውም ገና አንድ ጨዋታ ይቀረናል" ሲል ሃሳቡን ሰጥቷል።