የሊቨርፑል አለቃ አርን ስሎት እንዴት ያልተጠበቀውን በማሳካት ሊቨርፑልን ለሻምፒዮንነት አበቁት?

"በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ሊቨርፑል የሊጉን ዋንጫ ያነሳል ወይ ብላችሁ ብትጠይቁ አብዛኞቹ ደጋፊዎች መልሳቸው በፍጹም የሚል ነበር" ብሏል የቀድሞው የክለቡ የግብ ጠባቂ ሳንደር ዌስተርቨልድ።

የርገን ክሎፕን መተካት በጣም አስቸጋሪ ነው።

ጀርመናዊው አሠልጣኝ ከኃላፊነታቸው እንደሚነሱ ሲገልጹ ሊቨርፑላዊያን ስጋት ገብቷቸው ነበር።

ማን ይተካቸዋል? የቡድኑስ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? የሚሉ ጥያቄዎች ተከተሉ።

"ክሎፕ ክለቡን ቀይረውታል። ይህ ደግሞ ሜዳ ውስጥ ብቻ የተገደበ አይደለም።"

የቀድሞው ክለቡ ተጫዋች እና ባየር ሊቨርኩሰንንን ለመጀመሪያ ቡንደስሊጋ ዋንጫ ያበቃው ዣቢ አሎንሶ በጀርመን ለመቀጠል መፈለጉ ትኩረት ወደ አርን ስሎት ዞረ።

"በወቅቱ አርንን አልጠበቅኩም ነበር" ሲል ዌስተርቨልድ ስለአገሩ ልጅ እና ስለቀድሞ የቡድን አጋሩ ተናግሯል።

"በእንግሊዝ እግር ኳስ አይታወቅም። የሚኖርበት ኃላፊነት ደግሞ ከፍተኛ ነበር።"

ከክሎፕ ወደ ስሎት የተደረገው ሽግግር ስኬታማ ሆኖ ከክለቡ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ክብረወሰን ተጋርቶ 20ኛ የሊግ ድሉን አሳክቷል።

ቡድኑ ከ34 ጨዋታዎች 25ቱን አሸንፎ በሁለቱ ብቻ ተሸነፈ። በመጨረሻም ሻምፒዮን መሆኑ ተረጋገጠ።

ከሁለት ዓመት በፊት ቶተንሃምን መቀላቀል ያልፈለጉት ስሎት በመጀመሪያ የውድድር ዘመናቸው የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ካነሱ አሠልጣኞች አንዱ ሆኑ።

ሆዜ ሞሪንሆ (ቼልሲ 2004/05)፣ ካርሎ አንቸሎቲ (ቼልሲ 2009/10)፣ ማኑዌል ፔሌግሪኒ (ማንቸስተር ሲቲ 2013/14) እና አንቶኒዮ ኮንቴ (ቼልሲ 2016/17) ቀደም ሲል በመጀመሪያ ዓመት ዋንጫ ያሳኩ አሠልጣኞች ናቸው።

የሊቨርፑል ኢኮ ፀሐፊው ኢያን ዶይል በበኩል "ማንም ይህንን አልጠበቀም" ብሏል።

የዘንፊልድ ራፕ አቅራቢው ኒል አትኪንሰን ደግሞ "ማንም ሰው አዲስ አሠልጣኝ መጥቶ የርገን ክሎፕን ለመሆን ሲጥር መመልከት አልፈለገም" ሲል ገልጿል።

"ስሎት ራሱን እንዲሆን ደጋፊው ይጠበቅ ነበር። ስሎትም ይህንን አድርጓል።"

የስሎት አስደማሚው ቀመር

የስሎት ዋነኛው ሥራ ክሎፕ የገነቡትን ቡድን አጠናክሮ ማስቀጠል ነበር።

የተከላካይ መስመሩን ማጠናከር እና የመሐል ሜዳውን የበላይነት ማስጠበቅን ሠርተዋል። ቡድኑ ሦስት ጨዋታ ካሸነፈ 90 ነጥብ ይደርሳል።

"ቡድኑ ደካማም ሆኖ በአስቸጋሪ ሁኔታም ደጋግሞ አሸንፏል" ብሏል አትኪንሰን።

ቡድኑ አዲስ ያስፈረመው ፍሬድሪኮ ኪዬሳ ብቻ ነው። እንደ ሪያን ግራቨንበርች ያሉ ተጫዋቾች ደግሞ አቋማቸው ተሻሽሏል።

የሞሐመድ ሳላህ የጎል ማስቆጠር ብቃት ደግሞ ካለፈው ዓመት አንጻር ተሻሽሏል።

ኮዲ ጋክፖም ካለፉት ዓመታት ከፍ ያለ ጎል ከመረብ አሳርፏል።

"አርን ስሎት ተጫዋቾቹን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያገኙ ቀደም ሲል ቡድኑ የነበረውን መረጃ አሰባስበው ነበር" ብሏል ዌስተርቨልድ።

"ቡድኑ ዋንጫ ካነሳው ቡድን አንጻር ውጤታማ አልነበረም። 'በርትታችሁ ሥሩ' ሲሉ ደጋግመው ተደምጠዋል።"

ሥልጠና ሂደቱም ተቀየረ። ስሎት 'ሰውነትን ማንቃት' የሚባል የአተነፋፈስ ልምምድ ከጨዋታ እና ከልምምድ በፊት እንዲከናወን ያደርጋሉ።

ቡድኑ በሜዳው ከሚያደርገው ጨዋታ በፊት በሆቴል የማደር ልምድ የነበረው ቢሆንም ይህ ግን አሁን ተቀይሯል።

የልምምድ ሰዓት ቢራዘምም ጉዳት እንዳይከሰት በሚል ጠንካራ ልምምድ አይሠራም።

ከሕክምና እና ከልምምድ ጋር የተያያዙ አዳዲስ ባለሙያዎችም ተቀጥረዋል።

ጓደኝነት እና ቤተሰባዊነትን መፍጠር

የሊቨርፑል ደጋፊዎች ስሎት አሠልጣኝ መሆናቸው ከተነገረ በኋላ የጀመሪያ ጨዋታቸውን ለማድረግ 3 ወር ያህል ቆይተዋል።

ክሎፕ ሥራቸውን ሲያጠናቅቁ ደጋፊዎች ስለስሎት እንዲዘምሩ አድርገገዋል።

"ከመጀመሪያ ጨዋታው በፊት አርን ስጋት ገብቶት እንደነበር ጥይቄዋልሁ" ብሏል ዌስተረቨልድ።

"'ታውቃለህ የፌይኖርድ አሠልጣኝ ስለነበርኩ ለምጄዋለሁ' ብሎኛል።"

"'አርን ትክክል አይደለህም። ይህ አንፊልድ እኮ ነው' ብለውም ነገሩን አቅልሎታል።"

"ሳስበው ግን ሊቨርፑል ለእሱ የተዘጋጀ ቡድን ነው። በጣም የተረጋጋ ሰው ነው። ለእሱ ሁሉም ነገር ተመሳሳይ በመሆኑ ምንም አይቀየርም።"

"ከ12 ጨዋታዎች 11ዱን ሲያሸንፍ አልተገረመም። ቡድኑ ከሊግ ዋንጫ እና ከሻምፒዮንስ ሊግ ሲወጣም አልደነገጠም።"

አሠልጣኙ በደጋፊዎች ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ከፍተኛ ነው።

የሰባት ዓመቱ አይዛክ ኬርኒ የቡድኑ ደጋፊ ሲሆን፣ ባለበት የጤና ዕክል ምክንያት እንደ ዕድሜ እኩዮች የማደግ ችግር አለበት።

ክለቡ አይዛክን እና ቤተሰቦቹን ጋብዞ ነበር።

ስሎት ሥራ ስለሚበዛባቸው ላይገኙ እንደሚችሉ ተነግሯቸው ነበር።

"አይዛክ ከሞ ሳላህ እና ቨርጂል ቫንዳይክ ጋር በአሠልጣኙ ቢሮ በኩል ሲያል 'አርን' ብሎ ተጣራ" ትላለች እናቱ ሜሊሳ።

"አሠልጣኙ ስብሰባ ላይ ቢሆኑም ወጥተው አይዛክን አናገሩት። ምሳ ስንበላም አርን መጥተው ነበር።"

"አርን መደሰቱን ሲጠይቁት ትሬንት አሌክሳንደር-አርኖልድ እየጠበቀ መሆኑን ሲነግራቸው አሁን እወስድሃለሁ አሉት" ብላለች።

መጋቢት ላይ አሠልጣኙ በቅጣት ቡድኑን መምራት እንደማይችሉ ሲታወቅ ጨዋታውን ከጓደኛቸው አይዛክ ጎን ሆነው እንደሚመለከቱ ተናግረው ግንኙነታቸውን መጠን አሳይተዋል።

ስሎት ተወዳጅ እና መግባባት የሚችሉ መሆናቸውንም አሳይተዋል።

"ሥራውን ቀለል አድርጎ ያከናውን ነበር። በቃለ መጠይቆቹ መቀለድም መሳቅም እንደሚችል አሳይቷል" ብሏል ዶይል።

ቡድኑ በሻምፒዮንስ ሊግ 2 ለ 1 ሲያሽንፍ የአርን አባት አረንድ ስሎት ደስተኛ አይደሉም መባሉ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

"ስደውለልት 'እንደሌሎቹ የሊቨርፑል ጨዋታዎች ሳቢ አይደለም' አለኝ" ብለዋል ስሎት።

በመርሲሳይድ ደርቢ ከኤቨርተን ጋር 2 አቻ ሲለያዩ ስሎት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተባረዋል።

"ሲባረር ተናዶ የነበረ ቢሆንም ሲመለከተኝ ፈገግ አለ" ብሏል ዌስተርቨርድ።

ኔዘርላንድ እያሉ ስሎት ከእነዌስተርቨርድ ጋር ይጫወቱ ነበር፤ አሁን ደግሞ ከሌሎች አሠልጣኞቻቸው ጋር ፓዴል ይጫወታሉ።

"ቤት እሄዳለሁ፣ እመገባለሁ እና ኮምፒውተሬን አውጥቼ ልምምዱን እመለከታለሁ፣ ለቀጣዩ ጨዋታ እዘጋጃለሁ" ሲሉ ቤት ሆነው የሚሠሩትን ገልጸዋል። ቤተሰቦቻቸው አሁንም ኔዘርላንድስ ነው የሚኖሩት።

"ጎበዝ እና ሥራውን አጥብቆ የሚሠራ ሰው ነው" ብሏል አትኪንሰን።

"ቀላል ይሆንለታል ብዬ አላሰብኩም ነበር'

ሊቨርፑል በተከታታይ ዓመታት የሊግ ዋንጫን ያነሳው በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ ነበር።

ለመሆኑ የዘንድሮውን ድል አጠናክረው ይቀጥላሉን?

ዘንድሮ ቡድኑን ያላጠናከሩት አሰልጣኙ ለቀጣዩ የውድድር ዓመት ተጫዋቾችን እንደሚያስፈርሙ ይጠበቃል።

ሳላህ ኮንትራቱን አራዝሟል። ቨርጂል ቫንዳይክም ተመሳሳይ ውሳኔ ላይ ደርሷል። ትሬንት ወደ ማድሪድ ማቅናቱ የማይቀር ይመስላል።

ሊቨርፑል ዓይኗን በአሌክሳንደር ኢሳክ እና ሚሎስ ኬርኬዝ ላይ ጥሏል።

"ስሎት አሠራረን የሚቀይር አይመስለኘም። አሁንም 0 ነጥብ እንደሚያሳኩ አስባለሁ። ይህ ደግሞ ለዋንጫ ያፎካክራል" ብሏል አትኪንሰን።

ዌስተርቨርድ ጓደኛው ዋንጫ ሲያነሳ ለመመልከት ሊቨርፑል ከክሪስታል ፓላስ የሚያደርገውን ጨዋታ ለመታደም ተዘጋጅቷል።

"በኔዘርላንድ ከማሰልጠን ወደ እንግሊዝ መጥቶ ስኬታማ መሆን ቀላል ይሆንለታል ብዬ አላሰበኩም ነበር" ብሏል።

"በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ባሸነፈ ቁጥር እንኳን ደስ አለህ እያልኩ መልዕክት እልክለት ነበር። በኋላ ላይ ግን አስለቺ እየሆነ ስለመጣ ተውኩት" ሲል ሃሳቡን አጠቃሏል።