የሶማሊያ ፖሊስ 'ኒቃብ' መቀማት ጀመረ

በሶማሊያ ደቡባዊ ከተማ ኪስማዩ ፖሊስ በርካታ የሴት ፊት መሸፈኛ ሻሾችን በዘመቻ መልክ ከነዋሪዎች መቀማት መጀመሩን የአካባቢው ፖሊስ ኃላፊ ገለጹ።

ፖሊስ ‘ኒቃብ’ የተሰኘውን የፊት መሸፈኛ ሻሽ ለመቀማት የተገደደው ከሽብር ጥቃት ጋር ተያይዞ ነው።

የፖሊስ ኃላፊው ዋርሳሜ አሕመድ ገሌ ለአገሬው ቴሌቪዥን እንደተናገሩት የአካባቢው ባለሥልጣናት በኒቃብ ላይ ዘመቻ ከፍተዋል።

ዘመቻው ጂሓዲስቶችን ለማደን ያለመ ነው ብለዋል።

ጂሓዲስቶች የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲሹ ማንነታቸውን በኒቃብ በመሸፈን ከእይታ ይሰወራሉ።

ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያለው አልሸባብ ላለፉት በርካታ ዓመታት በሶማሊያ የሽብር ጥቃት ሲፈጽም ኖሯል። በዚህም ሺዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

አልሸባብ አብዛኛውን ደቡባዊና ማእከላዊ ሶማሊያን ተቆጣጥሮ ያስተዳድራል።

ባለፈው ዐርብ በሞቃዲሾ አልሸባብ ፈጸምኩት ባለ ጥቃት የበርካቶች ሕይወት ጠፍቷል።

ይህን ተከትሎ በኪስማዮ ፖሊስ ሴቶችን በመንገድ ላይ እያስቆመ ኒቃብ የተሰኘውን የሙሉ ፊት መሸፈኛ ሻሽ ሲቀማ አልያም እንዲያወልቁት ሲያስገደድ ነበር።

ዋሳሜ እንዳሉት ይህ ዘመቻ የተጀመረው ከባለፈው ረቡዕ ወዲህ ነው።

ከዚህ ወዲህ ኒቃብ የሚለብሱ ሴቶች የገንዘብ ቅጣት አልያም እስር ይጠብቃቸዋል።

ይሁንና አልሸባብ ደቡባዊ ሶማሊያን በአመዛኙ ስለሚቆጣጠር፣ ከመላው የጁባላንድ ግዛት ይህ ሕግ ተፈጻሚ ሊሆን የሚችለው በኪስማዮና አካባቢው ብቻ ነው።

ግዛቱ ኒቃብ ላይ እግድ የጣለው በፈረንጆቹ 2013 ዓመተ ምሕረት ቢሆንም ተፈጻሚነቱ ግን ያን ያህል አይደለም።

ኒቃብ በሙስሊም ሴቶች ዘንድ የጨዋነት መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል።

ኒቃብን ከሒጃብ የሚለየው ከዐይን በስተቀር ሙሉ የፊት ገጽታ የሚሸፍን በመሆኑ ነው።

ሒጃብ በአንጻሩ ጸጉርን ብቻ የሚሸፍን ነው።

መንግሥት እንደሚለው ከሶማሊያ ሕዝብ 99 ከመቶ የእስልምና እምነት ተከታይ ነው።

ባለፈው ዐርብ በሞቃዲሾ በተፈጸመው ጥቃት ፖሊስ 37 ሰዎች መገደላቸውን ቢገልጽም ጥቃቱን መፈጸሙን ያመነው አልሸባብ ግን የሟቾቹ ቁጥር ከዚህ በብዙ እጥፍ የበለጠ ነው ብሏል።