ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሐምሌ ወር በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ለተከሰተው የመሬት መንሸራተት ምክንያቱ ምንድን ነው?
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን ካዎ ኮይሻ ወረዳ ጤፓ ቀበሌ ሰኞ ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም. በተከሰተ የመሬት ናዳ አደጋ ቢያንስ የ11 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የወረዳው አስተዳደር አስታወቀ።
ከአደጋው በኋላ በተደረገው ፍለጋ እና የነፍስ አድን ጥረት እስከ ሰኞ አስር ሰዓት ድረስ የ11 ሰዎች አስከሬን የተገኘ ሲሆነ፣ ነገረ ግን የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል የካዎ ኮይሻ ወረዳ አስተዳደር ገልጿል።
ይህ አደጋ የደረሰው ከአንድ ሳምንት በፊት ሐምሌ 15/2016 ዓ.ም. በዚያው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ በተባለ ወረዳ በደረሱ ሁለት ተከታታይ የመሬት መንሸራተቶች አደጋ ከ250 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሕይወት አልፏል።
በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው በዚህ የመሬት መንሸራተት አደጋ የሕይወት አድን እና ፍለጋው ከሳምንት በላይ የተደረገ ሲሆን፣ በአደጋው ቀበሌው ሙሉ ለሙሉ ጉዳት እንደደረሰበት እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም እንዲፈናቀሉ አድርጓል።
ይህንን ጨምሮ በወርሃ ሐምሌ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች አምስት የሚሆኑ የመሬት መንሸራተት እና መሰንጠቅ አደጋዎች ያጋጠሙበት ነው።
በተለይም በደቡባዊው የኢትዮጵያ ክፍል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፉ አደጋዎች በሦስት አካባቢዎች ተከስተዋል።
ከቀናት በኋላ ደግሞ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ካፋ ዞን ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም. በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው የተባሉ የሦስት ዓመት ሕጻንን ጨምሮ የሦስት ሰዎች ሕይወት አልፏል።
በዞኑ ዴቻ ወረዳ ሞድዮ ጎንበራ ቀበሌ ልዮ ስሙ መንደር ሦስት ወይም አሸብ በተባለው አካባቢ የደረሰው አደጋ በአንድ ሰው ላይ ከባድ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፤ በርካታ ሰዎችም ተፈናቅለዋል።
ሐምሌ 21/ 2016 ዓ.ም. በሲዳማ ክልል ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት ማለፉን እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የክልሉ አስተዳደር አስታውቋል።
ባለፈው ሳምንት ደግሞ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማ በደረሰ የመሬት መሰንጠቅ አደጋ የሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ባይደርስም በአንድ መስጂድ እና የግለሰብ ቤት ላይ ጉዳት መድረሱን የከተማው አስተዳደር ተናግሯል።
ወቅቱ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የክረምት ጊዜ በመሆኑ እነዚህ አደጋዎች በየአካባቢዎቹ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ መጣሉን ተከትሎ የደረሱ ናቸው።
መሬት የሚንሸራተተው ምን ሲሆን ነው?
በኢትዮጵያ የመሬት መንሸራተት ክስተቶች አዲስ ባይሆኑም፤ በተደጋጋሚነታቸው እና በጉዳት መጠናቸው ግን ከሰሞኑን የደረሱ አደጋዎች ከባድ የሚባሉ ናቸው።
የመሬት መንሸራተት በተለይም በሰሜን እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክፍሎች በተደጋጋሚ እንደሚከሰት የሚናገሩት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የሥነ ምድር ምህንድስና መምህር አቶ ቶላ ገሮ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ አደጋው እየበዛ ነው ይላሉ።
የዓለም ሙቀት በጨመረ ቁጥር የዝናብ መጠን እንደሚጨምር ጥናቶችን በዋቢነት የሚጠቅሱት መምህሩ፤ ለመሬት መንሸራተት ዋነኛው መንስኤ ዝናብ እንደሆነ ይናገራሉ።
በመሆኑም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመሬት መንሸራተት አደጋ መብዛት በአብዛኛው ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይጠቁማሉ።
መምህሩ ለመሬት መንሸራተት ውስጣዊ እና ውጫዊ የሆኑ መንስኤዎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ የድንጋይ እና የአፈር ዓይነትን ለክስተቱ መንስኤነት በቀዳሚነት ያነሳሉ።
“አፈሩ በደንብ ያልተጣበቀ ከሆነ፣ ጥንካሬው ዝቅተኛ ከሆነ፣ ድንጋዮች ደግሞ የተሰነጣጠቁ ከሆኑ ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ ይሆናል” ይላሉ።
የመሬት አቀማመጥን በሁለተኛ መንስኤነት የሚያነሱ ሲሆን፤ ብዙ ጊዜ የመሬት ምንሸራተት የሚፈጠው በጣም ከፍታማ በሆኑ አካባቢዎች እንደሆነ ይገልጻሉ።
“ለጥ ያለ መሬት ላይ ብዙ ጊዜ የመሬት መንሸራተት አንጠብቅም። ዳገት በጨመረ ቁጥር የመሬት መንሸራተት የመከሰት ዕድል እጨመረ ነው የሚሄደው። . . . ሌላው ድንጋይ እና አፈር በሚገናኙበት በተለይም አካባቢ ተራራማ ከሆነ አፈሩ ድንጋዩ ላይ ይንሸራተታል ማለት ነው” ሲሉ መሬት የሚንሸራተትበትን ውስጣዊ መንስኤ ያብራራሉ።
በውጫዊ መንስኤነት የመሬት መንሸራተትን የሚቀሰቅሱ የሚባሉት ደግሞ እንደ ዝናብ ዓይነት ተፈጥሯዊ ክስተቶች ናቸው።
በአመዛኙ የመሬት መንሸራተት የሚፈጠረው ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት እንደሆነ የሚያነሱት ባለሙያው፤ “ዝናብ የአፈር ባዶ ቦታዎች ውስጥ በመግባት ጫና ይፈጥራል” ይላሉ።
“ለምሳሌ ተራራማ ቦታ ላይ በመኪና አፈር ብንደፋና ከላይ ውሃ ብናፈስበት፤ ውሃው በከፊል አፈር ውስጥ ይገባል። አፈር ውስጥ ገብቶ ወደ ታች ግፊት ይፈጥራል። ሌላው ውሃው በራሱ ክብደት ስላለው አፈሩን ወደ ታች ይገፋዋል። ስለዚህ የዝናብ ውሃ ድንጋይ ውስጥም ሊሆን [ሊገባ] ይችላል፤ አፈር ውስጥ በመግባት ግፊት በማሳደር የመሬት መንሸራተት እንዲፈጠር ያደርጋል” ሲሉ ዝናብ ለመሬት መንሸራተት ዋነኛ መንስኤ መሆኑን ይገልጻሉ።
የመሬት መንቀጥቀጥ ሌላኛው ውጫዊ መንስኤ ሲሆን፤ መምህሩ ከመሬት መንቀጥቀጥ ጋር ተያይዞ የመሬት መንሸራተት የመከሰት ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ያነሳሉ።
በሦስተኛ ደረጃ ለመሬት መንሸራተት መንስኤ የሚባለው የሰው ልጅ እንቅስቃሴ ነው።
“ለምሳሌ መንገድ ሲሠራ ብዙ ጊዜ ተራራዎች በኤክስካቫተር፣ በተለያዩ ማሽኖች ይናዳሉ። እና ከስር ለመንገድ ወይም ደግሞ ለሌሎች ግንባታዎች አፈር ወይንም ድንጋይ በምናነሳበት ወቅት [መሬቱን] ድጋፍ እናሳጣዋለን ማለት ነው። ስለዚህ ከታች ድጋፍ የሚሰጠውን ክፍል ካነሳን ከላይ ያለው ክፍል ደግሞ ይደረመሳል ማለት ነው” ይላሉ።
ቢቢሲ ለሥነ ምድር ምኅንድስና መምህሩ የመሬት መንሸራተትን ማቆም ይቻላል ወይ ብሎ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፤ የመሬት መንሸራተትን ማቆም ሳይሆን መቀነስ እንደሚቻል ጠቁመዋል።
“የመሬት መንሸራተት የሚፈጠረው በጊዜ ሂደት ስለሆነ፤ [ሊደርስ የሚችል] መንሸራተት የሆነ ቦታ ላይ መኖሩን የሚጠቁሙ መሳሪዎች አሉ። የመሬት መንሸራተት መፈጠሩን የሚለኩ [እንደ Extensometer የተባሉ] መሳሪያዎች አሉ” ቢሉም እነዚህ መሳሪያዎች ግን በአገሪቱ አለመኖራቸውን ተናግረዋል።
የመሬት መንሸራተትን ለመቀነስ መጀመሪያ ጥናቶችን መሠራት አለባቸው የሚሉት መምህሩ፤ የስጋት አካባቢዎችን በመለየት የመከላከል እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚቻል ይገልጻሉ።
“የሆነ ቦታ ላይ መሬት መንሸራተት ይፈጠራል አይፈጠርም የሚለውን መጀመሪያ በጥናት መለየት ይቻላል። [መንስኤዎችን] እንደ መለኪያ ግብዓት በመጠቀም በተፈለገው ስፍራ የመሬት መንሸራተት ይፈጠል ወይስ አይፈጠርም ብለን ማስቀመጥ እንችላለን። ከፍተኛ የስጋት አካባቢ፣ መካከለኛ የስጋት አካባቢ፣ ዝቅተኛ የስጋት አካባቢ ብለን መለየት እንችላለን” ይላሉ።
የስጋት አካባቢዎቹ ከተለዩ በኋላ ለመቀነስ የተለያዩ ተግባራት ማከናወን እንደሚቻል የሚናገሩት የሥነ ምድር ምህንድስና መምህሩ ቶላ ገሮ፤ ለዚህም ምሳሌ ይጠቅሳሉ።
“ለምሳሌ ዳገቱን ማስተካከል ይቻላል። ተፋሰሶችን መሥራት እንችላለን። ውሃ ወደ መሬት ውስጥ ገብቶ ግፊት እንዳይፈጥር እያጠጋጋን ተፋሰሶችን በመሥራት የሚዘንበው ዝናብ ወደ መሬት ሳይገባ በቦይ እንዲሄድ ማድረግ እንችላለን። ሌላው ደግሞ ችግኞችን መትከል ነው” ሲሉ ያሉ አማራጮችን ያስቀምጣሉ።
ነገር ግን ከፍተኛ ስጋት ባለባቸው አካባባቢዎች “ሁሉም ማኅበረሰብ ከፍተኛ ስጋት ላይ ከሆነ ወደ ሌላ ቦታ ማስፈር” እንደሚመረጥ ይመክራሉ።
በርካታ ተራራማ አካባቢዎች ያሏት ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ የቆዳ ስፋቷ 49 በመቶ የሚሆነው መሬት ለመንሸራተት አደጋ የተጋለጠ መሆኑን የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ።