ባሏ እና ልጆቿን በጎፋው የመሬት መንሸራተት አጥታ ብቻዋን የቀረችው እናት ሰቆቃ

ባሏ እና ልጆቿን በጎፋው የመሬት መንሸራተት አጥታ ብቻዋን የቀረችው እናት ሰቆቃ

ባለፈው ሰኞ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የደረሰው የመሬት መንሸራተት ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል የበርካታ ቤተሰቦች አባላትን ሕይወት ቀጥፏል። ልጆችን ያለ አባት እና እናት፣ ወላጆችን ያለ ልጆች ነዋሪዎችን ያለ ወዳጅ ዘመድ አስቀርቷል።

መሰለች ጎሳም ይህ ከባድ ሐዘን ከገጠማቸው ነዋሪዎች አንዷ ናት፥ በአደጋው ባሏን እና ሁለት ልጆቿን አጥታለች። የባለቤቷን እና የአንድ ልጇን አስከሬን ያገኘች ሲሆን፣ አንደኛው ልጇ ግን ላለፉት አምስት ቀናት እየተፈለጉ ካሉት መካከል ነው።

መሰለች ከሰኞ ጀምሮ ለባሏ እና ለልጆቿ እያለቀሰች ከአደጋው ስፍራ አልተለየችም። አደጋው ከደረሰ አምስት ቀናት ያለፉ ቢሆንም ተስፋ አልቆረጠችም። ብቻዋን ላለመቅረት አንደኛው ልጇ ይገኛል ብላ በደበዘዘ ተስፋ እየጠበቀች ነው።

በጎፋ ዞን ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ የደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ እስካሁን ከ250 በላይ ሰዎች መሞታቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ ቁጥሩ እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል ተሰግቷል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የአደጋውን አሰቃቂነት መሠረት አድርጎ ከቅዳሜ ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሐዘን አውጇል።