ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትራምፕ የዘመቻ አማካሪ በአሜሪካ የዩኬ አምባሳደር ተሿሚን 'ደደብ' ሲሉ ዘለፏቸው
የዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ የዘመቻ አማካሪ የሆኑት ግለሰብ በአሜሪካ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ሆነው የተሾሙትን፣ሎርድ ፒተር ማንደልሰንን "ፍፁም ደደብ" ሲሉ ዘለፉ።
ክሪስ ላሲቪታ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ሎርድ ማንደልሰን " እዛው ቤቱ መቆየት አለበት" ሲሉ ጽፈዋል።
የትራምፕ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ስራ አስኪያጅ የነበሩት ሚስተር ላሲቪታ የብሪታንያ መንግሥት "በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበሩትን አምባሳደርን በፍፁም ደደብ" ሰው ሊተካ ነው ሲሉ ውሳኔውን ተችተዋል።
ሎርድ ማንደልሰን በቶኒ ብሌር እና በጎርደን ብራውን የስልጣን ዘመን በበርካታ የሚኒስትርነት ስልጣኖች ውስጥ ያገለገሉ እና በብሪታኒያ ፖለቲካ ውስጥ በጣም ታዋቂ የሆኑ ናቸው።
ሎርድ ማንደልሰን በአሜሪካ ቀጣይ የእንግሊዝ አምባሳደር ሆነው መሾማቸውን "ትልቅ ክብር" ሲሉ ነበር የገለጹት።
ዘ ታይምስ እንደዘገበው ሎርድ ማንደልሰን፣ በ2025 መጀመሪያ ላይ ትራምፕ ወደ ኋይት ሀውስ ሲገቡ የስልጣን ዘመናቸው ሊያበቃ የተቃረበውን አምባሳደር ዴም ካረን ፒርስን ይተካሉ።
የ71 ዓመቱ አዛውንት እና "የጨለማው ልዑል" የሚል ቅጽል ስም የተሰጣቸው የአዲሱ ሌበር ፓርቲ ወሳኝ ሰው፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በትራምፕ መጪ አስተዳደር መካከል፣ በአሜሪካ እና ዩኬ መካከል ለሚኖረው ዲፕሎማሲ ቁልፍ ሰው ይሆናሉ።
ልክ እንደሌሎች የሌበር ከፍተኛ ባለስልጣኖች፣ ሎርድ ማንደልሰን ዶናልድ ትራምፕን በመተቸት ይታወቃሉ። በአንድ ወቅት "የነጭ ብሔርተኛ እና የዘረኝነት ርዝራዥ" በማለት ገልጸዋቸው ነበር።
ላሲቪታ በሎርድ ማንዴልሰን ላይ ለሰነዘሩት ትችት መነሻ የሆኑት እነዚያ አስተያየቶች ሲሆኑ፣ በኤክስ ገጻቸው ላይ በለጠፉት ጽሑፍ መጪው አምባሳደር "ትራምፕን የዓለም ስጋት እና የነጭ ብሔርተኛ ርዝራዥ" ሲሉ ገልፀውታል ብለዋል ።
የሪፐብሊካን ፖርቲ አንጋፋ ሰው ላሲቪታ በርካታ አሥርት ዓመታት ልምድ ያላቸው ሲሆኑ የትራምፕ የ2024 የምርጫ ዘመቻ ከፍተኛ አማካሪ ነበሩ። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ በአስተዳደሩ ውስጥ ምንም ዓይነት ይፋዊ ስልጣን የላቸውም።
ሎርድ ማንደልሰን ሹመቱን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ "በብሪታንያ ፈተናዎች ብቻ ሳይሆን ትልልቅ እድሎችም ያጋጥሙናል፤ እናም እነዚያን እድሎች ለመጠቀም ከመንግሥት ጋር መስራት ትልቅ እድል ነው" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር፣ ሎርድ ማንደልሰንን በመሾማቸው "በጣም መደሰታቸውን" ተናግረዋል።
በመግለጫው " ወዳጅነታችን ወደ አዲስ ምዕራፍ ሲሸጋገር ዩናይትድ ስቴትስ በጣም አስፈላጊ አጋራችን ናት" ብለዋል።
"ፒተር በዚህ ሚናቸው ተወዳዳሪ የሌለው ልምድ ያስገኛሉ፤ አጋርነታችንንም ከጥንካሬ ወደ ጥንካሬ ያሻግሩታል።"
ሰር ኬር በተጨማሪም ዴም ካረንን "ላለፉት አራት ዓመታት በዋጋ ሊተመን ስለማይችለው አገልግሎቷ እና በተለይም ከሐምሌ ወር ጀምሮ በግል ለሰጠችኝ ጥበብ እና ጽናት" በማለት አመስግነዋቸዋል።
የእንግሊዝ አምባሳደሮች በመደበኛነት ልምድ ያላቸው ዲፕሎማቶች ወይም ሲቪል ሰርቫንቶች የነበሩ ቢሆንም፣ አሁን ግን የሌበር ፓርቲ አንጋፋ ፖለቲከኛ በመምረጣቸው "ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ያለን ግንኙነት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያሳያል" ብለዋል ።
ከፍተኛ የወግ አጥባቂ የፓርላማ አባል ሰር አይን ዱንካን ስሚዝ ውሳኔውን አምርመረው ተቃውመዋል።
የሎርድ ማንደልሰንን ሹመት፣ የኋላ ታሪክ "አስተማማኝ ነው ወይስ በአሜሪካ በኩል ቅሬታ ሊፈጥር ይችላል" የሚለውን ለማጣራት ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ሰር ኢይን አክለውም "የዲፕሎማሲው ተሿሚ አይደሉም፣ እርሳቸው የፖለቲካ ተሿሚ ናቸው፤ እና የፖለቲካ ተሿሚዎች ብዙውን ጊዜ በተለይ ለተወሰነ ጊዜ ከፓርላማ እና ከመንግሥት ስራ ውጭ ከሆኑ ጣጣ አያጣቸውም" ሲሉ አክለዋል
እ.ኤ.አ. በ2019 ሎርድ ማንደልሰን ከጣሊያን ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ትራምፕን "ግዴለሽ እና ለዓለም አደገኛ" ሲሉ ገልፀዋቸው ነበር።
እ.ኤ.አ. በ2018 ከኢቪኒንግ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ትራምፕን "ተሳዳቢ" ሲል ጠርተዋቸዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ውስጥ በጣም ወሳኝ በሆነው በዚህ የዲፕሎማቲክ ሹመት ዕጩ መሆናቸው ከታወቀ ጀምሮ፣ ሎርድ ማንደልሰን በትራምፕ ላይ ተለሳልሰዋል።
በሕዳር ወር እሁድ በሚቀርብ የቢቢሲ አንድ ፕሮግራም ላይ ከአሜሪካ ጋር "ከልዩ ግንኙነት ይልቅ አዲስ ግንኙነት" ስለ መፍጠር አጥብቀው ሲናገሩ ነበር።
በተጨማሪም ለሌሎች መገናኛ ብዙኃን "ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር የሚያደርጉትን ለመረዳት እና ለመተርጎም ብቻ ሳይሆን ተጽዕኖ ለማሳረፍ የሚያስችለንን ግንኙነት መመስረት በጣም አስፈላጊ ነው" ብለዋል።
አክለውም የሌበር መንግሥት ከትራምፕ አጋር እና ቢሊየነሩ ኤሎን መስክ ጋር "ግንኙነቱን ለማደስ" መሞከር አለበት ብለዋል ።
የሰር ኪር መንግሥትን ሲተች የነበረው መስክ፣ በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ምንም እንኳ ይፋዊ የመንግሥት ክፍለ ባይሆንም፣ የመንግሥት ቅልጥፍና ዲፓርትመንት አማካሪ ቡድን መሪ ሆኖ መሾሙ ይታወቃል።